ትምህርት አስራ ስድስት: የእግዚአብሔር መንግስትና ጸሎት
6) ምንድ ነው እንድንጸልይ የሚፈለገው? ምንድን ነው የምንጸልየው? ማቴ 6፡10
“ፈቃድህ በሰማያት እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” በለን እንጸለይ። ምክንያቱም በሰማይ ፍጹም በሆነ ሁኔታ የእግዚአብሔር ፈቃድ እንደሚፈጸም በምድር ላይ መፈጸሙ ለእግዚአብሔር መንግስት መምጣት(በመካከላችን መሆን) እርግጠኝነት አስፈላጊ ስለሆነ።
ከውድቀት በኋላ እያንዳንዱ ሰው ከልጅነቱ ጀምሮ ይህን “እፈልጋለሁ!” እያለ ከራሱ ፈቃድ ጋር ጦርነት በማድረግ ይታገላል። ከጎለመሰም በኋላ በቤተሰብ ውስጥ፣ በሥራ ቦታ፣ በአገልግሎት ወይም ሌሎች የግል ፍላጎቶቹን በመወሰን ሂደት ውስጥ ነገሮች ከቁጥጥሩ ውጭ በመውጣት ያስቸገሩታል። ምክንያቱም ልባችን በተፈጥሮ የሚገፋው ወደ እኛ ምንፈልገው ነገር እንጂ እግዚአብሔር ወደሚፈልገው አይደለምና። ለዚህ ነው ኢየሱስ በመንግስቱ ጸሎት ውስጥ፣ "ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” ብለን እንድንጸልይ ያስተማረን።
ይህ የጸሎት ጥያቄ ቀላል አይደለም ምክንያቱም ለእርሱ መገዛትን የመምረጥ ጸሎት ነውና። የእግዚአብሔርን ፍላጎት ከእኛ ፍላጎት በላይ የማያድረግ ምርጫና ውሳኔን የሚጠይቅ ጸሎት ነውና። በሰማይ ያለው ታዛዥነት ወደ ምድራዊ ሕይወታችን እንዲገባ የሚጋብዝ ጸሎት ነውና። ይህን ጸሎት በቅንነት ስንጸልይ እያልን ያለነው "አባቴ ሆይ ፈቃዴ ሳይሆን ፍቃድህ በህይወቴ ይሁን” እያልን ነውና። ይህ ማለት ህይወቴ፣ ቤተሰቤ፣ ቤተክርስቲያኔ እና የምኖርበት ዓለም የሰማይን ታዛዥነት ያንጸባርቁ እያልን ነው። ስለዚህ ይህ ጸሎት ምን ማለት እንደሆነ፣ ኢየሱስ ለምን እንዳስተማረው እና እንዴት ልንረዳው እንደሚገባ ቀጥለን እንመለከታለን።
1. “ፈቃድህ በሰማይ እንድሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን” ማለት ምን ማለት ነው?
ስለ “እግዚአብሔር ፈቃድ” ስንናገር መጽሐፍ ቅዱስ ይህንን ሐረግ በተለያየ መንገድ እንደሚጠቀም መረዳት አለብን። ሊቃውንት ብዙውን ጊዜ የእግዚአብሔርን ፈቃድ በሁለት ገጽታዎች ይለያሉ/ይመድባሉ ይህም፦
1.2 የእግዚአብሔር ሉዓላዊ ፈቃድ (የተደበቀ የእርሱ እቅዱ)
ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በምንምና በማንም ሊቆም የማይችል የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ዓላማ ነው። ይህን አስመልክቶ ዳን 4:35 እንዲህ ይላል። "እጁንም የሚከለክላት ወይም ምንታደርጋለህ? የሚለው የለም"። ይህም ማለት እግዚአብሔር በእቅዱ ውስጥ የፈለገውን ይፈቅዳል የፈለገውን ይሾማል ማለት ነው። ማንም ይሄንን መቆጣጠር አይችልም። እናም ጌታችን ኢየሱስ እያስተማርን ያለው ይህን የእግዚአብሔር ዘላለማዊ እቅድ ለመለወጥ እንድንጸልይ አይደለም።
1.2 የተገለጠው የእግዚአብሔር ፈቃድ (ትእዛዛቱ እና የሞራል ፈቃዱ)
ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በቅዱሳት መጻሕፍት እግዚአብሔር ያዘዘውና እንዴት መኖር ፣ ማሰብ፣ መናገር እና ማድረግ እንዳለብን የሚወስን ነው። መዝ 40፡8 እንዲህ ይላል። "አምላኬ ሆይ፥ ፈቃድህን ላደርግ ወደድሁ፥ ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው”። ጌታችን ኢየሱስ በዚህ ምድር በአምላክ ሰውነቱ በተመላለሰ ጊዜ የፈጸመው አንድና ብቸኛ ነገር የእግዚአብሔርን ፈቃድ በምድር ላይ መታዘዝ ነው። ስለዚህ “ፈቃድህ በምድር ትሁን” ብለን ስንጸልይ እያልን ያልነው"እግዚአብሔር ሆይ፣ በሁሉም የህይወቴ ክፍል ቃልህን እንዲታዘዝ እርዳኝ።"
2. የእግዚአብሔር ፈቃድ በሰማይ እንዴት ነው የሚፈጽመው?
የእግዚአብሔር ፈቃድ በሰማይ እንዴት እንደሚፈጽም ቅዱስ ቃሉ የሚከትለውን አብነት ወይም ማሳያ ይነግርናል እነርሱም፦
2፡1. ሰማይ ሙሉ በሙሉ ፈጽሞ ይታዘዛል።
መዝ 103፡20–21 መላእክት “ቃሉን እንደሚያደርጉ” እና “የቃሉን ድምፅ እንደሚታዘዙ” ይነግረናል። ምንም ማመንታት ክርክር የለም። ከፊል መታዘዝም የለም። ሰማይ ሙሉ በሙሉ ይታዘዛል ምክንያቱም ሰማይ የእግዚአብሔርን ፍጹም ቅድስና ያውቃልና።
2:2. ሰማይ ወዲያውኑ ያለምንም መዘግየት ይታዘዛል
እግዚአብሔር ሲናገር መላእክት ይንቀሳቀሳሉ። ሁለተኛ ሀሳብ የለም፣ ቅሬታ የለም፣ ምንም መዘግየት የለም። ሰማይ ለእግዚአብሔር ትእዛዛት ወዲያውኑ ምላሽ ይሰጣል።
2፡3. ሰማይ በደስታ ይታዘዛል
ራዕይ 5:6-14 የሰማይ አካላት ማለትም ሀያ አራቱ ሽማግሌዎችና ቅዱሳን መላእክቱ ሲያመልኩ፣ ሲያገለግሉ እና ሲደሰቱ ይታያል። በሰማይ መታዘዝ ሸክም አይደለም በደስታ የሚፈጽም ተግባረ እንጂ ። በሰማይ የእግዚአብሔር ፈቃድ ፍጹም፣ ያማረ እና መልካም እንደሆነ ያታወቃል።
ስለዚህ “ፈቃድ በሰማይ እንደሆንች እንዲሁ በምድር ትሁን” በሚለው ጸሎት ውስጥ ጌታችን ኢየሱስ ወደ በስማይ ወዳለው ታዛዥነትና መገዛት እየጠራን ነው። በሰማይ በግዳጅ መታዘዝ የለም። በሰማይ ሳይፈልጉ በጭንቀት መታዘዝ ሳይሆን በደስታ፣ በፈቃደኛነት፣ ወዲያው በመታዘዝ ምላሽ የሚሰጥበት የእግዚአብሔር ፍቃድ መፈጽም ነው ያለው።
3. ፈቃድ በምድር ላይ ትሁን/ትፈጸም ምን ማለት ነው?
ፈቃድህ በምድር ትሁን ማለት አሁን በሰማይ ያለውን ያንን የእዚአብሔር ፈቃድ የሚፈጽምበትን ሞዴል ወደ ምድር እናመጣለን ማለት ነው። በሕይወታችን እንደ ሰማይ የሆነው መታዘዝ ሲመጣ ደግሞ፦
3፡1. በግል ህይወታችን ለእግዚአብሔር ፈቃድ ብቻ መገዛት ይሆናል
ይህ ጸሎት መልሱ በአማኝ ልብ ይጀምራል። ምክንያቱም ለአለም ከመጸለያችን በፊት ለራሳችን መጸለይ ስላለብን። ጌታችን ኢየሱስም ለራሱ እንዲህ ብሎ ጸለየ “የአንተ እንጂ የኔ ፈቃድ አይሁን”። (ማቴ 26፡39)ኢየሱስ ኃጢአት የሌለበት፣ ንፁህና ጻድቅ ሆኖ ሳለ ፈቃዱን ለአብ አሳልፎ ከሰጠ፣ እኛስ እንዴት አብልጠን ይህን ማድረግ አለብን? "ጌታ ሆይ ምኞቴን ቀይርልኝ፣ የምትፈልገውን እንድፈልግ አስተምረኝ፣ ውሳኔዎቼን ሁሉ እንደ ቃልህ አድርግልኝ ብለን እንጸልያለን። ፈቃድህ በሰማይ እንድሆንች በምድር ትሁን የሚለው ጸሎት ይህ ነው።
3.2 በሞራልና በስነ-ምግባር ስርነቀል ለውጥ ማድርግን መጠየቅ/መፍቅድ ነው።
1ኛ ተሰ 4፡3 እንዲህ ይላል። "ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም መቀደሳችሁ ነው”።የእግዚአብሔር ፈቃድ በከዚህ አኳያ ምስጢር አይደለም። እግዚአብሔር ሁሌም በኑሮአችን ሁሉ ከሕዝብ የሚጠቀው ቅድስና ነው። እግዚአብሔር ንጽህናን፣እውነትን፣ ታማኝነትን፣ ፍቅርን፣ ገርነትን እና ይቅርታን እንድንኖር ይፈልጋል ።እንግዲህ “ፈቃድህ ይሁን” ብለን ስንጸልይ እግዚአብሔር ክርስቶስን እስኪያንጸባርቅብን ድረስ ባሕርያችንን እንዲለውጥ እየጠየቅን ነው።
ማጠቃለያ
በሰማያት፣ የእግዚአብሔር ፈቃድ ፍጹም በሆነ ሁኔታ፣ በደስታ፣ እና ወዲያውኑ ይፈጸማል። ስልዚህ ይህን ጸሎት ስንጸልይ ፈቃድህ “በሕይወቴ ፣በቤቴ፣ በቤተክርስቲያኔና በምድር እንደ ሰማይ ሁሉ የእግዚአብሔ ፈቃድ ይፈጸም ብለን እንጸልያለን ማለት ነው። አለመታዘዝን አሳልፎ መስጠት በየቀኑ ፈቃድህ እንጂ ፈቃዴ አይሁን ማልት ነው። በዚህ ጽሎት መስረት እግዚአብሔር አሁን እንድታዘዘው የሚጠይቅህ የትኛው የህይወታችን ክፍል ነው? በቤተሰባችን፣ በቤተክርስቲያናችም ወይስ በምንኖርበት ማህበረሰብ ውስጥ? ፈውቃዱን ለመታዘዝ የእግዚአብሔርን ኃይል ጠይቁ።
Source: https://cmaeec.com/w...
John 3:16
Whoever believes in him shall not perish but have eternal life.