Home » Sunday sermon – May 24, 2026

በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ መኖር

Last updated on May 24, 2026 - by Pastor Tariku Eshetu

የእግዚአብሔር መንግሥት በመጸሀፈ ዕዝራ

በቃሉ እና በእግዚአብሔር ሕልውና መታደስ
የንባብ ክፍል፦ ዕዝራ 1:1-4፤ 3:10-13፤ 7:10፤ 9:8-9

መግቢያ

የዕዝራ መጽሐፍ እግዚአብሔር ሕዝቡን ከምርኮ እንዴት እንደመለሰ የሚተርክ መጸሀፍ ነው።ስለዚህ መጽሀፉ በመጀመሪያ ሲታይ፣ ስለእስራኤል ወደ አገር መመለስ፣ ቤተ መቅደስ ስለ መሥራቱ እና አምልኮን ስለ ማደስ የሚናገር ብቻ ይመስላል። ነገር ግን ከዚህ ሁሉ በስተጀርባ ጥልቅ የሆነ መልእክት አለ ይህም እግዚአብሔር መንግሥቱን እያስቀጠለ መሆኑ የሚያሳይ እውነት ነው። ይህም የዕዝራ መጽሐፍ የሚያሳየን እውነት የእግዚአብሔር መንግሥት በሰው ኃይል ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሔር የተስፋ ቃል፣ በእግዚአብሔር ሕልውና እና በእግዚአብሔር ቃል እንደሚገነባ ነው።

1. የመንግሥቱ መታደስ የሚጀምረው በእግዚአብሔር አነሳሽነት ነው

በዕዝራ 1:1-4 ላይ፣ የእግዚአብሔር ሕዝብ ተመልሰው የእግዚአብሔርን ቤት እንዲሠሩ እግዚአብሔር የፋርስን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ እንዳነሳሳ እናነባለን። ይህ ተራ የፖለቲካ ጉዳይ አልነበረም፤ መለኮታዊ ዓላማ ነበረው። እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር የገባውን ኪዳን አልረሳም፤ በምርኮ ዘመንም እንኳ መንግሥቱ ወደ ፊት እየገሰገሰች ነበር።ምክንያቱም የእግዚአብሔር መንግሥት መታደስ የሚጀምረው ሁልጊዜ በእግዚአብሔር እንጂ በሰው አይደለምና። ሕዝቡ አቅም ባጣ ጊዜ እግዚአብሔር በር ከፈተ። በተበተኑ ጊዜ እግዚአብሔር ሰበሰባቸው። ተስፋ በቆረጡና በቆሙ ጊዜ፣ እግዚአብሔር ቃሉን ለመፈጸም በታሪክና በገዥዎች መካከል ተናገረ።

“የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዲህ ይላል፦ የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል፣ በይሁዳም ባለችው በኢየሩሳሌም ቤት እሠራለት ዘንድ አዝዞኛል።” (ዕዝራ 1:2) ይህ ቃል ማንኛውም ምድራዊ መንግሥት በሰማያዊው ንጉሥ ሥልጣን ሥር መሆኑን ያስታውሰናል። የእግዚአብሔር መንግሥት በመንግሥታትም ሆነ በስሮርዎ መንግስታት (በኢምፓየሮች)፣ወይም በሰው ውድቀት ሊገታ አይችልም።ምክንያቱም እግዚአብሔር መንግስቱን ለማድስ ሁሌም ተነሳሽቱ የእርሱ ብቻ ስለሆነ።

2. የእግዚአብሔር መንግሥት መታደስ አምልኮን ማዕከል ያደርጋል

ሕዝቡ ከምርኮ በተመለሱ ጊዜ፣ ቅድሚያ የሰጡት ለምቾታቸውና፣ ለድሎታቸው ወይም ለሀብታቸው አልነበረም።ነገር ግን ቅድሚያ የሰጡት ለአምልኮተ እግዚአብሔር ነበር። ስልሆነም በዕዝራ 3:10-13 ላይ እንደምንመለክተው የቤተ መቅደሱ መሠረት ተጣለ፣ ሕዝቡም እግዚአብሔርን አመሰገኑ።ምክንያቱም ቤተ መቅደሱ እግዚአብሔር በሕዝቡ መካከል የመኖሩ ምልክት ነበርና። ቤተ መቅደሱን እንደገና መሥራት ማለት በእግዚአብሔር አገዛዝ ሥር የሕይወትን ማዕከል ማደስ ማለት ነው።የእግዚአብሔር መንግሥት ሁልጊዜ አምልኮን ስለ ማደስ ነውና። እግዚአብሔር ሕዝቡ በሕይወት እንዲኖሩ ብቻ ሳይሆን፣ እርሱን በትክክለኛው መንገድ እንዲያመልኩት ይፈልጋል። እውነተኛው የእግዚአብሔር መንግሥት የሚለካው በግዛት ስፋት ብቻ ሳይሆን፣ የንጉሡ ሕልውና እና ክብር በሕዝቡ መካከል በመኖሩ ነው።

“አናፂዎቹም የእግዚአብሔርን መቅደስ መሠረት በጣሉ ጊዜ፣ አልባሰተ ተክህኖ የለበሱት ካህናት መለከት ይዘው፣ ... እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ዘንድ ቆሙ።” (ዕዝራ 3:10-11) ነገር ግን በዚሁ ጊዜ ሕዝቡ ያለቅሱም ነበር። አንዳንዶቹ የቀድሞውን ቤተ መቅደስ አይተው ስለነበር፣ ይህ አዲሱ ጅማሬ አነስተኛ መስሎ ስለታያቸው ያለቅሱ ነበር። ይህ የሚያስተምረን እግዚአብሔር ብዙ ጊዜ ሥራው በሰው ዓይን ሲታይ በትናንሽ ነገሮች እንደሚጀምር ነው። መንግሥቱ መጀመሪያ ላይ ደካማ ሊመስል ይችላል፣ ነገር ግን እግዚአብሔር አሁንም በሥራ ላይ ነው።

3. የመንግሥቱ መታደስ በእግዚአብሔር ቃል አማካኝነት ይቀጥላል

ዕዝራ ራሱ ለመንግሥቱ ሕይወት ማሳያ ወይም ሞዴል ሆኗል። ዕዝራ 7:10 በመጽሐፉ ውስጥ ካሉት ዋና ጥቅሶች አንዱ ነው፦“ዕዝራም የእግዚአብሔርን ሕግ ይፈልግና ያደርግ ዘንድ፣ ለእስራኤልም ሥርዓትንና ፍርድን ያስተምር ዘንድ ልቡን አዘጋጅቶ ነበርና።” (ዕዝራ 7:10)
ይህ ጥቅስ የመንግሥቱን አገልግሎት ሥርዓት ያሳየናል የመንግስቱ አገልግሎት፦
1. ቃሉን ማጥናት ይጠቃል (መፈለግ)።
2. ቃሉን ማድረግ ይጠይቃል (መታዘዝ)።
3. ቃሉን ብቻ ማስተማር ግድ ይላል።(ተልኮን መወጣት)

ምክንያቱም የእግዚአብሔር መንግሥት የሚቀጥለው የእግዚአብሔር ሕዝብ በቅዱሳት መጻሕፍት ሲቀረጹ ነውና።ዕዝራ ምሁር ብቻ አልነበረም፤ ልቡ ለእግዚአብሔር ቃል የተሰጠ ሰው እንጂ። ዕዝራ እውቀትን ከተግባር አልለየውም። ራሱ ለመኖር ፈቃደኛ ያልሆነውን ነገር ለሌሎች አላስተማረም።የእግዚአብሔር መንግሥት በቤተሰባችን፣ በቤተ ክርስቲያናችን እና በማኅበረሰባችን ውስጥ እንዲያድግ ከፈለግን ወደ እግዚአብሔር ቃል መመለስ አለብን። መንግሥቱ የሚታደሰው ቃሉ በሚከበርበት፣ቃሉን መታዘዝ ባለበትና ቃሉ በታማኝነት በሚሰበክበት ስፍራ ነው።ቃሉ ስፍራውን ይያዝ።

4. መንግሥቱ በትሕትና በእግዚአብሔር ላይ መደገፍን ይጠይቃል

በዕዝራ 9:8-9 ላይ፣ ዕዝራ ለቀሩት ወገኖች ጸጋውን ስላሳየ እግዚአብሔርን በጸሎት እንዲህ ያመሰግናል። መመለሳቸው በራሳቸው ብቃት ሳይሆን በእግዚአብሔር ምሕረት መሆኑን ይገነዘባል። (ዕዝራ 9:8-9) ይህ ለመንግሥቱ ሕይወት ዋናው ልብ ነው እርሱም በጸጋው ወይም በቸርነቱ ላይ መደገፍ። የእግዚአብሔር መንግሥት በሰው ጥረት የሚገኝም ሆነ የሚታዳስ አይደለም። በእግዚአብሔር ምሕረት የሚቀበሉት እና በጸጋው የሚጸና ነው እንጂ። ዕዝራ በሕዝቡ መሻሻል ላይ አልተመካም፤ ይልቁንም በትሕትና በእግዚአብሔር ፊት ተንበረከከ።ብዙ ጊዜ እኛ የመንግሥቱን ውጤት እንፈልጋለን ነገር ግን የመንግሥቱን ትሕትና አንፈልግም። እግዚአብሔር ግን በቃሉ ፊት የሚንቀጠቀጡትን እና በምሕረቱ ላይ የሚደገፉትን ያድሳል፣ ይቅር ይላል፣ ያድሳልም።

ከዚህ አንጻር የዕዝራ መጽሐፍ ሦስት ጥያቄዎችን እንድንጠይቅ ይጠራናል፦
1. እግዚአብሔር ሕይወቴን እየገዛ ነው?
መንግሥቱ የሚጀምረው እግዚአብሔር በልባችን ውስጥ የመጀመሪያውን ስፍራ ሲይዝ ነውና።
2. አምልኮ በሕይወቴ ውስጥ ማዕከላዊ ስፍራ አለው?
እንደተመለሱት ምርኮኞች፣ እኛም ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅርና አምልኮ እንደገና መገንባት አለብንና።
3. የእግዚአብሔር ቃል እየቀረጸኝ ነው?
እንደ ዕዝራ ልናጠናው፣ ልንታዘዘውና ልናስተምረው ይገባልና። የእግዚአብሔር መንግሥት የወደፊት ተስፋ ብቻ አይደለም። የእግዚአብሔር ሕዝብ ለእርሱ አገዛዝ በተሰጡበት፣ በቅንነት ባመለኩበትና በቃሉ ሥር ስልጣን በሚኖሩበት ስፍራ ሁሉ አሁን ያለ እውነታ ነው።

ማጠቃለያ

ዕዝራ እግዚአብሔር የመንግሥቱን ዕቅድ መቼም እንዳልተወ ያስተምረናል። ከምርኮ በኋላ እንኳ ሕዝቡን ይሰበስብ፣ አምልኮን ያድስ እና የተለያዩ ሰወችን ልቦች ለታላቅ ነገር ያዘጋጅ ነበር። ቤተ መቅደሱ ተሠራ፣ ቃሉ ተሰበከ፣ ሕዝቡም ወደ ኪዳኑ ታማኝነት ተጠሩ። ነገር ግን ጥልቁ መልእክት ይህ ነው የእግዚአብሔር መንግሥት ፍጻሜውን የሚያገኘው እግዚአብሔር ራሱ በሕዝቡ መካከል በሚያደርገው ሕልውና ወይም መገኘት ነው።ስለዚህ ዕዝራ ኃጢአት ያበላሸውን ሊያድስ ወደሚመጣው ታላቅ ንጉሥ ይጠቁመናል። በእርሱ ውስጥ የእግዚአብሔር መንግሥት መታወጅ ብቻ ሳይሆን ተገልጧል፣ ተቀባይነት አግኝቷል፣ ወደ ፊትም እየገሰገሰ ነው። “የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር የምድርን መንግሥታት ሁሉ ሰጥቶኛል።” (ዕዝራ 1:2) እግዚአብሔር አሁንም ይነግሣል። መንግሥቱ አሁንም ወደ ፊት ይገሰግሳል። ቃሉም አሁንም ሕዝቡን ወደ ቤት ይጠራል።ስለዚህ በቃሉ እና በእግዚአብሔር ሕልውና መታደስ ይሁንልን።

Source: https://cmaeec.com/w...

the cross
Jesus is Lord
John 3:16

Whoever believes in him shall not perish but have eternal life.