Home » Sunday sermon – March 22, 2026

በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ መኖር

Last updated on March 22, 2026 - by Pastor Tariku Eshetu

ርዕስ፦ ከባዶነት ወደ ሙላት – የሚታደገው አምላክ (ሩት 1–4)

መግቢያ

የሩት መጽሐፍ ትንሽ ታሪክ ቢሆንም ትልቅ መልዕክት ያለው ነው። ይህ ታሪክ የሁለት መበለቶች፣ የአንዲት መጻተኛ፣ የአንድ ጻድቅ ሰው እና የማዳን እጁ የማይታይ የታዳጊው አምላክ ታሪክ ነው። በረሃብ፣ በሞት እና በጥልቅ ተስፋ መቁረጥ ውስጥ፣ እግዚአብሔር ዛሬም ድረስ ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እና ወደ እኛ ሕይወት የሚያመለክተውን የቤዛነት ታሪክ በዝግታ ይህ መጸሐፍ ይዘግባል። ከዚህ እውነት አንጻር በዛሬው መልዕክት እግዚአብሔር በባዶነታችን ውስጥ ይገናኘናል፤ በታማኝ ፍቅሩ፣ ዋጋ በሚያስከፍል ኃላፊነት እና በጸጋው አካታችነት ይቤዠናል የሚለውን የመንግስቱን እውነት እንመልከታለን። ለዚህም በሦስት ዋና ዋና ነጥቦች ላይ እናተኩራለን የባዶነት ሕመም የታማኝ ፍቅር መንገድ የቤዛነት ኃይል

I. የባዶነት ሕመም (ሩት 1)

የሩት መጽሐፍ የሚጀምረው በሐዘን ነው። ረሃብ አቢሜሌክንና ኑሀሚንን ከቤተልሔም ወደ ሞዓብ እንዲሰደዱ ያደርጋቸዋል። በዚያም ኑሀሚን ባሏንና ሁለቱን ልጆቿን ታጣለች። በዚህ ምክንያት “በሙላት ወጣሁ እግዚአብሔርም ወደ ቤቴ ባዶዬን መለሰኝ እግዚአብሔር አዋርዶኛልና ሁሉን የሚችል አምላክ አስጨንቆኛል” በማለት ወደ ቤቷ ትመለሳለች።

• ባዶነት ለእግዚአብሔር ሕዝቦችም ቢሆን እውነተኛ ስሜት ነው፦ ኑሀሚን አማኝ ናት፤ ነገር ግን ተመርራለች፣ ቆስላለች፣ ግራ ተጋብታለች። እግዚአብሔር በእሷ ላይ እንደተነሳባት ይሰማታል።
• ዛሬም በቤተክርስቲያን ብዙዎች እንደ ኖሀሚን ይሰማቸዋል፦ በሞት፣ በፈረሰ ግንኙነት፣ በገንዘብ ችግር፣ በመንፈሳዊ ድርቀት ወይም በውድቀት ምክንያት ባዶነት ይሰማቸዋል።
• ተጥለናል ብለን ስናስብ እንኳ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ነው፦ ኑሀሚን ሕይወቷን “እግዚአብሔር አሳዘነኝ” ብላ ብትተረጉመውም፣ እግዚአብሔር ግን በዚያው ወቅት ሥራውን እየሠራ ነበር፦ “እግዚአብሔር ሕዝቡን እንደጎበኘና ምግብ እንደሰጣቸው” ሰማች፤ ሩትም ከጎኗ ቆማለች።

ተግባራዊ ትምህርት፦
እንደ ኑሀሚን “ተመርሬአለሁ፣ ባዶነት ይሰማኛል” ብሎ ማመን መንፈሳዊ አለመሆን አይደለም። እግዚአብሔር የልጆቹን ቅን የሐዘን ድምፅ መስማት ይችላል። ባዶነት የታሪኩ ማብቂያ አይደለም። የወደፊት ተስፋ የለም ብለን በምናስብበት ጊዜ፣ እግዚአብሔር ለኛ የማይታየንን የቤዛነት ዘር እያበቀለ ሊሆን ይችላል።ስለዚህ እንመነው።

II. የታማኝ ፍቅር መንገድ (ሩት 1–2)

የሩት የቃል ኪዳን ፍቅር፦
በኑኀሚን መራራነት መካከል፣ ሩት በሚያስደንቅ የቃል ኪዳን ፍቅር ታበራለች ሞዓባዊቷ ሩት የኑሀሚንን አምላክና ሕዝብ ትመርጣለች “አንቺ ወደምትሄጂበት እሄዳለሁ... ሕዝብሽ ሕዝቤ፣ አምላክሽም አምላኬ ይሆናል።” ይህን በመናገሯ ሩት ራሷን ከኑኃሚን ጋር ብቻ ሳይሆን ከእስራኤል አምላክ ጋር አቆራኝታለች።

የሩት ትሕትና እና ታታሪነት፦
ድሆች በሚሠሩበት መስክ ቃርሚያ ለመቃረም ትወጣለች፤ ሩት 2:3 “ሄደችም፥ ከአጫጆች በኋላ በእርሻ ውስጥ ቃረመች እንደ አጋጣሚም ወደ የአቤሜሌክ ወገን ወደ ነበረው ወደ ቦዔዝ እርሻ ደርስች።” ምንባቡ "እንደ አጋጣሚ" ይላል። ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ነገረ መልኮት ውስጥ "አጋጣሚ" የሚባል ነገር የለም። ለእኛ በአጋጣሚ የሆነ የሚመስለው ነገር እውነቱ መለኮታዊ ጥበቃን የያዘ መሆኑ ነው ምክንያቱም እግዚአብሔር ክስተቶችን እንደ ፈቃዱ የሚያስተዳድር ስልሆነ ።

የእግዚአብሔር መንግሥት ብዙውን ጊዜ አይታይም እንጂ መቼም ቢሆን ሥራ አያቆምም ስለዚህ፦
በማይታወቁ የሕይወት ወቅቶቻችን ውስጥ፣ እግዚአብሔር አሁንም እየመራን ነው። በተለመደው የዕለት ተዕለት ተግባር ውስጥ፣ እግዚአብሔር አሁንም እየሠራ ነው በዝምታ ጊዜያት ውስጥ፣ እግዚአብሔር አሁንም አብሮን አለ።

የቦዔዝ ቸርነት፦
የእግዚአብሔር መንግስት ሥነ-ምግባር በተግባር ቦዔዝ ሕጉን ከመፈጸም ባለፈ ለሩት ጥበቃ ያደርጋል፣ በደግነት ያናግራታል፣ በልግስናም ያቀርብላታል።ቦኤዝ የሚያየው አንዲት ድሃ መጻተኛን ብቻ ሳይሆን፣ ክብር ያላትን ሴት ነው፤ በክብርም ያስተናግዳታል፣የእግዚአብሔር መንግሥት ፍቅርና ታማኝነት እንጂ አመቺ ሁኔታን ተከታይነት አይደለምና። ነገሮች መራራ ሲሆኑም ከቤተሰብ፣ ከቤተክርስቲያንና ከጓደኞች ጋር መቆምን ይጠይቃል።

III. የቤዛነት ኃይል (ሩት 3–4)

የታሪኩ ትልቅ ለውጥ “የቅርብ ዘመድ ተቤዢ” (Go’el) የሚለው ሐሳብ መከሰቱ ነው። ይህ ዘመድ መሬትን የመመለስ፣ ለሟቹ ስም የማስቀጠልና ቤተሰብን የመጠበቅ ኃላፊነት ያለበት ሰው ነው።በዚህ መሰረት ተቤዢው ቦዔዝ ሥልጣኑን ሌሎችን ለመበዝበዝ ሳይሆን ለመጠበቅ፣ ጥቅምን ለማሳደድ ሳይሆን የታሪክን ስም ለመመለስ ተጠቀመበት።የቤዛነቱ ፍሬ ከመራራነት ወደ በረከት፦ በአንድ ወቅት “ማራ (መራራ) በሉኝ” ያለችው ኑሀሚን፣ አሁን ሕፃኑን ኢዮቤድን በታቀፈች ጊዜ ባዶነቷ ወደ ሙላት ተለወጠ።

ከኢዮቤድ እስከ ክርስቶስ ያለው ትልቁ ታሪክ፦ ፦ መጽሐፉ የሚደመደመው በዘር ሐረግ ነው ይህም ኢዮቤድ፣ እሴይ፣ ዳዊት በሚል።በዚህ ታሪክ ውስጥ እንደምልመለከትው እግዚአብሔር የአንድን ቤተሰብ ታሪክ ብቻ ሳይሆን የመንግሥቱን ዕቅድ እያስቀጠለ ነበር። በሞዓባዊቷ ሩት በኩል እግዚአብሔር የታላቁን ንጉሥ የዳዊትን እና በመጨረሻም የዳዊት ልጅ የሆነውን የኢየሱስን የዘር ሐርግ መስመር እያዘጋጀ ነበር።

የወንጌል ተግባራዊ ትምህርት፦ ቦዔዝ የኢየሱስ ምሳሌ ነው። ቦዔዝ የቤተሰቡ ዘመድ ነበር፤ ኢየሱስም የእኛ “ዘመድ” (ቤዛ) ለመሆን ሰው ሆነ። ቦዔዝ ዋጋውን ለመክፈል ፈቃደኛ ነበር፤ ኢየሱስም የቤዛነታችንን ዋጋ በገዛ ደሙ ከፈለ። ቦዔዝ መጻተኛዋን ወደ እስራኤል የቃል ኪዳን ቤተሰብ አስገባት፤ ኢየሱስም ኃጢአተኞችንና ከየአሕዛቡ የሆኑትን ወደ እግዚአብሔር ቤተሰብ አመጣ።

ማጠቃለያ

የሩት መጽሐፍ በረሃብ፣ በሞትና በመራራነት ይጀምራል፤ ነገር ግን በሕፃን ልጅ፣ በታደሰ ቤተሰብና በንጉሣዊ የዘር ሐረግ ይጠናቀቃል። እግዚአብሔር እንዲህ ነው፤ ወደ ተሰበሩ ታሪኮች ውስጥ ገብቶ የቤዛነትን ታሪክ ይጽፋል። ስለዚህ ባዶነታችሁን ወደ ተቤዢው ጌታ አምጡ። እንደ ሩት ታማኝነታችሁንና ፍቅራችሁን ስጡ። እንደ ቦዔዝ ጥንካሬአችሁንና ሀብታችሁን ለበጎ ተጠቀሙበት። የኑሀሚን ዕንባ ወደ ደስታ፣ የሩትንም ውርደት ወደ ክብር የለወጠ አምላክ ዛሬም በዝግታና በታማኝነት በእናንተ ውስጥ መንግሥቱን እየገነባ እንደሆነ እመኑ።አሜን

Source: https://cmaeec.com/w...

the cross
Jesus is Lord
John 3:16

Whoever believes in him shall not perish but have eternal life.