Home » Sunday sermon – February 15, 2026

በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ መኖር

Last updated on February 15, 2026 - by Pastor Tariku Eshetu

የእግዚአብሔር መንግሥት በዘኁልቁ መጽሐፍ

ዋናው ሀሳብ

እግዚአብሔር በተዋጁት ህዝቡ መካከል ነግሷልና፣ ወደ ተስፋ ቃሉ በሚያደርጉት ጉዞ እንደ ንጉስ እንዲያምኑት ህዝቡን ይጠራቸዋል።

መግቢያ

ብዙ ሰዎች ስለ ዘኍልቍ መጽሐፍ ሲሰሙ፣የነገድ ዝርዝሮችን፣ የሕዝብ ቆጠራን እና በምድረ በዳ ውስጥ መንከራተትን ያስባሉ። ነገር ግን የዘኊልቅ መጸሐፍ የመንግሥቱን ስርዓት የምንማርብት መጽሐፍ ነው። ስለዚህም አንድ ወሳኝ ጥያቄ ይመልሳል እግዚአብሔር ንጉሥ ሲሆንና ሕዝቡ በእሱ አገዛዝ ሥር ለመኖር ሲታገሉ ምን ይሆናል?የሚለውን።የዘኊልቅ መጸሐፍ ህዝቡ በአገዛዙ እንዲታመኑ `ልባቸውን በትዕግሥት እየቀረጸና ወደ ተስፋው ቃል ፍጻሜ እየመራ በተቤዣቸው ሕዝቦች መካከል የሚኖር ቅዱስ አምላክን ያሳየናል።

I. እግዚአብሔር በምድረ በዳ መንግሥቱን መስርቷል። ዘኊ 1–10

እግዚአብሔር እስራኤልን ከግብፅ ታድጓል። መቤዠትንም አስቀድሞ አድርጎአል። ስልዚህ አሁን እግዚአብሔር ህዝቡን ማደራጀት ጀምሯል። ይህንም ሲያደርግ እንደ ቀድሞ የባሪያዎች ቡድን አደረጃጀት ሳይሆን እንደ መንግሥት ማህበረሰብ አድርጃጀት ነው። ስልዚህ፦

ሀ. እግዚአብሔር በማዕከላዊነት ከህዝብ ጋር ይኖራል

የእስራኤል በማደሪያው ድንኳን ዙሪያ እንዲሰፍር ተድርጎአል።ስለዚ እግዚአብሔር የሁሉ ነገር ማዕከል ነው ዳር ላይ አይደለም፣ እግዚአብሔር ከህዝቡ ሩቅ አይደለም፣እግዚአብሔር መዕከላዊ ነው። የነገድ ሁሉ ፊት ወደ ሀልወቱ ውስጥ ይመለከታል። ይህ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት አንድ መሠረታዊ ነገር ያስተምረናል፡- የመንግሥቱ ትኩረት ወዴት እንደምንሄድ ብቻ ሳይሆን በምንሄድበት ጊዜ መሃል ላይ ያለው ማን ነው? የሚለው ነው። ምክንያቱም እግዚአብሔር ማዕከላዊ ካልሆነ እንደ መንግሥት ሰዎች እየኖርን አይደለም።ያለ እግዚአብሔር መዕከላዊነት የቱንም ያህል ሃይማኖተኛ ብንመስል ጥቅም የለውም።

ለ. እግዚአብሔር በሥርዓት እና በቅድስና ይገዛል።

እግዚአብሔር ስለ ንጽህና፣ ስለአምልኮ፣ ስለአመራር እና ስለመታዘዝ ግድ የሚሉ ህጎችን ይሰጣል።ይህንም የሚያደርገው ጨቋኝ ስለሆነ ሳይሆን ንጉሥ ስለሆነ ነው። ቅድስና ቅጣት አይደለም፣ ቅድስና በቅዱሱ ንጉሥ አጠገብ ለመኖር መዘጋጀት ነው።የዘኊልቅ መጸሐፍ ከምዕራፍ 1-10ከሚያስትምርን እውነትይህ አንዱ ነው።

II. የእግዚአብሔር ንግሥና በሕዝቦቹ ተቃውሞ ገጠመው ዘኍ 11-14

በዚህ የእግዚአብሔር አሰራር ውስጥ ህዝቡ በጣም በፍጥነት ማጉረምረም ይጀምራል። ይህም ስለምግብ፣ስለአመራር ወይም መሪነትና፣ ስለእግዚአብሔር እቅድ ያጉረመርማሉ። በዘኊልቅ ማጉረምረም ስሜታዊ ብቻ ሳይሆን መንግስቱን የመቃወም አመጽ ነው።

ሀ. ህዝቡ በፍጥነት ማጉረምረም ጀመሩ።

እያንዳንዱ ቅሬታ ወይም ማጉረምርም እንዲህ ይላል"እግዚአብሔር ሆይ፣ የአንተን አመራር አናምንም"፣በምድረ በዳ ህዝቡ በሙሴ ላይ ማመጻቸው ሙሴን እየተቃወሙ አይደለም።ነግር ግን የእግዚአብሔርን መንግሥት እየተቃወሙ ነበር።ለዚህ ነበር እግዚአብሔር እራሱ መልስ ይሰጣቸው የነበርው።ዘኊ 14:11-12፣ 26-30

ለ. በቃዴስ በርኔ ቀውስ ተከሰተ

አሥራ ሁለት ሰላዮች የተስፋይቱን ምድር ሊሰልሉ ተልከው የከነዓንን ምድር አዩ።የአስሩ ትኩረት በግዙፎቹ በኤናቃውያን ላይ ሲሆን ፣የሁለቱ ትኩረት ደግሞ በእግዚአብሔር ላይ ነበር አስሩ ሰላዮች አይናቸውን በኤንቃውያን ስላድረጉ ፍርሃት አሸነፈ እምነት ጠፋ። ስለዚህ ወደ ርስታችው ለመግባት ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ እግዚአብሔር ለሙሴ፡-"ይህ ሕዝብ እስከመቼ ይንቀኛል? በፊቱስ ባደርኩት ታምራት እስከ መቼ አያምንብኝም?"አለ። (ዘኁ14:11) ይህ ሁኔታ ጥንካራ የመንግሥቱን እውነት ያስተምራል። እግዚአብሔርን እንደ ንጉስ አለመቀበል የእግዚአብሔርን ልብ እንደሚስብር። እግዚአብሔር እስራኤልን ከባርነት ታድጓል፣ተአምራቱን አይቷቸዋል፣ በእግዚአብሔር መገኘት ተመላልሰዋል፣ነገር ግን እግዚአብሔርን እንደ ንጉሥ እንዲያምኑት እና በእምነት እንዲራመዱ ሲጠራቸው፣ አይሆንም አሉ።

ሐ. መንግሥቱና የማጉረምረም ውጤቶች

እግዚአብሔር ይቅር ይላል፣ እርሱን የማይታመን ትውልድ ግን ወደ ወደተስፋው ምድር አይገባም። ምክንያቱም ጸጋ ያለመታዘዝን መዘዝ አይሰርዝም። ፍቅርም ተግሣጽን አያስወግድምና ነው። ስለዚህ የሚበዙት በምድርበዳ ቀሩ ይለናል። እግዚአብሔርን እንደ ንጉስ አለመታዘዝ የእርሱን መንግስት መቃውም ነው። መንግስቱን የሚቃወም ሁሉ የሚወርስው ርስት አይኖርውም። ዘኊ 11-14 ይህን እውነት ያሰተምርናል

III. የእግዚአብሔር መንግሥት የሰው ልጅ ተቃውሞ ቢገጥመውም ይቀጥላል ዘኍልቍ 15-25

እስራኤል የእግዚአብሔርን አገዛዝ ቢቃወምም እግዚአብሔር ግን ዙፋኑን አልተወም።ስለዚህ እርሱ መመሪያ መስጠትን፣ አቅርቦትንና ጥበቃ ማድረግን ፣እንዲሁም መናግርን ቀጥሏል። በጣም ግልፅ ከሆኑት የመንግስት መገለጫዎች አንዱ በበለዓም በኩል የመጣው መልዕክት "እግዚአብሔር አምላካቸው ከእነርሱ ጋር ነው የንጉሥ እልልታ በመካከላቸው አለ” የሚለው ነው። (ዘኁ 23:21) ጠላት እግዚአብሔር የመረጠውን መርገም አይችልም። ምክንያቱም የማንም ሰው ውድቀት እግዚአብሔርን ከዙፋን አያወርድምና። የእግዚአብሔር መንግሥት ደካማ አይደለም።

IV. እግዚአብሔር ቀጣዩን ትውልድ ለመንግሥቱ ያዘጋጃል።ዘኍ 26–36

ከዚህ ሁሉ ሒደት በኋላ እንደገና አዲስ ቆጠራ ተካሄደ፣በዚህም አዲስ ትውልድ ተነሳ ምክንያቱም የቀደመው ትውልድ በምድረ በዳ ሞቷልና ነገር ግን ተስፋው ከእነርሱ ጋር አልሞትም። ስለዚህ እግዚአብሔር ኢያሱን አስነሳው። ሙሴ ለመተካካት ተዘጋጀ።በመንግስቱ ውስጥ አመራር ይለወጣል - ንጉሱ ግን በመንግስቱ ይኖራል። ይህም የእግዚአብሔር መንግሥት ከየትኛውም የመሪ፣ የትውልድ ወይም የታሪክ ቅጽበት ይበልጣል። የዘኁልቅ መጽሐፍ ይህን ያስታውሰናል፡-

V. የመንግሥቱ ትምህርቶች ከዘኍልቍ መጸሐፍ

እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ይኖራል እርሱ ከሕዝቡ ሩቅ አይደለም ይልቁንም በህዝቡ መካከል አለ። እግዚአብሔር የሚገዛው በቃሉ ነው። ቃሉን መታዘዝ ሕግ ጠባቂነት ሳይሆን ታማኝነት ነው። የእግዚአብሔር መንግሥት እምነትን ይፈልጋል ርስቱን ሊያወርሳቸው ቃል ተገብቶ ነበርና፣ በእምነት መግባት ነበረባችው። ዓመፀኞች ቢኖሩበትም የእግዚአብሔር መንግሥት እየገሰገሰ ነው። ምክንያቱም የሰው ውድቀት መለኮታዊ ዓላማን ፈጽሞ አይሽረውም።

VI. ኢየሱስ እና የመንግሥቱ ፍጻሜ

እስራኤል በምድረ በዳ በወደቀችበት፣ ኢየሱስ ተሳክቶለታል። እስራኤል አጉረመረመች ኢየሱስ ግን ታማኝ ሆኖአል ታዘዘ ። እስራኤል አመጸ ኢየሱስ ግን እስከ መስቀል ሞት ድረስ ታዘዘ። እስራኤላውያን ኤናቃውያንን ፈሩ ኢየሱስ ግን በመስቀል ለመሞት ታማኝ ነበር። ኢየሱስ “የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርቧል።” ብሎ እያወጀ መጣ በዚህም ወደ ከነዓን ሳይሆን የሚመራን ወደ ዘላለም ሕይወት ነው።

ማጠቃለያ

የዘኍልቍ መጸሐፍ ትውልድን ሁሉ ተመሳሳይ ጥያቄ ይጠይቃል፡- እግዚአብሔርን እንደ ንጉሥ ታምናለህ - ወይንስ እንደ አዳኝ ብቻ? እግዚአብሔር የሚፈልገው ከግብፅ ሊያወጣን ብቻ ሳይሆን ቃል በገባንበት መንገድ በህይወታችን ላይ ሊነግስ ይፈልጋል። እርሱ በመካከላችን አድሮልና በንጉሥ እልልታ የምንኖር ህዝቦች እንሁን።

Source: https://cmaeec.com/w...

the cross
Jesus is Lord
John 3:16

Whoever believes in him shall not perish but have eternal life.