የእግዚአብሔር መንግሥት በትንቢተ ኢሳይያስ
ክፍል አንድ፦የተስፋው ሕፃንና የእግዚአብሔር መንግሥት
ዋና የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል፦ ኢሳይያስ 9፥6–7
ዋና ሐሳብ፦ በኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት የእግዚአብሔር መንግሥት ተገልጧል፤ እርሱም የዚህ መንግሥት ንጉሥ ነው። መንግሥቱ በአሁኑ ጊዜ በሕዝቡ ሕይወት ውስጥ እየተገለጠ ሲሆን፣ በዳግም ምጽአቱ ሙሉ በሙሉ ይፈጸማል።
ዋና ዋና ነጥቦች፦
1. ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር መንግሥት ተስፋና መገለጫ ነው።
2. ኢየሱስ የእግዚአብሔር መንግሥት ጻድቅና ዘላለማዊ ንጉሥ ነው።
3. የእግዚአብሔር መንግሥት የሰላምና የጽድቅ ዘላለማዊ መንግሥት ነው።
መግቢያ፦
ወዳጆች በጌታ፣ ዛሬ ከምንመለከተው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል አንዱ ኢሳይያስ 9፥6–7 ነው። ይህ ክፍል ስለሚወለድ ሕፃን ብቻ አይናገርም፤ ስለሚመጣው ንጉሥ፣ ስለሚመሠረተው መንግሥትና ስለማያቋርጠው ግዛት ይናገራል። በኢሳይያስ ዘመን የእስራኤል ሕዝብ በፖለቲካዊ ችግር፣ በጦርነት፣ በፍርሃትና በመንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር በነቢዩ አማካይነት የተስፋ መልእክት ሰጠ። የሚመጣው ተስፋ በሰው ኃይል፣ በጦር መሣሪያ ወይም በፖለቲካዊ ሥልጣን ላይ አይመሠረትም፤ እግዚአብሔር ለህዝቡ በሚሰጠው ንጉሥ ላይ ይመሠረታል። ይህ ተስፋ በኢየሱስ ክርስቶስ ተፈጽሟል። ኢየሱስ የመጣው ሰዎችን ከኃጢአት ለማዳን ብቻ ሳይሆን፣ የእግዚአብሔርን ንግሥና ለማሳየትና ሰዎችን ወደ መንግሥቱ ለመጥራትም ነው።ከዚህ እውነት አንጻር ስለዚህ ዛሬ ሦስት ዋና ዋና ነጥቦችን እንመለከታለን።
1. ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር መንግሥት ተስፋና መገለጫ ነው
ኢሳይያስ 9፥6፤ ሉቃስ 1፥31–33፤ ማቴዎስ 4፥17 ኢሳይያስ 9፥6 እንዲህ ይላል፦ «ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናል፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል።» ይህ ትንቢት ስለሚመጣው መሲሕ እና ስለ ንጉሣዊ ሥልጣኑ ይናገራል። ሕፃኑ የሚወለደው ተራ የሰው ልጅ ሆኖ ብቻ አይደለም፤ የእግዚአብሔር የመንግሥት ንጉሥ ሆኖ ነው እንጂ።ስለዚህ እውነት በአዲስ ኪዳን መልአኩ ለማርያም የነገረውን ስንመልከት። ሉቃስ 1፥32–33 ኢየሱስ የዳዊትን ዙፋን እንደሚወርስና መንግሥቱም ፍጻሜ እንደማይኖረው ይናገራል። ኢየሱስ ራሱም በማቴዎስ 4፥17፦ «ንስሐ ግቡ፤ የመንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና» ብሎ ሰበከ።
ይህ ምን ያሳየናል? የእግዚአብሔር መንግሥት በኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ መምጣት ወደ ሰወች ታሪክ ገብቷል። መንግሥቱ የሚገለጠው በሰው ሥልጣን ወይም በዓለማዊ ኃይል ሳይሆን፣ በንጉሡ በኢየሱስ አገልግሎት፣ በሞቱና በትንሣኤው ነው። ኢየሱስ በመስቀል ላይ ሲሞት የመንግሥቱን ሕዝብ ከኃጢአት ባርነት ለማዳን የመዋጀት ሥራውን ፈጸመ። በትንሣኤውም ሞትን ድል አደረገ።ስለዚህ የእግዚአብሔር መንግሥት የሚጀምረው ከክርስቶስ ጋር ባለን ግንኙነት ነው። እርሱን እንደ ጌታና አዳኝ ስንቀበል፣ በእርሱ ሥልጣን ሥር እንገባለን።ስለዚህ ዛሬ ጌታን በተመለከተ፣ የእኛ ዋና ጥያቄ ይህ ነው ኢየሱስ በሕይወታችን ውስጥ ተራ እንግዳ ነውን? ወይስ የሕይወታችን ንጉሥ ነው?
2. ኢየሱስ የእግዚአብሔር መንግሥት ጻድቅና ዘላለማዊ ንጉሥ ነው
ኢሳይያስ 9፥6–7፤ 11፥1–5፤ ዮሐንስ 18፥36–37 ኢሳይያስ 9፥6 ስለሚመጣው ንጉሥ አራት አስደናቂ ስሞችን ይጠቅሳል፦
• ድንቅ መካር፦ የእርሱ ጥበብ ፍጹም ነው። ሕዝቡን በእውነትና በጥበብ ይመራል።
• ኃያል አምላክ፦ እርሱ ከሰው ኃይል በላይ የሆነ መለኮታዊ ሥልጣን አለው።
• የዘላለም አባት፦ የሕዝቡን ደኅንነት የሚጠብቅና በዘላለም የሚነግሥ ንጉሥ መሆኑን ያሳያል።
• የሰላም አለቃ፦ እውነተኛ ሰላምን የሚያመጣ ንጉሥ ነው።
እነዚህ ስሞች የንጉሡን ባሕርይና የመንግሥቱን ባለሥልጣንነት ያሳያሉ።የዓለም መንግሥታት በሰው ኃይል፣ በጦር መሣሪያና በፖለቲካዊ ሥልጣን ሊጸኑ ይሞክራሉ። ነገር ግን የክርስቶስ መንግሥት በጽድቅ፣ በእውነትና በፍትሕ ላይ የተመሠረተ ነው። ኢሳይያስ 11፥3–5 ይህን በግልጽ ያሳያል። ይህ ንጉሥ በትክክል ይፈርዳል፤ ድሆችን በጽድቅ ይፈርዳል፤ እውነትና ጽድቅ የንግሥናው መሠረት ይሆናሉ። ይህ ለእኛ በጣም አስፈላጊ ነው። ክርስቶስን ንጉሣችን እንላለን፤ ነገር ግን በሕይወታችን ውስጥ የእርሱን ንግሥና እየተቀበልን ነው? የእግዚአብሔር መንግሥት በቃላችን ብቻ አይታይም። በጽድቅ፣ በፍቅር፣ በይቅርታ፣ በቅድስናና በመታዘዝ ይገለጣል። በቤተሰባችን፣ በቤተ ክርስቲያናችን፣ በሥራችንና በማኅበራዊ ግንኙነታችን ውስጥ የክርስቶስ ንግሥና መታየት አለበት።ወዳጆች በጌታ፣ የመንግሥቱ ሕዝብ መሆን ማለት የመንግሥቱን ንጉሥ ሥልጣን በሕይወታችን መቀበል ማለት ነውና።
3. የእግዚአብሔር መንግሥት የሰላምና የጽድቅ ዘላለማዊ መንግሥት ነው
ኢሳይያስ 9፥7፤ 11፥6–10፤ ራእይ 21፥1–5 ኢሳይያስ 9፥7 እንዲህ ይላል፦ «በመንግስቱ ላይ አለቅነቱ ይበዛል ለሰላሙም ፍጻሜ የለውም።» ይህ በመንግሥቱ ውስጥ የሚኖረውን ሰላምና ዘላለማዊነት ያሳያል። የዓለም መንግሥታት ይመጣሉ፤ ይሄዳሉም። የዓለም መሪዎች ይነግሣሉ፤ ዘመናቸውም ያበቃል። ነገር ግን የክርስቶስ መንግሥት ፍጻሜ የለውም። ኢሳይያስ 11፥6–9 በሚያስደንቅ ምሳሌ የመጪውን የመንግሥቱን ሰላም ይገልጻል። ተኩላና በግ አብረው ይኖራሉ፤ ጥፋትና ጉዳትም አይኖርም። ይህ የፍጥረት ሁሉ እድሳትና የእግዚአብሔር ፍጹም ሰላም መገለጫ ነው።
ነገር ግን አንድ አስፈላጊ እውነት መረዳት አለብን። የእግዚአብሔር መንግሥት በክርስቶስ አገልግሎት ጀምሯል፤ አሁንም በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በሕዝቡ መካከል እየተገለጠ ነው። ሆኖም ሙሉ ፍጻሜው ገና ወደፊት ነው። ለዚህም ነው ራእይ 21፥1–5 እግዚአብሔር አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደሚፈጥር፣ ሞት፣ ሐዘን፣ ጩኸትና ሕመም እንደማይኖሩ የሚናገረው። ይህ የክርስቶስ መንግሥት የመጨረሻ ድል ነው።
ስለዚህ እኛ እንደ መንግሥቱ ሕዝብ በተስፋ መኖር አለብን። ዛሬ መከራ ቢኖር፣ ሕይወታችን ፈተና ቢያጋጥመው፣ ዓለም በኃጢአትና በክፋት ቢሞላ፣ የእኛ ተስፋ በዚህ ዓለም ሁኔታ ላይ አይመሠረትም። በዘላለማዊው ንጉሣችን በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ይመሠረታል። ስለዚህ የመንግሥቱ ሕዝብ ዛሬ በተስፋ ይኖራል፤ ነገ የሚገለጠውንም የክርስቶስን ክብር ይጠብቃል።
ማጠቃለያ
ኢሳይያስ 9፥6–7 ስለ ሕፃን መወለድ ብቻ የሚናገር ትንቢት አይደለም። ስለ እግዚአብሔር መንግሥት፣ ስለ ንጉሡና ስለ ዘላለማዊው ንግሥናው የሚናገር ታላቅ ተስፋ ነው። ዛሬ ያየናቸውን ሦስት ነጥቦች እንደገና እናስታውስ፦
1. ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር መንግሥት ተስፋና መገለጫ ነው።
2. ኢየሱስ የእግዚአብሔር መንግሥት ጻድቅና ዘላለማዊ ንጉሥ ነው።
3. የእግዚአብሔር መንግሥት የሰላምና የጽድቅ ዘላለማዊ መንግሥት ነው።
ስለዚህ ዛሬ ለራሳችን ሦስት ጥያቄዎች እንጠይቅ፦
• ኢየሱስ በሕይወቴ ውስጥ እውነተኛ ንጉሥ ነውን?
• የእግዚአብሔር መንግሥት እሴቶች በሕይወቴና በቤተ ክርስቲያኔ ውስጥ ይታያሉን?
• ዘላለማዊውን የክርስቶስን መንግሥት በተስፋ እየጠበቅሁ እኖራለሁን?
የምንሰብከው ወንጌል ስለ ሰው ስኬት ብቻ አይደለም?። ስለ ክርስቶስ ንግሥናና ስለ እግዚአብሔር መንግሥት ነው። ቤተ ክርስቲያንም የራሷን መንግሥት ለመገንባት ሳይሆን የንጉሡን መንግሥት ለማወጅና ለመመስከር ተጠርታለች።
የመዝጊያ አዋጅ፦
ኢየሱስ ተወለደ፤ የመንግሥቱ ንጉሥ ሆኖ መጣ።
ኢየሱስ ሞተ፤ ሕዝቡን ከኃጢአት ለመዋጀት።
ኢየሱስ ተነሣ፤ ሞትን ድል ለማድረግ።
ኢየሱስ ይነግሣል፤ መንግሥቱም ፍጻሜ የለውም!
አሜን።
Source: https://cmaeec.com/w...
John 3:16
Whoever believes in him shall not perish but have eternal life.