Home » Sunday sermon – December 28, 2025

በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ መኖር

Last updated on December 28, 2025 - by Pastor Tariku Eshetu

ትምህርት አስራ ዘጠኝ፦ የስንዴው እና የእንክርዳዱ ምሳሌ - ትዕግስት የሚያስፈልገው መንግሥት

ማቴ 13:24–30, 36–43

ኢየሱስ ስንዴና እንክርዳድ ስለሚዘራበት እርሻ ሌላ ምሳሌ ተናገረ።”መንግስተ ሰማይ በእርሻው መልካም ዘርን የዘራ ሰው ትመስላለች። ጠላት በሌሊት መጥቶ በስንዴው መካከል እንክርዳድን ዘራ። ስንዴው በበቀለና በአፈራ ጊዜ እንክርዳዱ ታየ። አገልጋዮቹም የእርሻውን ባለቤት ሁልት ጥያቄ ጠየቁት እንክርዳዱ ከየት እንደመጣና፣ እንድንነቅለው ትፈልጋለህ የሚል ነው። ባለቤቱም አይሆንም በማለት ከለከላቸው ፤ ምክንያቱም እንክርዳዱን ስትነቅሉ ስንዴውን ልትነቅሉ ስለምትችሉ በሚል አመክንዮ። እንክርዳዱ የሚነቀለብት የመከር ጊዜ ይመጣል አላቸው። የሚነቅሉትም መለአክት ናችው።”

የምሳሌው ትርጉም፦
መልካምን ዘር የዘራው የሰው ልጅ ነው።እርሻውም ዓለም ነው።መልካሙም ዘር የመንግስት ልጆች ናቸው።እንክርዳዱም የክፉው ልጆች ናቸው።የዘራውም ጠላት ዲያብሎስ ነው።መከሩም የዓለም መጨርሻ ነው።አጫጆቹም መላዓክት ናቸው።ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ!!!!!

የምሳሌው ቁልፍ ትምህርቶች፦

ሀ. መልካሙ እና ክፉ አሁን አብረው ያድጋሉ።

በዚህ ዘመን እውነተኛ አማኞች እና ሐሰተኛ አማኞች አብረው ይኖራሉ ይህም መኖሪያቸው፦ በዓለም ላይ፣ በአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት ውስጥ፣በአገልግሎት ውስጥ፣በክርስቲያን ማህበረሰብ ውስጥ ተቀላቅለው ሊኖሩ ይችላሉ። እነዚህ ሰወች በውጫዊ መልካቸው ሲታዩ አማኞች ሊመስሉ ይችላሉ (ስንዴ የሚመስሉ እንክርዳዶች ናቸው) ፣ነገር ግን ልባቸው ለክርስቶስ አልተገዛም። ቢሆንም እግዚአብሔር ለአንድ ሰሞን ወይም አሁን አብረው እንዲኖሩ ይፈቅዳል።

ለ. ጠላት በለሊት ይሠራል

ሰይጣን የእግዚአብሔርን መንግስት ሁል ጊዜ በግልጽ አያጠቃም ለሊትን በመጠቅም እንክርዳድ ይዘራል። ጠላት ወይም ክፉ የሚሰራበት ለሊት ደግሞ የሐሰት ትምህርት ይባላል። ክፉ በሐሰት ትምህርት አማካይነት ሐሰተኛ ደቀ መዛሙርትን በመንግስቱ መካከል ይተክላል እነርሱም እውነተኛ ክርስቲያን ይመስላሉ ስለዚህ በቀላሉ ለመለየት ያስቸግራሉ። ይህ ማታለያው በጣም ረቂቅ ነው ስንዴ ለብስለት እስኪ ደረስ እንክርዳድ ስንዴን ይመስላል። እንክርዳድን ለመለየት ፍሬ ማፍራት ያስፈልጋል። አልበለዚያ ይህን ጥቃት መመከት አይቻልም።

ሐ. እግዚአብሔር ታጋሽ ነው እንጂ - ግድየለሽ አይደለም።

ብዙ ጊዜ እግዚአብሔር ቶሎ እንዲፈርድ እንደምንፈልግ ሁሉ አገልጋዮቹም እንክርዳዱን ወዲያውኑ ለመንቀል ፈለጉ። እግዚአብሔር ግን ፍርዱን ያዘገየዋል ምክንያቱም፡-እውነተኛ አማኞችን እርሱ ይጠብቃልና፣ፍርዱ በሰወች ከተፈጸመ ስንዴው ሊጠፋ ወይም ሊነቀል ይችላልና። ሌላው እግዚአብሔር ለሰዎች የንስሐ ጊዜን ይሰጣልና ነው። (2ኛ ጴጥሮስ 3፡9)። ይህ የእግዚአብሔር ትዕግስት የደካማነቱ ማስረጃ አይደለም ነገር ግን ጥልቅ ምሕረቱ መገለጫ ነው።

መ. ስንዴና እንክርዳድ በመጨረሻ መለያየተቻው እርግጠኛ ነው።

እግዚአብሔር አሁን ቢታገስም ፍርዱ የማይቀር መሆኑ የተረጋገጠ ነው። በመከር ወቅት ማለትም በመጨረሻው ፍርድ ጊዜ ሰወች ሳይሆን መላእክት እውነተኛውን ከሐሰተኛው ይለያሉ። እግዚአብሔርም ልብን ሁሉ ያጋልጣል። እምነትን ማስመሰል ከእንግዲህ አይሰራም። ይህ ምሳሌ የአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን አባል መሆን ብቻውን ከክርስቶስ አካል ጋር አንድ መሆን ማለት እንዳልሆነ እና ደግሞም መንግስቱን ማየታችንን በሚያርጋግጥ ፍሬ ልዩነት መፍጠር እንድሚገባን ያሳስበናል።

ሠ. እውነተኛ እምነት የሚገለጠው በፍሬ ነው።

ስንዴ በመጨረሻ ስንዴን ያፈራል እንጂ እንክርዳድን አያፈራም። እንደዚሁም፣ እውነተኛ አማኞች እውነተኛ መንፈሳዊ ፍሬ ያፈራሉ ፣ይህም ንስሐ መግባት፣ መታዘዝ፣ ፍቅር፣ ጽናት፣ ቅድስና ነው። ፍሬ አያድነንም ነገር ግን እምነታችን እውነተኛ መሆኑን ያረጋግጣል።ስልዚህ እውነተኝነታችንን ለማረገጋጥ ማፍራት እንጂ ማስመሰል አይጠበቅብንም።

ማጠቃለያ

የስንዴ እና የእንክርዳዱ ምሳሌ እንደሚያስተምረን እውነተኛ አማኞች እና ሐሰተኛ አማኞች በዚህ ዓለም አብረው ይኖራሉ ነገር ግን እውነተኞቹ ፍሬን ሲያፈሩ ሐሰተኞቹ ይገለጣሉ። በመጨረሻው የፍርድ ጊዜ ደግሞ እግዚአብሔር ፍጹም ለዘለዓለም ይለያቸዋል። በዚያን ጊዜ ጻድቅን በአባታቸው መንግስት እንደ ጸሐይ ይበራሉ። እንክርዳድ ተለቅሞ በእሳት እንድሚጣል የመንግስቱ እንቅፋቶችና አመጽን የሚያድርጉ ሁሉ ወደ እቶን እሳት ይጣላሉ በዚያም ልቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይሆናል። የሚሰማ ጆሮ ያለው ይስማ!!!!!!!!

the cross
Jesus is Lord
John 3:16

Whoever believes in him shall not perish but have eternal life.