Home » Sunday sermon – February 22, 2026

በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ መኖር

Last updated on February 22, 2026 - by Pastor Tariku Eshetu

የእግዚአብሒር መንግስት በዘዳግም መጸሐፍ

መግቢያ

የዘዳግም መጽሐፍ የሕግ መጽሐፍ ብቻ አይደለም። ነገር ግን እግዚአብሔር ንጉሥ እንደሆነ እና ሕዝቡ በእሱ አገዛዝ ሥር እንዲኖሩ መጠራታቸውን የሚያሳይ ኃይለኛ መግለጫ ወይም አዋጅ ነው። እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ከመግባታቸው በፊት እግዚአብሔር ለማን መገዛት እንዳልባቸውና በመንግሥቱ ውስጥ ያለው የሕይወት ስርዓት ምን መሆን እንዳለበት በዚህ መጸሐፍ አሳስቧቸዋል። ይህን እውነት በተመለከተ የሚከተሉትን እውነቶች በዚህ ትምህርት እንመለከታልን።

1. እግዚአብሔር የሕዝቡ ንጉሥ ነው።

የእስራኤል ህዝብ ወደ ተስፋይቱ ምድር ከመግባቱ በፊት መርሳት የሌለበት ነገር ቢኖር እግዚአብሔር የሁል ጊዜ የሁሉ ስፍራ ንጉስ መሆኑን ነው። በከነዓንም እነርሱ የህዝቡ ንጉስ ሆኖ መቀጠሉን ማስታወስ አስፈላጊ ነበር። ምክንያቱም በኢያሱ 12:24 እንደምንመልክተው 31 ነገስታትና በርካታ ጣዖታት በዚያ ነበሩና። ስለዚህ ዘዳግም እግዚአብሔርን ከሁሉ የላቀ እና ተወዳዳሪ የሌለው ንጉሥ መሆኑን ይገልጻል። እስራኤል ንጉሥ አድርጎ አልመረጠውም ምክንያቱም እርሱ አስቀድሞ ንጉሥ ነው። "አምላክህ እግዚአብሔር የአማልክት አምላክ የጌቶችም ጌታ ነው።" ዘዳ 10:17 ይህ ማለት እግዚአብሔር ሁሌም የትም ፍጹም ሥልጣን አለው ማለት ነው። እንዲሁም መንግስቱ በሰው ሃይል ላይ ሳይሆን በመለኮታዊ ሉዓላዊነቱ ላይ የተመሰረተ ነው።

2. ኪዳኑ የመንግሥቱ ህዝብ ከአምላኩ ጋር ያለውን ግንኙነት ያሳያል

በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ፣ በንጉሡና በሕዝቡ መካከል ያለው መቆራኘት የሚገለጸው በቃል ኪዳን ነው። እግዚአብሔር እስራኤልን የጠራው እንዲታዘዙለት ብቻ ሳይሆን እንዲወዱትም ጭምር ነው። ስለዚህ ይህ ጥሪ ለህዝቡ ቀርቦአል " እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ እግዚአብሔር አምላካችን አንድ እግዚአብሔር ነው። አምላክህን እግዚአብሔርን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህ በፍጹምም ኃይልህ ውደድ "ዘዳ6: 4-5 ። በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ መገዛት በግዳጅ ሳይሆን ከፍቅርና ከታማኝነት የሚመነጭ የህይወት ስርዓት ነው።

3. መታዘዝ በመንግሥቱ ውስጥ ሕይወት ነው።

በእግዚአብሔር አገዛዝ ስር መኖር በረከትን፣ ሰላምን እና ህይወትን ያመጣል። ታዛዥነት እግዚአብሔር በእውነት በህዝቡ ልብ ውስጥ እንደሚገዛ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። ስለዚህ ይህ ማሳሰቢያ ተሰጥቶአል "በመንገዱም ትሄድ ዘንድ የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ጠብቅ። ዘዳ 8:6 "በከተማ ቡሩክ ትሆናለህ በእርሻም ቡሩክ ትሆናለህ" ዘዳ 28:3 በአንጻሩ ደግሞ የእግዚአብሔርን አገዛዝ አለመቀበል መዘዝ ያስከትላል ተብሎም ተነግሮአል። የአምላካችሁን የእግዚአብሔርን ቃል ባትሰሙት... እነዚህ ሁሉ እርግማኖች በአንተ ላይ ይደርሳሉ። ዘዳ 28:15 መታዘዝ በመንግስቱ ውስጥ ሕይወት ነው።

4. መንግሥቱን የመምረጥ ጥሪ

እግዚአብሔር፣ እንደ ንጉሥ፣ ለሕዝቡ ግልጽ ምርጫን ይሰጣል ይህም ሕይወት ወይም ሞት፣ በረከት ወይም መርገም የሚል ነው። ህዝቡ ምርጫውን እንዲያስተካክል ጥሪ ቀርቦለታል። “በፊትህ ሕይወትንና ሞትን፣ በረከትንና መርገምን አኑሬአለሁ። አንተና ዘርህ በሕይወት እንድትኖሩ ሕይወትን ምረጥ።” ዘዳ 30:19 ሕይወትን መምረጥ ማለት የእግዚአብሔርን መንግሥት፣ አገዛዙንና መንገዶቹን መምረጥ ማለት ነው።

ማጠቃለያ

በዘዳግም ውስጥ፣ የእግዚአብሔር መንግሥት የተብራራው እግዚአብሔር እንደ ንጉሥ ሲገዛ፣ ሕዝቡን በቃል ኪዳኑ እየመራ፣ ለፍቅር፣ ለታዛዥነት እና ለታማኝነት ሲጠራቸው በማሳየት ነው። ሕይወት፣ በረከት እና ተስፋ የሚገኘው እግዚአብሔር በህዝብ ልብ ውስጥ ሲገዛ ነው። እኛም በሕይወታችን ውስጥ ለእግዚአብሔር መንግሥት በመገዛት ሕይወትን እንምረጥ። ኣሜን።

የዘዳግም መጸሐፍ ሙሴ የእስራኤልን የጉዞ ግምገማ በተመለከተ እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ በኋላ እግዚአብሔር ያደረገላቸውን ነገር ያስታወስበት መጸሐፍ ነው።ካለፉት ስኬቶች እና ውድቀቶች ህዝቡ እንዲማር እንደገና ይናገራል።ይህም ኪዳንን ስለማደስ፣ፍቅር እና ለእግዚአብሔር መታዘዝን በተመልክት ሕጉ ማብራራት፣በረከቶች እና ውጤቶቻውን ማስወቅ፣እንዲሁም ለተስፋይቱ ምድር መዘጋጀትንና የሙሴ የመጨረሻ ንግግሮች እና ሞት የያዘ መጸሐፍ ነው። በዚህ መጽሀፍ ውስጥ መንግስተ እግዚአብሔር እንዴት እንደተብራራ በዚህ ትምህርት እንመለከታልን።

Source: https://cmaeec.com/w...

the cross
Jesus is Lord
John 3:16

Whoever believes in him shall not perish but have eternal life.