የእግዚአብሔር መንግስት በዘሌዋውያን
ዋና ጭብጥ፦ “የእግዚአብሔር መንግሥት ያኔና አሁን --- ከዘሌዋውያን ወደ ኢየሱስ”
ቁልፍ ምንባባት፦ ዘሌ26:11-12፣ዘሌ 19:2, 18፣ማር 1:15፣ማቴ 22፡37-40
መግቢያ
ብዙዎች እንደሚያስቡት የዘሌዋውያን መጸሐፍ ስለ ሌዋውያን ሕጎች ብቻ የሚናገር መጸሐፍ አይደልም። ነገር ግን እግዚአብሔር ንጉሥ በሚሆንበት ጊዜ ሕይወት ምን እንደሚመስል የሚያሳይ መጸሐፍም ጭምር ነው። ጌታች ኢየሱስ ዘሌዋውያንን ወደ ፍጽመት አምጥቶታል። ስለዚህ በዘሌዋውያን የተገለጠው የእግዚአብሔር መንግሥት በኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ መምጣት ውስጥ እንዴት ፍጻሜውን እንዳገኘ እና እንደተገለጠው በዚህ ትምህርት እንመለከታልን።
I. በዘሌዋውያን የእግዚአብሔር መንግሥት እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር የሚኖርበት ነው።
ዘሌዋውያን 26:11-12 " ማደሪያዬን በእናንተ መካከል አድርጋልሁ ነፍሴ አትጸየፋችሁም። በመካከላችሁም እሄዳለሁ፥ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ፥ እናንተም ሕዝብ ትሆናላችሁ። ”የእግዚአብሔር መንግሥት ማለት የእርሱ ሥልጣን የሚገለጥበት ብቻ አይደለም ነገር ግን የእግዚአብሔርን በህዝቡ መካክል መገኘት የሚመለክትም ነው። ስለዚህ የማደሪያው ድንኳን የሚያረጋግጥልን እግዚአብሔር በሕዝቡ መካከል ሆኖ እየገዛ መሆኑን መሆኑን ነው።
ጌታችን ኢየሱስ በማርቆስ 1:15 "የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለች" በማለት ጌትችን ኢየሱስ የእግዚአብሔር መንግሥት ወይም አገዛዝ በማደሪያው ድንኳን ውስጥ ተወስኖ እንደማይኖር እና እራሱ ንጉሱ ወደ ህዝብ መምጣቱን ተናግሯል።በዚህም የእግዚአብሔር መንግሥት በቦታ የተወስነች አልመሆንዋንና የእግዚአብሔር ከእኛ ጋር መሆንን የሚያረጋግጥ መሆኑን አሳይቶአል።
II. የእግዚአብሔር መንግሥት በቅድስና ምልክት ተደርጎበታል።
“እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ። ዘሌ 19፡2 ቅድስና ማለት በዘሌዋውያን መጸህፍ ውስጥ በተለየ መንገድ መኖር ማለት ነው። ምክንያቱ ደግሞ እግዚአብሔር የህዝቡ ንጉሥ መሆንና በመካከሉ ማደሩ ነው ። ሕጉ የህዝቡን የዕለት ተዕለት ኑሮ ቅርጽና መልክ የሚስጥ ነው። ለምሳሌ ህጉ የህዝብን ምግብ አመጋገብ፣ማህበርዊ ግንኙነቶችንና ፍትህ አስጣጥን ቀርጿል።
ጌታችን ኢየሱስ ማቴዎስ 5፡48 “እንግዲህ በሰማያት ያለው አባታችሁ ፍጹም እንደ ሆነ እናንተ ፍጹማን ሁኑ። ”ብሎአል ስለዚህ ኢየሱስ ቅድስናን ከውጫዊ ስርዓት ባህሪው ወደ ልብ ለውጥ ቀይሮታል። ይህም የሚያረጋግጥልን የመንግሥቱ ቅድስና የሚፈሰው ከተለወጠ ሕይወት ነው እንጂ ከሕግጋት ብቻ አለመሆኑን ነው። በጌታችን ትምህርት መሰርት ቅድስና ፍጽምና ሳይሆን በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ የህይወት ለውጥ መመሪያ ነው።
III. ፍቅር የመንግሥቱ ልብ ነው።
በዘሌዋውያን 19:18 እንደምንመለከትው "ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ"የሚለው የህግና የነቢያት ሁሉ ፍጻሜ የሆነው እውነት የእግዚአብሔር መንግሥት የተመሰረተበት ሕግ ፍቅር መሆኑን እነደሚያረጋግጥ ነው።እንዲሁም ፍትህ፣ ምህረት እና ርህራሄ የመንግስቱ እሴቶች መሆናቸውን ነው ።
ጌታችን ኢየሱስ ማቴዎስ 22፡39-40 "በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ላይ ሕጉ ሁሉ ነቢያትም ተሰቅለዋል። ”ብሎአል በማስተማሩ ጌታችን ኢየሱስ የዘሌዋውያኑን የእግዚአብሔር መንግስት መርህ የትምህርቱ ማዕከላዊ እውነት አድርጎ እንድወሰደው እንመለከታልን። ስለዚህ ፍቅር የመንግሥቱ ሕይወት መጠቃለያ ነው። የጌታችን ትምህርትም የሚያርጋግጥልን እውነት ፍቅርን ካልተማርክ በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ መኖር አትችልም የሚልውን መርህ ነው።
IV. መንግሥቱ የኀጢአት ሥርየትን ይፈልጋል
ዘሌ 17፡11 "የስጋ ሕይወት በደሙ ውስጥ ነውና ደሙ ከህይወቱ የተነሳ ያስተሰርያልና በመሰዊያው ላይ ለነፍሳችሁ ማስተሰረያ ይሆን ዘንድ ሰጠሁት ለነፍስ ማስተሰረያ የሚሆነው ደሙ ነው።” በዘሌዋውያን " መሥዋዕቶች ኃጢአተኛ ሰዎች ከቅዱስ ንጉሥ ጋር እንዲኖሩ አስችሏቸዋል።ምክንያቱም መንግሥቱ እንዲቀጥል ይቅርታ ማግኘትን ይጠይቃልና።
ኢየሱስ ማቴዎስ 26፡28 "ይህ ስለ ብዙዎች የኃጢአት ይቅርታ የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው። ”በማለት" ኢየሱስ የመጨረሻው የኀጢአት ስርየት የሚገኝበት መስዋዕት ሆኖአል። በዚህም ንጉሱ ኢየሱስ እኛን ወደ መንግስቱ ለማምጣት ህይወቱን ሰጥቷል። የቃሉ እውነት የሚያረጋግጠውም ወደ መንግሥቱ መግባት ነጻ ስጦታ ነው።ይሁን እንጂ መንግስቱን ለመመሥረት ግን ታላቅ ዋጋ መክፈሉን ነው። ያለንበት መንግስት የጸና አና የታመነ ነው።
V. በመንግሥቱ ውስጥ ህዝቡ የማን ነው?
ዘሌ 20፡26 "የእኔ እንድትሆኑ"በማለት እግዚአብሔር ለራሱ ሕዝብን ይለያል።ስለዚህ በዘሌዋውያን እስራኤል የእግዚአብሔር በመሆኑ ለእርሱ እንዲኖር ተጠይቆአል።ህጉና ስርዓቱ የተሰጡብትም ምክንያት ይኸው ነበር።
ኢየሱስ ማቴዎስ 5፡3 "በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና።" ብሎ ባስትማረው መሰረት ወደ መንግስቱ መግባት የሚመጣው በትህትና እና በእምነት እንጂ በውርስ አይደለም። ይህም መንግሥቱ ለንጉሡ ለሚገዙ ሁሉ ክፍት መሆኑን የሚያበስር ነው። ኢየሱስ ባቀርብው ግብዣ መሰረት መንግሥቱ ንጉሱ እንደሚያስፈልጋቸው ለሚያውቁ ሰዎች ሁሉ የተፈቅደ ነው።
ማጠቃለያ
ዘሌዋውያን የእግዚአብሔርን መንግሥት አወቃቀር ያሳየናል። ኢየሱስ ደግሞ የእግዚአብሔርን መንግሥት ልብ ያሳየናል። በዘሌዋውያንም ሆነ በኢየሱስ ትምህርት በሁለቱም ውስጥ እንደምንመልከተው በቅድስና፣ በፍቅር እና በጸጋ እግዚአብሔር ነግሷል። ስለዚህ ዛሬ ጥያቄው የሚሆነው ንጉሥህ እግዚአብሔር ብቻ ነው ወይስ በልብህ ሌላንጉስ አለ የሚል ነው?
Source: https://cmaeec.com/w...
John 3:16
Whoever believes in him shall not perish but have eternal life.