Home » Sunday sermon – March 29, 2026

በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ መኖር

Last updated on March 29, 2026 - by Pastor Tariku Eshetu

የእግዚአብሔርን መንግሥት በ መጽሐፍ 1 ሳሙኤል ውስጥ

እግዚአብሔር ይነግሣል

ምንባብ፦1 ሳሙ 8:1–22፤ 1 ሳሙ 16:1–13

ጭብጥ

የሰው ነገሥታት ቢወድቁም የእግዚአብሔር መንግሥት ግን ታሸንፋለች።

መግቢያ

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለ እያንዳንዱ ታሪክ ስለ እግዚአብሔር መንግሥት እውነትን ይነግረናል። በመጀመሪያ ሳሙኤል መጽሐፍ ውስጥ፣ እስራኤል ከመሳፍንት አገዛዝ ወደ ንጉሣዊ አገዛዝ የተሸጋገረችበትን የታሪክ ምዕራፍ እንመለከታለን። ሕዝቡ "እንደ አሕዛብ ሁሉ" ንጉሥ እንዲነግሥላቸው የጠየቁት ጥያቄ እረፍት የሌለውን ልባቸውን ይገልጣል፤ ይህም ቁጥጥርን፣ በዓይን የሚታይ መሪንና ሰብአዊ ደኅንነትን መፈለጋቸው ነው። ይሁን እንጂ፣ በዓመፃቸው መካከል እንኳን እግዚአብሔር የእርሱ ንግሥና የበላይ መሆኑን ያሳያል። መልእክቱ ዘላቂ ነው የእግዚአብሔር መንግሥት በሰው ውድቀት አትናወጥም—በመለኮታዊ ታማኝነት ግን ወደፊት ትገሰግሳለች። ምክንያቱም የእግዚአብሔር መንግሥት በሰው ጥንካሬ ወይም ምርጫ ላይ ሳይሆን በእግዚአብሔር ሉዓላዊ ምርጫና ዘላለማዊ ዕቅድ ላይ የተመሠረተች ናት ነው።

I. መለኮታዊ ንግሥናን አለመቀበል (1 ሳሙኤል 8)

እስራኤላውያን ንጉሥን ሲጠይቁ፣ጥያቄያቸው የፖለቲካ ለውጥ ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ክህደትም ነበረ። ሳሙኤል ሰብአዊ ንጉሥ "እንደሚነግስባቸውና" "እንደሚገዛቸው" ቢያስጠነቅቃቸውም፣ እነርሱ ግን አጥብቀው ይህንኑ ለመኑ። የእግዚአብሔር ምላሽ አስገራሚ ነበር "እኔ በእነርሱ ላይ እንዳልነግሥ እኔን ናቁ እንጂ አንተን አልናቁህም።"አለው።

ቁልፍ እውነት፦
• የእስራኤል ፍላጎት የተሳሳተ እምነትን ያሳያል። እግዚአብሔር በቀጥታ እንዲመራቸው አልፈለጉም፤ ይልቁንም ሌሎች አሕዛብ ያላቸውን አይነት ንጉስ ፈለጉ።
• እግዚአብሔር ጥያቄያቸውን ፈቀደ—ይህ ግን ይሁንታው ሳይሆን ተግሣጹ ነበረ። የእርሱ ሉዓላዊነት በዓመፃቸው ውስጥም እንኳ ይሠራልና።
ተግባራዊ ትምህርት፦ እኛም ብዙ ጊዜ የማይታየውን የእግዚአብሔርን አገዛዝ በሚታዩ ምትኮች እንለውጣለን—በሥልጣን፣ በዝነኝነት፣ በገንዘብ ዋስትና ወይም በሰው ዘንድ ተቀባይነትን በማግኘት። ነገር ግን የእግዚአብሔር መንግሥት ከተከፋፈለ ታማኝነት ጋር አብራ አትቆምም። መንገዶቹ ተሰወሩ ቢመስሉም እንኳ ለሥልጣኑ እንድንገዛ ይጠራናል።

II. የሰው ንግሥና መነሳት (1 ሳሙኤል 9–15)

እግዚአብሔር የፈለጉትን ዓይነት ንጉሥ ሰጣቸው። ሳኦል ረጅም፣ ግርማ ያለውና ማራኪ ሰው ነበር። ነገር ግን የሳኦል አገዛዝ የሰውን ልብ ደካማነት ገለጠ። ሳኦል ውድቀቱና ደካማንቱ የጀመረው ከእግዚአብሔር ይልቅ ሰውን መፍራት በጀመረ ጊዜ ነው (1 ሳሙ. 15:24)። የሳኦል አለመታዘዝ የሚያሳየው፣ በተሰጥኦ ባለቤት የሆኑ መሪዎች እንኳ ለፈቃዱ ካልተገዙ የእግዚአብሔርን መንግሥት ሊያስቀጥሉ እንደማይችሉ ነው።
ቁልፍ እውነት፦
• የእግዚአብሔር መንግሥት በማራኪ ቁመና ወይም በችሎታ አይጸናም የሚጸናው በመታዘዝ ነው።
የሳኦል ውድቀት እንደ እግዚአብሔር ልብ ለሆነውና ለሚመጣው ታላቅ ንጉሥ መንገድ ጠራጊ ሆነ።
ተግባራዊ ትምህርት፦ ልቡ ለራሱ ወይም እንደ ልቡ የሆነን ሰው፣ ያማረ ዘውድ የእግዚአብሔር ሕዝብ እውነተኛ ንጉሥ ሊያደርገው አይችልም። የሳኦል ውድቀት ለዚህ እውነት ሕያው ምስክር ነው።

III. የእግዚአብሔር እውነተኛ ንጉሥ መገለጥ (1 ሳሙኤል 16)

ሳሙኤል ዳዊትን ሲቀባው፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት የልብ ትርታ እንመለከታለን። እግዚአብሔር ለነቢዩ እንዲህ አለው፦ "ሰው ፊትን ያያል፣ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል።" የዳዊት ታሪክ እንደሚያሳየው እውነተኛ ንጉሥነት የሚመነጨው ከመለኮታዊ ምርጫና ከውስጣዊ ቅንነት እንጂ ከማዕረግ ወይም ከጉልበት አይደለም።
ቁልፍ እውነት፦
• የእግዚአብሔር መንግሥት የሚሠራው ሙሉ በሙሉ ለእርሱ በሚገዙ በተመረጡ አገልጋዮቹ በኩል ነው።
• ዳዊት ፍጹም ታዛዥ የሆነውንና ዙፋኑ ዘላለማዊ የሆነውን ዋናውን ንጉሥ ኢየሱስ ክርስቶስን ያሳየናል።
ተግባራዊ ትምህርት፦ የመንግሥቱ ጥሪ የውስጥ ታማኝነት ጥሪ ነው። እግዚአብሔር ዛሬም ከእርሱ ጋር የተስማማ ልብን ይፈልጋል። የእግዚአብሔር መንግሥት የእግዚአብሔር ፈቃድ በሚደረግበት ስፍራ ሁሉ አለች ይህም መጀመሪያ በልባችን ውስጥ ይጀምራል።

IV. የክርስቶስ ማዕከላዊነት፦ ፍጹሙ ንጉሥ (Christological Fulfillment)

በ1ኛ ሳሙኤል ውስጥ የምናየው የንጉሥ ፍለጋ ፍጻሜውን የሚያገኘው በዳዊት ልጅ በናዝሬቱ ኢየሱስ ነው። እስራኤላውያን "እንደ አሕዛብ ሁሉ" ንጉሥ ቢፈልጉም፣ እግዚአብሔር ግን "ከአሕዛብ ሁሉ የተለየ" ሰማያዊ ንጉሥ አዘጋጀ።
ቁልፍ እውነት፦
• ከሳኦል ይልቅ የሚበልጥ፦ ሳኦል የሰውን ውጫዊ ግርማ ወክሎ ወድቋል፤ ኢየሱስ ግን በመስቀል ላይ ተዋርዶ ሳለ የእግዚአብሔርን እውነተኛ ክብርና ድል ገለጠ።
• ከዳዊት ይልቅ የሚበልጥ፦ ዳዊት "እንደ እግዚአብሔር ልብ" የሆነ ሰው ቢሆንም፣ እርሱ ግን ኃጢአተኛና ሟች ነበር። ኢየሱስ ግን ኃጢአት የሌለበት፣ ሞትን ድል አድርጎ የተነሣና መንግሥቱ መጨረሻ የሌለው የዘላለም ንጉሥ ነው።
• እውነተኛው ቅባት፦ ሳሙኤል ዳዊትን በዘይት ቀባው፤ አብ ግን ወልድን በመንፈስ ቅዱስ ቀባው። ዳዊት እስራኤልን ከፍልስጥኤማውያን አዳነ፤ ኢየሱስ ግን እኛን ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ነፃ አወጣን።
ተግባራዊ ትምህርት፦ ዛሬ ጥያቄው "ንጉሥ አለን ወይ?" ሳይሆን "ንጉሣችን ማነው?" የሚል ነው። የ1ኛ ሳሙኤል ታሪክ የሚያበቃው በምድራዊ ዙፋን ላይ ሳይሆን፣ በሰማያዊው ዙፋን ላይ ለተቀመጠው ለበጉ ክብር በመስጠት ነው። ሕይወታችንን ለዚህ ንጉሥ ስናስገዛ፣ የማይናወጠው መንግሥት ወራሾች እንሆናለን።

ማጠቃለያ

በእውነተኛው ንጉሥ ሥር ለመኖር ከመጀመሪያ ሳሙኤል መጽሐፍ የምንማረው፦ የእግዚአብሔር መንግሥት ሉዓላዊ ናት፤ በሰው ይሁንታ ላይ የተመሠረተች አይደለችም። ምድራዊ ነገሥታትና ሥርዓቶች ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔር አገዛዝ ግን ለዘላለም ይኖራል። የእስራኤል ተስፋ—የእኛም ተስፋ ዛሬ—በሰው ኃይል ሳይሆን ልቡ ከአብ ጋር ፍጹም አንድ በሆነው ንጉሥ ላይ ነው። ስለዚህ፣ በምድራዊ ሥልጣንና በመለኮታዊ ሉዓላዊነት መካከል ስንኖር፣ በእምነት እንዲህ እንበል፦ "እግዚአብሔር ለዘላለም ይነግሣል።" መንግሥቱ በሰው ጥንካሬ ላይ ሳይሆን በእርሱ ዘላለማዊ ዓላማ ላይ ስለቆመች ከቶ አትወድቅም። አሜን!!!!

Source: https://cmaeec.com/w...

the cross
Jesus is Lord
John 3:16

Whoever believes in him shall not perish but have eternal life.