Home » Sunday sermon – January 25, 2026

በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ መኖር

Last updated on January 25, 2026 - by Pastor Tariku Eshetu

የእግዚአብሔር መንግሥት - በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ

ዘፍጥረት 1–50

መግቢያ

ሁሉም ሰው በመንግሥት ሥር ይኖራል። አንዳንዶች በራሳቸው ሀገር መንግሥት፣ ሌሎች በሰው ሥርዓት፣ ሥልጣን፣ ገንዘብ ወይም ወግና ባህል ሥር ይኖራሉ። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛና ዘላለማዊ መንግሥት አንድ ብቻ እንደሆነ ያስተምራል እርሱም የእግዚአብሔር መንግሥት። ብዙ አማኞች የእግዚአብሔር መንግሥት የሚጀምረው በአዲስ ኪዳን በኢየሱስ ነው ብለው ያስባሉ። እንደ እውነቱ፣ ከሆን ግን መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔርን መንግሥት የሚያስተዋውቀው ከመጀመሪያው የቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ነው። የዘፍጥረት መጽሐፍ መጀመሪያውን የሚናገር መጽሐፍ ብቻ አይደለም የእግዚአብሔርን ንጉሳዊ አግዛዝ ጭምር የሚነግርን መጽሐፍ ነው። የእግዚአብሔር መንግሥት በፍጥረት ይጀምራል፣ በሰው ዓመፀኝነት ይሞገታል፣ ነገር ግን በእግዚአብሔር ሉዓላዊ አገዛዝ እና የአዳኝነት ተስፋዎች በኩል ፍጻሜን ያገኛል።

I. ንጉሰ እግዚአብሔር፡ መንግስቱን መሰረተ (ዘፍ 1-2)

መጽሐፍ ቅዱስ “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ”። በሚል የንግሥና መግለጫ ንግግሩን ይጀምራል ይህ ንጉሣዊ ቋንቋ ነው። ዘፍጥረት ስለ እግዚአብሔር ሥልጣን አይከራከርም ነገር ግን እውቅና በመስጠት ንግስናውን ያርጋግጣል። ይህም የታየበት መንገድ፦

1. የፍጥረት መፈጠር እንደ ንጉስ ድርጊት/ተግባር መሆኑ

እግዚአብሔር በትዕዛዝ ይፈጥራል፡- “እግዚአብሔርም አለ…” ንጉሱ በትእዛዝ ቃል ይገዛል፣ ፍጥረትም ወዲያውኑ ይታዘዛል። ትግል የለም፣ ተቃውሞ የለም፣ እኩል የሚሆን ወይም የሚገዳድር ኃይል የለም። እግዚአብሔር ይናገራል እውነታ ድግሞ ምላሽ ይሰጣል። ይህም እግዚአብሔር የፍጥረት አካል እንዳልሆነ ያስተምረናል እርሱ በፍጥረት ላይ ጌታ ነው። አጽናፈ ዓለሙ በዘፈቀደ አይደለም የሚተዳደረው በንጉሱ የትዕዛዝ ቃል እንጂ።

2. ሰው የንጉሱን መልክና አምሳይ -ተሸካሚ መሆን (አዳምና ሔዋን)

ዘፍ 1፡26-28 የሰው ልጅ በእግዚአብሔር መልክ ምሳሌ እንደተፈጠረ እና ስልጣን እንደተሰጠው ይነግረናል። በጥንቱ ዓለም ነገሥታቱ በሚገዙበት ግዛቶች ውስጥ ምስላቸውን ያኖሩ ነበር። እግዚአብሔርም በምድር ላይ እንዲሁ አድርጎል፣ነገር ግን እርሱ ሕያዋን ምስሎችን ነው ያስቀመጠው። የሰው ልጆች የተፈጠሩት በምድር ላይ የእግዚአብሔርን አገዛዝ ለመወከል ነው።ይህ ገዢነት ደግሞ ሌላውን መበዝበዝ አይደለም ነገር ግን በእግዚአብሔር ሥልጣን ሥር በመሆን ባላደራነትን መፈጸም ነው።

3. ኤደን ገነት እንደ መንግሥት ኅብረት

ኤደን ገነት ከአትክልት ስፍራነት በላይ ነው። እግዚአብሔር ከህዝቡ ጋር የሚኖርበት የተቀደሰ ቦታ ነው። እግዚአብሔር ንጉሥ ነው፣ የሰው ልጅ ደግሞ የንጉሱ ታዛዥ ነው፣ይህ ግንኙነት ባልተቋረ ጊዜ ሁሉ ፍጥረት ሰላም ነው። ይህ የእግዚአብሔር መንግሥት የመጀመሪያ ወይም ጥንታዌ ሥዕል/ንድፍ ነው። እግዚአብሔር የፈጠረን በእርሱ አገዛዝ ሥር እንድንኖር እንጂ በራሳችን አገዛዝ ስር እንድንኖር አይደለም።

II. መንግሥቱ ከሰው ውስጥ ሰው ድግሞ ከኤደን ገነት በአመጽ ምክንያት ወጣ፡- (ዘፍጥረት 3–11)

1. የሰው ውድቀት የእግዚአብሔርን ንግሥና አለመቀበል ነው።

ዘፍ 3 የሚነግረን ስለ አለመታዘዝ ብቻ ሳይሆን ስለ አመፀኝነትም ጭምር ነው። አዳምና ሔዋን የእግዚአብሔርን ሥልጣን ተቃውመው ራስን መቻልን መረጡ። በዚህ ምክንያት የእግዚአብሔር አገዛዝ ከሰው ልብ ወጣ ሰውም ከኤደን ገነት ወጣ።ስለዚህ ኃጢአት ማለት “ራሴን እገዛለሁ”ማለት ነው።የኔ ገዢ እኔ ነኝ ማለት ነው። ስልዚህ የሰው ልጅ እግዚአብሔርን እንደ ንጉሥ ሳይቀበል ሲቀር መንግሥቱ ይለያል።

2. ከእግዚአብሔር መንግሥት መገኘት መውጣት ነው።

አዳምና ሔዋን ከኤደን ገነት ተባረሩ። ይህ የመጀመሪያው ስደት ወይም ከመንግስቱ መገኘት መውጣት ነው። ቢሆንም የሰው ልጅ በእግዚአብሔር ስልጣን ሥር ይኖራል ነገር ግን በእግዚአብሔር አገዛዝ መገኘት ውስጥ የመኖርን ልዩ መብቱን አጥቶአል።

3. የእግዚአብሔር አገዛዝ በሌላቸው ሰብዓዊ መንግሥታት መገዛት ሆነበት።

ዘፍ 4–11 የኃጢአትን መብዛትና እድገት ያሳያል—አመፅ፣ ሙስና፣ ትዕቢት እንዲሁም የባቤል ግንብ የሰው ልጅ ያለ እግዚአብሔር አገዛዝ መንግሥት ለመገንባት የሚያደርገውን ሙከራ ያመለክታል።ለዚህ ደግሞ እግዚአብሔር በፍርድ ምላሽ ይሰጣል። የሚሰጠውም ምላሽ የመንግስቱን እቅድ በማጥፋት ሳይሆን የሰውን ኩራት በመግታት ነው።ምክንያቱም ለእግዚአብሔር ሳይገዙ ሕይወትን ለመገንባት የሚደረግ ሙከራ ሁሉ ግራ መጋባትንና ኪሳራን ያስከትላልና።

III. የእግዚአብሔር አገዛዝ በቃል ኪዳን ውስጥ (ዘፍ 12–22)

የሰው ዓመፅ የእግዚአብሔርን መንግሥት እቅድ አይሰርዝም። ይልቁንም እግዚአብሔር በተስፋ ቃል የመንግሥቱን ለመመለስ በቃልኪዳን እንዲጀምር አደረገው እንጂ። የመንግሥቱ ቃል ኪዳን፦

1. በአብርሃም ጥሪ ይጀምራል

ዘፍ 12፡1-3 የለውጥ ነጥብ ነው። እግዚአብሔር አሕዛብን ሁሉ ይባርክ ዘንድ አንድ ሰው መርጧል። ይህ የመንግስት ተሃድሶ በዘር መልክ ነው። እግዚአብሔር ቃል ኪዳንም ገብቶአል ይህም ቃል ኪዳን ምድርን፣ ዘርን፣ እና በረከትን ይሚያካትት ቃል ኪዳን ገብቷል—እንዚህ ሁሉም የመንግስት እውነታዎች ናቸው።

2. በእምነት በተገነባ መንግሥት ታሪክ ውስጥ ይቀጥላል።

አብርሃም ጥሪውን ተቀብሎ ከወጣ በኋላ ርስቱን በጉልበቱ ድል አድርጎ አልወርሰም።ነገር ግን በእምነት እየተመላለሰ እንደ ምጻተኛ ይኖር ነበር። ይህ የሚያስተምረን የእግዚአብሔር መንግሥት በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ የሚያድግው በሰው ኃይል ሳይሆን በመተማመን እና በመታዘዝ መሆኑን ነው። የእግዚአብሔር መንግሥት የሚያድገው በእምነት በተሞላ ታዛዥነት እንጂ በሰው ቁጥጥር ወይም ጥርት አይደለም።

III. ስውሩ የእግዚአብሔር መንግሥት አገዛዝ። (ዘፍጥረት 37–50)

የዮሴፍ ታሪክ እግዚአብሔር ዝም ቢልም እንዴት እንደሚገዛ ያሳየናል። ዮሴፍ በወንድሞቹ ተከድቶአል፣ ለበባርነት ተሽጦአል፣ ታስሯል—እግዚአብሔር ግን ፈጽሞ ሁኔታው መቆጣጠር አላቆመም ነበር። ይህን የተርዳው ዮሴፍ በህይወቱ ማብቂያ ለወንድሞች አንድ ሚስጥር ነግራቸው "እናንተ ክፉ ነገርን አሰባችሁብኝ እግዚአብሔር ገን ዛሬ እንድሆንው በዙ ህዝብ እንዲድን ለማድረግ ለመልካም አሰበው።” ይህ የእግዚአብሔር መንግሥት ሥነ-መለኮት ነው የእግዚአብሔር አገዛዝ ብዙውን ጊዜ የማይታይ ነው፣ ነገር ግን ሁልጊዜ ንቁ ነው/በስራ ላይ ነው። በመከራ ውስጥም እንኳ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት ዓላማዎች እየገሰገሱ ነው።

IV. የሚመጣው ንጉሥ ወይም የሚጠበቀው መንግሥት ነው።

ኦሪት ዘፍጥረት በተስፋ ያበቃል። የተስፋው ዘር የተስፋ ቃል (ዘፍጥረት 3:15)የተስፋው ዘር የንግሥና መስመር (ዘፍጥረት 49:10) የተስፋው ቅል ዘር የሆነውና የወደፊቱ ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስ በዘፍጥረት የተጀመረውን የመንግስቱን የተስፋቃል ፈፅሟል።ይህንንም እንዲህ ሲል አስታውቆል። "የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለች" ማቴ 4:17

አዳም በወደቀበት፣ ክርስቶስ ታዘዘ። የሰው ልጅ ባመፀበት ቦታ ክርስቶስ ተገዛ።ስለዚህ በመስቀል ሞቱ እና በትንሳኤው፣ ኢየሱስ ወደ እግዚአብሔር መንግስት ይመልሰናል።

ማጠቃልያ

ኦሪት ዘፍጥረት እግዚአብሔር ንጉሥ እንደሆነ ያስተምረናል፣ መንግሥቱም እውነት ነው፣ስልሆነም ሁሉም ሰው ለመንግቱ ጥሪ ምላሽ መስጠት አለበት። ጥያቄው እግዚአብሔር ይነግሣል አይነግስም የሚለው አይደለም ፣ ነገር ግን በእርሱ አገዛዝ ሥር ለመኖር ፈቃደኛ ነን ወይ የሚለው ነው። ንሰሐ እንግባ እራሳችንን ለመግዛት አንጣጣር። ለእግዚአብሔር ስልጣን እንገዛ። ስለሚጠቅመን በሁሉ ላይ የሚነግሰውን ንጉስ እንመን። እግዚአብሔር ንጉስ ነው መንግስቱም ለዘላለም ነው። አሜን

Source: https://cmaeec.com/w...

the cross
Jesus is Lord
John 3:16

Whoever believes in him shall not perish but have eternal life.