Home » የዘፍጥረት መጽሐፍ (Tuesday Sermons) » Tuesday – March 24, 2026

የዘፍጥረት መጽሐፍ ታሪካዊ ዳራ

Last updated on March 24, 2026 - by Pastor Tariku Eshetu

3ኛው ሳምንት፡ የሰው መውደቅና የኃጢአት ወደ ዓለም መግባት

የርዕስ ጉዳይ ቅደም ተከተል፡-“ከገነት ወደ ጸጋው፦ የሰው ውድቀት፣ የኃጢአት መስፋፋት እና የእግዚአብሔር ምሕረት መሻት” የሚል ነው።
ዋናው ምንባብ፡- ዘፍጥረት 3፡1-24
ተዛማጅ ምንባባት፡ ዘፍ 1-2; ሮሜ 5:12; 1ኛ ቆሮ 15:22

መግቢያ

ወንጌልን፣ድነትን፣ ጸጋን እና መስቀልን ለመረዳት ከፈለግን መጀመሪያ ውድቀትን መረዳት አለብን። ብዙ ሰዎች ጠቃሚ ጥያቄዎችን ይጠይቃሉ አለም ለምን ተሰበረ? መከራ፣ ስቃይ እና ሞት ለምን ኖረ? ሰዎች ትክክል የሆነውን እያወቁ ለምን ኃጢአት ይሠራሉ? የሚሉ ናቸው። የነዚ ጥያቄዎች መልስ በሮሜ መጸሐፍ ሳይሆን በዘፍጥረት መጸሐፍ ይጀምራል ። ከዚህ አንጻር ዘፍጥረት ምዕራፍ 3 ኃጢአት እንዴት ወደ ዓለም እንደገባ ሲያብራራልን፣
ዘፍጥረት ምዕራፍ 4-11 ደግሞ ኃጢአት እንዴት እንደተስፋፋ ያሳየናል። የዘፍጥረት መጸሐፍ በእግዚአብሔር መልካም ፍጥረት የሚጀምር መጽሐፍ ነው። ሆኖም በዘፍጥረት ምዕራፍ 3 ግን ሁሉም ነገር ይለወጣል። ይህ ምዕራፍ ኃጢአት እንዴት ወደ ዓለም እንደገባ እና እያንዳንዱ ሰው ዛሬ አዳኝ ለምን እንደሚያስፈልገው ያብራራል።

I. ከውድቀት በፊት የእግዚአብሔር መልካም ፍጥረት ( ዘፍ 1:31፣ 2:15–17)

Ø " እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፥ እጅግም መልካም ነበረ። ( ዘፍጥረት 1:31) የሚለው ገለጣ የእግዚአብሔር የፈጠራ ስራ የሚያካትተውን የሰውን በእግዚአብሔር መልክ መፈጠር፣ (ዘፍ 1፡26-27) የሚያካትት ነው።ሰው የተፈጠረው ከእግዚአብሔር ጋር ለመተባበርና በእግዚአብሔር ሥልጣን ሥር ለመገዛት ነው።

Ø በዚህ ወቅት አዳም ተሳትፎ( Adam functioned as)፡- እንድ ንጉሥ - የፍጥረት ገዥ፣ እንደ ካህን - በእግዚአብሔር ፊት ማገልገል ፣እንደ ተወካይ - ለሁሉም የሰው ልጅ በቆመ ነው። ዘፍጥረት 2:15 አዳም የአትክልት ስፍራውን 'ያበጃትና ይጠብቃት' ሲል ይናገራል፤ ይህ ቃል ከጊዜ በኋላ በማደሪያው ድንኳን ውስጥ ካህናት ይገለገሉበት የነበረውን ሁኔታ የሚያሳይ ነበር። የዚህ ቃል ጠቃሚ እውነት አዳም ሰው ብቻ አልነበረም የሚልና እርሱ የሰው ልጅ የቃል ኪዳን ተወካይ ነበር የሚልም ነው።

Ø ኃጢአት ወደ ዓለም ከመግባቱ በፊት እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ እጅግ መልካም ነበር። "እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፥ እጅግም መልካም ነበረ። (ዘፍ 1:31) አዳምና ሔዋን ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም በሆነ ኅብረት ኖሩ፣ ምንም እፍረት፣ ፍርሃት ወይም የጥፋተኝነት ስሜት አላጋጠማቸውም ነበር። በእግዚአብሔር በአምላክ ፍቅርና ሥልጣን ሥር ለመኖር ነፃነት አግኝተዋል።

Ø እግዚአብሔር አዳምን በአትክልቱ ስፍራ አስቀመጠውና አንድ ትዕዛዝ ሰጠው። "መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ" ( ዘፍ 2:17) ይህ ትእዛዝ ጨቋኝ አልነበረም። የመተማመን እና የመታዘዝ ፈተና ነበር እንጂ። መልካሙንና ክፉውን የመለየት መብት ያለው እግዚአብሔር ብቻ ነው።ሰው ይህ መብት አልነበረውም። እዚህ ላይ ያለው ቁልፍ እውነት፡-ኃጢአት የእግዚአብሔር ንድፍ ወይም የቅድመ ፍጥረት አካል አልነበረም ነገር ግን ኀጢአት በሰው አለመታዘዝ ወደ ዓልም ገባ የሚል ነው።

II. ዛፉ ምንድነው፡ የመተማመን እና የሥልጣን ፈተና ነው። ( ዘፍጥረት 2:16–17)

መልካምንና ክፉን የሚያስታውቀው ዛፍ ክፉ አልነበረም። ትክክለኛው ጥያቄ የነበረው ግን መልካሙን እና ክፉውን የሚወስነው ወይም የሚበይነው ማን ነው የሚል ነው? እግዚአብሔር ወይስ ሰው?። ይህን ተዕዛዝ መታዘዝ ማለት መታመን ማለት ነው ፣ ባአንጻሩ አለመታዘዝ ደግሞ ነፃነት ወይም በእግዚአብሔር ስልጣን ላይ ማመጽ ማለት ነው። የሰው ውድቀት በዋናነት ፍሬ መብላቱ አይደለም ነገር ግን የእግዚአብሔርን ሥልጣን አለመቀበሉ ነው። መልካምና ክፉውን ማወቅ የእግዚአብሔር ስልጣን ብቻ ነበር።

I. ሰው የወደቀበት ፈተናው፡ በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተደረገ ጥቃት ነብር
(ዘፍጥረት 3:1–5)
Ø ዘፍጥረት 3 የሚጀምረው በሔዋንና በእባቡ መካከል ባለው ውይይት ነው።በዚህ ውይይት ውስጥ እባቡ የእግዚአብሔርን ቃል ይጠይቃል ወይም ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል እንዲህ ብሎ"በእውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዞአልን…?" (ዘፍጥረት 3:1) የሰይጣን የመጀመሪያ መሳሪያው ጥርጣሬ ነው።ስለዚህ ሰዎች የእግዚአብሔርን እውነት እንዲጠራጠሩ ያደርጋል።በዚህም የእግዚአብሔርን ቃል ያጠቃል ማለት ነው።

Ø እባቡ የእግዚአብሔርን ቃል ያጣምማል እንዲ አድርጎ፦ "በእርግጥ ሞትን አትሞቱም ( ዘፍ 3:4) ይህ ቀጥተኛ ውሸት ነው።
ሰይጣን ከእግዚአብሔር ቃል ጋር በግልጽ ይጋጫል።ይህም የእግዚአብሔርን ቃል የማጥቃት አካል ነው።

Ø እባቡ የእግዚአብሔርን ባሕርይ ያዛባል እንዲህ አድርጎ "ከእርሷ በበላቹ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔር መልካምና ክፉውን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ ።" (ዘፍ 3:5) በማለት የእግዚአብሔርን ባህርይ በውሸቱ ያዛባል ። በዚህም እያለ ያለው እግዚአብሔር መልካም ነገርን ለሰው ይከለክላል፣ እግዚአብሔር ሊታመን አይችልም፣ነፃነት ከመታዘዝ ይሻላል እያለ ነበር። ይህ የኃጢአት ሁሉ ሥር ነው እርሱም የእግዚአብሔርን ሥልጣን አለመቀበል ነው። ኃጢአት በሰው ህይወት የተጀመረው በእግዚአብሔር መታመን ሲቆምና እግዚአብሔርን በመጠራጠር ሲተካ ነው።

III. ውድቀት፡ ያለመታዘዝ ድርጊት/ተግባር ነው። (ዘፍጥረት 3:6)

"ሴቲቱም የዛፉ ፍሬ ለመብላት መልካም ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ ለጥበብም መልካም እንደሆነ አየች ከፍሬውም ወስዳ በላች።"ሔዋን ከመታዘዝ ይልቅ ምኞቷን መረጠች። ከእሷ ጋር የነበረው አዳምም በላ። ይህን ያድረገው በድንቁርና ወይም ባልማውቅ አልነበረም ነገር ግን አመጾ ነው እንጂ። ይህ ቅጽበት ውድቀት ይባላል ፣ ምክንያቱም የሰው ልጅ ንፁህ ከመሆን ጥፋተኛ ወደ መሆን ከኅብረት ወደ መለያየት ከሕይወት ወደ ሞት ተሸጋገረ።ስለዚህ ኃጢአት ሕግን መጣስ ብቻ አይደለም የእግዚአብሔርን አገዛዝ አለመቀበልም ነው።

V. የኃጢአት ፈጣን ውጤቶች (ዘፍጥረት 3:7-13)

ንፁህነት በውርደት ተተካ "እራቁት መሆናቸውን ተረዱ። " (ቁ.7) ኃጢአት የጥፋተኝነት ግንዛቤን ኩነኔን አምጥቷል። ህብረት በፍርሃት ተተካ "ዕራቁቴንም ስለሆንሁ ፈራሁ ተሸሸግሁም" (ቁ.10) ኃጢአት ሁል ጊዜ ሰዎች ከእግዚአብሔር እንዲሰወሩ/እንዲሸሸጉ ያደርጋቸዋል። ኃላፊነት በተጠያቂነት ተተካ አዳም ሄዋንን ወቀሰ ሔዋን እባቡን ወቀሰች። ኃጢአት ሁሉንም ግንኙነቶች አበላሸ።ሰው ከእግዚአብሔር ጋርና ከሌሎች ጋር እንዲሁም ከራሱ ጋር ቅራኔ ውስጥ ገባ።

VI. የእግዚአብሔር ፍለጋና ጥያቄ፡- “አዳም ሆይ ውዴት ነህ?” (ዘፍ 3:9)

ይህ ክፍል በዘፍጥረት ውስጥ ካሉት በጣም አስፈላጊ ጥቅሶች አንዱ ነው። እግዚአብሔር መረጃ አይፈልግም።ስለዚህ ወዴት ነህ የሚለው ቃል የሚያመለክተው እግዚአብሔር ከፍርድ በፊት ጸጋን ማቅረብን እንደሚያሰቀድም ነው። ከዚህ ቅጽበት ጀምሮ፣ኃጢአተኞችን የሚያሳድድ ሳይሆን የሚፈልገን አምላክን መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጣልናል።ድነት ሁል ጊዜ የሚጀምረው እግዚአብሔር እኛን ከመፈለጉ ነው። ሰወች እግዚአብሔርን ከመፈለጋቸው የሚጀምር አይድልም።

VII. የእግዚአብሔር ፍርድ እና ፍትህ (ዘፍ 3:14–19)

እግዚአብሔር ቅዱስ ነው እና በኃጢአት ላይ መፍረድ አለበት ስለዚህ እባቡን "ጭንቅላትህን ይቀጠቅጣል ብሎ አወጀ " (ዘፍ 3:15) ይህ የመጀመሪያው የወንጌል ተስፋ ነው።ሰይጣንን የሚያሸንፈው የወደፊቱ አዳኝ ነው። ሴቲቱ በወሊድ ጊዜ ህመም ወይም ጭንቅ እንዲበዛባት ሆነ የተበላሸ ስምምነት በግንኙነታቸው ውስጥ ሆነ። ሰውየው በሚያሠቃይ የጉልበት ሥራ ውስጥ ገባ። ሞትም በሰው ሕይወት ውስጥ ገባ " አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ" (ቁ.19) ኃጢአት ሁል ጊዜ ወደ ሞት ይመራል።

VIII የመጀመሪያው የወንጌል ተስፋ (ዘፍጥረት 3:15)

"እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል." ይህ ቁጥር ፕሮቶኢቫንጀሊይም (Protoevangelium) ይባላል። ትርጉሙም የመጀመሪያው የወንጌል ስብከት ማለት ነው። በዚህ ስብከት እግዚአብሔር አዳኙን እንድሚልክ ቃል ገብቷል። የሚመጣው ቤዛ ደግሞ ሰውን በሰይጣን ላይ ድል ያቀዳጃል የሚል ነው። በ“ዘሯ” በኩል የተባለውን ተስፋ ሰወች ሁሉ ይገነዘቡ ዘንድ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ፣ የዘፍጥረት መጸሀፍ ተስፋ የተደረገበትን ዘር መስመር ይከተላል። በዚህ መሰረት ሴት አቤልን ተክቷል፣ ኖህ የሰውን ልጅ/ዘር ያስቀጥላል። አብርሃም የተስፋውን ቃል ተቀብሏል። ኦሪት ዘፍጥረት ፍጻሜውን ለማግኘት የሚጠባበቅ የተስፋ መጽሐፍ ነው።

IX. የእግዚአብሔር ምሕረት ወይም የቆዳ ልብሶች (ዘፍ 3:21)

Ø "እግዚአብሔር አምላክም ለአዳምና ለሚስቱ የቁርበት ልብስ አለበሳቸው። ይህ የሚያሳየው ኃጢአት ሞትን ይጠይቃል። እግዚአብሔር የሰውን እራቁትነት መሸፈኛን ይሰጣል።የእግዚአብሔር ፀጋ ከሽንፈት/ከውድቀትም በኋላም በግልጽ ይታያል የሰውን እፍረትን ለመሸፈን ደም ፈሰሰ ይህም ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ የቤዛነት ስራ ይጠቁማል።

X. ከኤደን መባረረና ስውሩ ምሕረት (ዘፍ 3:22–24)

እግዚአብሔር አዳምና ሔዋንን ከገነት ያስወጣቸው እነርሱን ለማጥፋት ሳይሆን ከኃጢአት ዘላለማዊ ሕይወት ለመጠበቅ ነው። በዚህ መስረት ጥበቃ የሚደረግለት ዛፍ የሚከተሉትን ያሳያል የሰው ከእግዚአብሔር መለያየት እውነት መሆኑን።የእግዚአብሔር ተስፋ በእርሱ ተጠብቆ የሚገኝ መሆኑን።እግዚአብሔር የድነትን መንገድ ይጠብቃል ተስፋወንም አይሰርዘውም።

XI. ኃጢአት በሰው ልጆች በኩል ይሰራጫል። (ዘፍ 4-11)

የዘፍጥረት መጸህፍ የኃጢአትን መሰርጨት ወይም መብዛት ያሳያል፡በዚህ መስርት ዘፍጥረት 4 - መገዳደል (ቃየን እና አቤል) ዘፍ 4:23 - ዓመፅ ተከበረ (ላሜሕ) ዘፍ 6 -ኀጢአት ተንሰራፋ ዘፍ 11 – የጋራ አመጽ በእግዚአብሔር ላይ (ባቤል) ኃጢአት የትውልድ ሆነ፣ባህል ሆነ፣ሥርዓታዊ ሆነ። ይህ የኀጢአት መንስራፋት ሂደት የሰው ልጅ እራሱን ማዳን ያልቻለው ለምን እንደሆነ ይገልፃል ወይም ያሳያል።

በኀጢአት መንሰራፋት ውስጥ የምንመለከተው ሌላው እውነት ኃጢአት ወደ ሰው ልጆች ሁሉ መሰራጫቱን ወይም መድረሱን ነው። (ሮሜ 5:12) "ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት" በአዳም ውድቀት ምክንያት ሁሉም ሰዎች የሚወለዱት በኃጢአተኛ ተፈጥሮ ሆነ።ሁሉም ሰዎች ሞት ደረሰባቸው ማንም ራሱን ማዳን አልቻም።ስልዚህ ሰወች ኃጢአተኞች የሚሆኑት ኃጢአት ስለሰሩ አይደለም።ነገር ግን ኃጢአት የሚሰሩት ኃጢአተኞች በመሆናቸው ነው ።ይህ በቀዳሚው አድም ምክንያት የተገኘ ነው።

ክርስቶስ፡ ሁለተኛው አዳም (1 ቆሮ 15:22)
ፊተኛው አዳም ኃጢአትን፣ሞትን ፣መለያየትን አመጣ። ሁለተኛው አዳም ኢየሱስ ጽድቅን፣ ሕይወትን፣ እርቅንና መዳንን አመጣ። አዳም በወደቀበት፣ ክርስቶስ ታዘዘ። በዚህም ኃጢአት በበዛበት፣ ጸጋው የበለጠ ጨመረ።ፊተኛው አዳም ሁለተኛው አዳም ያላቸው ንፅፅር ይህ ነው።

ማጠቃለያ

ከኤደን ገነት ወይም ከአትክልት ስፍራ ከመጥፋት እስከ መጪው መንግሥት ያለውን ነገረ-መለኮታዊ ታሪክ ለማሳየት ዘፍጥረት የሚጀምረው ሰው በጠፋበት የአትክልት ቦታ ነው።መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ታሪክ የሚያጠናቅቀው የአትክልት ቦታውን በማደስ ነው። ነገር ግን የእግዚአብሔር ጥያቄ አሁንም "የት ነሽ፧"የት ነህ” እያለ ያስተጋባል። በኃጢአት ውስጥ እንሸሸጋለን ወይስ ወደሚፈልገን አምላክ እንመለሳለን? የሚል ነው።

Source: https://cmaeec.com/w...

the cross
Jesus is Lord
John 3:16

Whoever believes in him shall not perish but have eternal life.