የእግዚአብሔር መንግሥት- በመዝሙረ ዳዊት መጸሐፍ
መንግስቱ እና የሕይወታችን መሠረት
መሪ ጥቅስ፦ “መንግሥትህ የዘላለም መንግሥት ናት፥ ግዛትህም ለልጅ ልጅ ነው።” (መዝሙር 145:13)
መግቢያ
ዛሬ በዓለማችን ላይ ብዙ መንግሥታት ሲነሱና ሲወድቁ፣ የሰው ኃይልና ሥልጣን ሲሻር እንመለከታለን። ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አንድ በፍጹም ስለማይናወጥ፣ ማብቂያና ወሰን ስለሌለው መንግሥት በዚህ በመዝሙረ ዳዊት መጸሐፍ ውስጥ ይነግረናል። እርሱም የእግዚአብሔር መንግሥት ነው። በመዝሙረ ዳዊት መጽሐፍ ውስጥ ንጉሡ ዳዊት በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ስለዚህ ድንቅ መንግሥት እና ስለ ንጉሡ ባህርይ ያስተማረንን አራት ዋና ዋና እውነቶች ዛሬ አብረን እንመለከታለን።
1. የእግዚአብሔር መንግሥት ዘላለም እና ሁለንተናዊ ነው
ይህ ማለት የእግዚአብሔር ንግሥና በምድራዊ ወሰን፣ በዘመን ወይም በሰው ልጅ ድካም የተገደበ አይደለም ማለት ነው። እርሱ በሰማይም በምድርም ላይ ያለ ማንምና ምንም ተወዳዳሪ ሁሉን የሚገዛ የፍጥረት ሁሉ ንጉሥ ነው ማለት ነው።
• ቃሉ እንዲህ ይላል፦ “መንግሥትህ የዘላለም መንግሥት ናት፥ ግዛትህም ለልጅ ልጅ ነው።” (መዝሙር 145:13)
• ከሕይወታችን ጋር ስናዛምደው፦ ምድራዊ ነገሮችና ሥልጣኖች ያልፋሉ፤ የሰው ተስፋም ሊቆረጥ ይችላል። የእግዚአብሔር መንግሥት ግን አይናወጥም።ስለዚህ ተስፋችንን በዘላለም ንጉሥ ላይ ስናደርግ ሕይወታችን በጽኑ መሠረት ላይ ይቆማል ማለት ነው።
2. እግዚአብሔር በጽድቅ እና በፍርድ ይገዛል
የእግዚአብሔር መንግሥት መሠረቱ ኃይል ወይም ጭቆና ሳይሆን እውነተኛ ፍርድ፣ ጽድቅ እና ቅድስና ነው።የእግዚአብሔር አገዛዝ በዚህ መሰርት ላይ የተገነባ በመሆኑ አድልኦ የሌለበትና በግፍ ሁሉ ላይ የሚፈርድ አምላክ እንዲሆን ያደርገዋል ማለት ነው።
• ቃሉ እንዲህ ይላል፦ “የዙፋንህ መሠረት ጽድቅና ፍርድ ነው፤ ምሕረትና እውነት በፊትህ ይሄዳሉ።” (መዝሙር 89:14)
• ከሕይወታችን ጋር ስናዛምደው፦ በዓለም ውስጥ ፍትሕ ቢጓደልም፣ የዚህ መንግሥት ዜጎች የሆነው እኛ ንጉሣችን ጻድቅ መሆኑንና በጽድቅ እንደሚፈርድ ማወቅ አለብን።ስለዚህም እኛም በሕይወታችን የእርሱን ጽድቅና እውነት ልንለማመድና አገዛዙን ልናንጸባርቅ ይገባል።
3. እግዚአብሔር ንጉሡ ለሚገዙለት ጠባቂ እና እረኛ ነው
እግዚአብሔር ከህዝቡ ተለይቶ በዙፋኑ ላይ የተቀመጠ ሩቅና ግዴለሽ ገዥ አይደለም። ይልቁንም ወደ መንግሥቱ ለሚመጡት እና ለሚታመኑበት ሁሉ ቅርብ የሆነ፣ የሚያስፈልጋቸውን የሚያሟላ እና የሚጠበቅ አባትና እረኛ ነው።
• ቃሉ እንዲህ ይላል፦ “እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፥ የሚያሳጣኝም የለም።” (መዝሙር 23:1)
• ከሕይወታችን ጋር ስናዛምደው፦ የዚህ መንግሥት ተገዢ በመሆናችን ብቻ ፍርሃታችን ይወገዳል።ምክንያቱም ንጉሣችን ስለእኛ ያስበልናል፣በእረፍት ውሀ ዘንድ ይመራናል፣ በሞት ጥላ ሸለቆ ውስጥ ስናልፍ እርሱ ከእኛ ጋር ይሆናል።ስለዚህ በንጉሱና በአገዛዙ ልናምን ይገባል።
4. የመንግሥቱ መገለጫ የሆነው የመሲሑ (የክርስቶስ) ንግሥና
መዝሙረ ዳዊት ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ሲናገር ወደፊት ስለሚመጣው ንጉሥ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በትንቢት ያመላክታል። እርሱ አሕዛብን ሁሉ በጽድቅ የሚገዛና ጠላቶቹን ሁሉ የሚያሸንፍ ዘላለማዊ ንጉሥ ነው።
• ቃሉ እንዲህ ይላል፦ “እግዚአብሔር ጌታዬን፦ ጠላቶችህን ለእግርህ መቀመጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው።” (መዝሙር 110:1)
• ከሕይወታችን ጋር ስናዛምደው፦ የእግዚአብሔር መንግሥት ሙሉ በሙሉ የተገለጠው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱን በሕይወታችን ንጉሥ አድርገን ስንቀበል የዚህ አሸናፊና ዘላለማዊ መንግሥት ባለመብት ዜጎች እንሆናለን።
ማጠቃለያ
ከዚህ እውነት አንጻር እስኪ ዛሬ ልባችንን እንመርምር በሕይወታችን ላይ የነግሠው ማን ነው?
ምድራዊ ነገሮችና ተግዳሮቶች ሊያናውጡን ሲሞክር፣ ዘላለማዊ፣ ጻድቅ፣ እረኛ እና አሸናፊ የሆነ ንጉሥ እንዳለን እናስብለን?ዛሬ ራሳችንን ለዚህ ንጉሥ እንስጥ፤ በንግሥናው ሥር እንጠለል፤ የጽድቁና የመንግሥቱ ወንጌል ተካፋዮች እንሁን።መንግስቱ የህይወታችን መሰረት ነውና።
Source: https://cmaeec.com/w...
John 3:16
Whoever believes in him shall not perish but have eternal life.