Home » Sunday sermon – December 21, 2025

በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ መኖር

Last updated on December 21, 2025 - by Pastor Tariku Eshetu

ትምህርት አስራ ስምንት፦ የመንግሥቱ የመርዳት አስፈላጊነት

የንባብ ክፍል፡- ማቴ 13

መግቢያ

ስለ እግዚአብሔር መንግስት ጌታችን በስፋት ካስተማረባቸውና በጣም አስፈላጊ ከሆኑት ምዕራፎች አንዱ ማቴ 13 ነው። በዚህ ምዕራፍ ጌታችን ኢየሱስ ስለ አንድ ጭብጥ እውነት ደጋግሞ ተናግሯል። እርሱም ስለመንግሥተ ሰማያት ወይም ስለ እግዚአብሔር መንግስት ነው። ጌታችን አራት ምሳሌዎች ተጠቅሞአል። ምሳሌዎቹም ጥልቅ መንፈሳዊ እውነቶችን የተሸከሙ ቀላልና ከሰወች የዕለት ተዕለት ህይወት ጋር ግንኝነት የነበርቸው ነበሩ። ይህን ያደረገበትን ምክንያት እርሱ እራሱ ሲገልጽ ”ስለዚህ እያዩ ስለማያዩ እየሰሙ ስለማይሰሙ ስለማያስተውሉም በምሳሌ እነግራቸዋለሁ” ብሎአል። ማቴ 13:13 ምክንያቱም ሰወች ስለ እግዚአብሔር መንግስት ማወቅ ብቻ ሳይሆን ማስተዋል ስለሚያስፈልጋቸው። ዛሬም ሰወች የእግዚአብሔርን መንግሥት እውነት ማወቅ ብቻ ሳይሆን መረዳት አስፈላጊያቸው መሆኑን እንመለከታልን።

1. የዘሪው ምሳሌ - የሰውን የልብ ሁኔታ ያሳያል። ማቴ 13:1–23

ኢየሱስ የእግዚአብሔር መንግስት ከሰው ጋር ያለውን ግንኙነት በምሳሌ ማስርዳት የሚጀምረው በሚታወቅ ትዕይንት ነው። “ገበሬ ዘር ለመዝራት ወጣ”። “ዘሩ በአራት የተለያዩ የአፈር ዓይነቶች ላይ ወደቀ” በሚል በመጨርሻም ኢየሱስ ዘሩ የመንግስት ቃል አፈሩ ደግሞ የሰውን ልብ እንደሚወክል በግልጽ ተናግሮል።

የመጀመሪያ መንገድ ላይ የወደቀው ዘር ቃሉን ሰምቶ የማያስተውለውን ሰው ልብ ይወክላል። ጠላት ወዲያው መጥቶ ቃሉን ነጥቆታል። ይህ የደነደነ የሰው ልብ ነው ሲሆን የተዘጋ፣ የሚቋቋም እና ምላሽ የማይሰጥ ልብ ነው።

ሁለተኛ፣ በጭንጫ መሬት ላይ የወደቀው ዘር ቃሉን በደስታ የሚቀበለውን ሰው ይወክላል፣ ግን ለአጭር ጊዜ ነው። ችግር ወይም ስደት ሲመጣ በፍጥነት ይክዳል። ይህ ጥልቀት የሌለው የሰው ልብን ይወክላል - ስሜታዊ ግን ያልተሰበረ ልብ ነው።

ሦስተኛ፣ በእሾህ መካከል የሚወድቀው ዘር በዚህ ዓለም ሀሳብ/በህይወት ጭንቀት እና በባለጠግነት መታለል/በሀብት ማታለል የተዘናጋ ልብን ይወክላል። ቃሉን ማደግ ይጀምራል ነገር ግን ታንቆ ፍሬ አልባ ይሆናል። ይህ የተከፋፈለ ልብ ነው።
Ø በመጨረሻም፣ በመልካም መሬት ላይ የወደቀው ዘር ቃሉን ሰምቶ፣ ተረድቶ፣ ሠላሳ፣ ስልሳ እና መቶ እጥፍ ፍሬ የሚያፈራ ልብን ያመለክታል። ይህ ተቀባይ እና ታዛዥ ልብ ነው።

ለምን እንዲህ ሆነ? ችግሩ ዘሩ አይደለም። የእግዚአብሔር ቃል ሕያውና የሚሰራ ነው። ጉዳዩ የልብ ሁኔታ ነው።ስልዚህ እራሳችንን በቅንነት እንጠይቅ ዛሬ ልቤ ምን አይነት አፈር ነው?የመንግስቱ ቃል ሥር እንዲሰድ፣ እንዲያድግ እና በሕይወታችን ፍሬ እንዲያፈራ እየፈቀድን ነው?ምክንያቱም የእግዚአብሔር መንግሥት የሚጀምረው በሰው ልብ ውስጥ ነው።

2፡ የመንግስቱ ቃል ወደ ማስተዋል መድረስ

2:1 እውቀት/መረጃ - እውነታውን ማወቅ ነው።

📖 "ህዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሳ ጠፍቷል" ሆሴ 4:6 እውቀት ምንድነው?
• እውቀት መረጃ ነው።
• እኛ ያለን መረጃ/ እውቀት"እውነታው ምንድነው? ለሚለው ጥያቄው መልስ ይሰጣል።

የእውቀት ምሳሌዎች፡-
• እሳት የሚያቃጥል መሆኑን ማወቅ
• የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን ማወቅ
• ውሸት ሀጢያት መሆኑን ማወቅ
• እግዚአብሔር ኃጢአትን እንደሚያስተሰርይ/ይቅር እንደሚል ማወቅ

እውቀት/መረጃ አስፈላጊ ነው ምክንይቱም፦
• ያለ እውቀት መሀይም እንሆናልና ነገር ግን፦

እውቀት/መረጃ ብቻውን ለመንግስቱ ህይወት በቂ አይደለም። ብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ያውቃሉ ግን በመጽሐፍ ቅዱስ አይኖሩም።

2፡2 መረዳት(ማስተዋል) - ትርጉምን ማወቅ

📖 "ከሀብትህም ሁሉ ማስተዋልን አትርፍ"(“In all your getting, get understanding.”) ምሳ 4:7
• መረዳት/ማስተዋል አንድ ነገር ለምን እና እንዴት እንደሚሰራ ማወቅ ነው።
• ማስተዋል እውቀትን/መረጃን ከማግኘት በላይ ጥልቅ ነው።
• ማስተዋል/መረዳት"ለምንድን ነው ይህ የሆነው?"ለሚለው ጥያቄ መልስ ይሰጣል።

የመረዳት/የማስተዋል ምሳሌዎች፡-
• እሳት ለምን እንደሚያቃጠል መረዳት
• የቅዱሳት መጻሕፍትን ትርጉም መረዳት
• ውሸት ለምን መተማመንን እንደሚያጠፋ መረዳት
• ኢየሱስ ለምን በመስቀል ላይ መሞት እንዳስፈለገው መረዳት

ማስተዋል/መረዳት እውቀትን ከልብ ጋር ያገናኛል። የእግዚአብሔርን ዓላማ እና ሐሳብ እንድናይ ይረዳናል። ነገር ግን መረዳት /ማስተዋል የመጨረሻው ግብ አይደለም።

2፡3 ጥበብ - ከእውነት ጋር መኖር ነው።

📖 "የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው።" ምሳ 9:10
• ጥበብ እውቀትን እና ማስተዋልን/መረዳትን በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ የመጠቀም ችሎታ ነው።
• ጥበብ "ምን ላድርግ?"ለሚለው ጥያቄ መልስ ይሰጣል።

የጥበብ ምሳሌዎች፡-
• እሳትን ላለመንካት መምረጥ
• አስቸጋሪ ቢሆንም እንኳ የእግዚአብሔርን ቃል መታዘዝ
• መዋሸት ቀላል ቢሆንም እውነትን መናገር
• ሥጋ በቀልን ሲፈልግ ይቅርታ ማድረግ ወይም ይቅርታ መጠየቅ

"ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ ሰሚዎች ብቻ አትሁኑ" ያዕ 1:22 ጥበብ መረጋገጥ የሚችለው በተግባር ነው ።

2፡4 የእውቀት፣ የማስተዋልና የጥበብ መጸሐፍ ቅዱሳዊ ምሳሌ

ማቴ 7፡24-27 ኢየሱስ ስለ ሁለት ሰዎች ተናግሯል። ሁለቱም ቃሉን ሰምተዋል (ዕውቀት) ሁለቱም የተናገረውን ተረድተዋል(ማስተዋል)። ግን አንዱ ብቻ ታዘዘ (ጥበብ) አንዱ በዓለት ላይ በተሠራ አንዱ በአሸዋ ላይ በተሰራ ተመሰሉ። ልዩነቱ እውቀት አልነበረም - ልዩነቱ መታዘዝ ነበር።

ማጠቃለያ

እኛ የት ላይ ነን? ብዙ አማኞች በእውቀት ላይ ይቆማሉ። አንዳንዶች ግንዛቤ/ማስተዋል ላይ ይደርሳሉ፣ እግዚአብሔር ግን ወደ ጥበብ ይጠራናል ። "ከእናንተ ማንም ጥበብ ቢጎድለው እግዚአብሔርን ይለምን" እርሱም ይሰጠዋል። ያዕ 1:5 እራሳችንን እንጠይቅ የእግዚአብሔርን ቃል የምንሰማ ብቻ ነን? የምናውቀውንና የተረዳነውን ቃል እየኖርን ነው? ሕይወታችንን በጥበብ እያሳየ ነው? እውቀት አእምሮን ያስታውቃል።

Source: https://cmaeec.com/w...

the cross
Jesus is Lord
John 3:16

Whoever believes in him shall not perish but have eternal life.