Home » Sunday sermon – April 19, 2026

በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ መኖር

Last updated on April 19, 2026 - by Pastor Tariku Eshetu

የእግዚአብሔር መንግሥት በ1ኛ ነገሥት መጽሐፍ

ዋና ዋና ምንባባት፦ 1ኛ ነገሥት 2፡1–4፣ 3፡5–14፣ 8፡22–61

መሪ ሐሳብ

የእግዚአብሔር መንግሥት የሚመሠረተው በሰው ጉልበት ወይም ኀይል ሳይሆን በእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ታማኝነት፣ በመለኮታዊ ጥበብ እና የእግዚአብሔርን ክብር ከፍ በሚያደርግ አምልኮ ነው።

መግቢያ

የ1ኛ ነገሥትን መጽሐፍ ስናነብ፣ በእስራኤል ታሪክ ውስጥ ትልቅ የሽግግር ወቅት ላይ እንቆማለን።ይህም የዳዊት ዘመነ መንግሥት እየተፈጸመ፣ የሰሎሞን ግዛት ደግሞ እየጀመረ ነው። በዚህ ወሳኝ ወቅት ላይ አንድ ጥያቄ ይነሳል፦ እግዚአብሔር የሚፈልገው መንግሥት ምን ዓይነት መንግስት ነው? በፖለቲካዊ ኃይል ወይስ በሥነ-ምግባራዊ ታማኝነት የተገነባ?የሰሎሞን ታሪክ እንደሚያሳየን የእግዚአብሔር መንግሥት መንፈሳዊ ሥር ያለው ሲሆን፣ እርሱም ለቃሉ በመታመን፣ በጥበቡ በመመራት እና በሕዝቡ መካከል ባለው መገኘት ላይ ያተኮረ ነው። የዳዊት እና የሰሎሞን አገዛዝ የሚያስተምረን የተቀመጡበት ዙፋን የሰው ሳይሆን የእግዚአብሔር መሆኑን ነው። ምድራዊ መንግሥታት ይነሳሉ፣ ይወድቃሉም፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ግን በታማኝነት በሚመላለሱት መካከል ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።

1፦ የእግዚአብሔር መንግሥት መሠረቱ የቃል ኪዳን ታማኝነት ነው (1ኛ ነገ 2፡1–4)

ዳዊት ከማለፉ በፊት ለሰሎሞን እንዲህ የሚል መመሪያ ሰጠው፦ "አምላክህ እግዚአብሔር እንድተጠብቅ ያዘዘውን ጠብቅ፤ በመንገዱም ሂድ።" ይህ ትእዛዝ የማንኛውም መንግሥት እውነተኛ ጥንካሬ በሠራዊቱ ብዛት ወይም በሀብቱ ብዛት ሳይሆን፣ ለእግዚአብሔር ቃል ለመታዘዝ ባለው የቃል ኪዳን ታማኝነት ላይ መሆኑን ያስገነዝበናል። ዳዊት ለእግዚአብሔር ቃል መታዘዝ ለመለኮታዊ አገዛዝ መሠረት መሆኑን ተረድቶ ነበር። የማይታዘዝ ልብ ማንኛውንም መንግሥት ያዳክማል፤ ለእግዚአብሔር የታመነ ልብ ግን የማይናወጥ ዙፋን ይገነባል። የሰሎሞን ስኬት የተመሠረተው በታማኝነቱ ላይ ነበር። ለእኛም እንዲሁ ነው። የእግዚአብሔርን መታዘዝ የቃል ኪዳን መሠረቱን ይጥልልናል ጥበብ ደግሞ ያ መሠረት በየቀኑ እንዴት መገንባት እንዳለበት ትወስልናለች። ይህ ልናውቀው የሚገባ የመንግስቱ እውነት ነው።

2፦ የእግዚአብሔር መንግሥት በመለኮታዊ ጥበብ ወደፊት ይገሰግሳል (1ኛ ነገ 3፡5–14)

ሰሎሞን ንጉሥ በሆነ ጊዜ፣ ታላቁ ተግባሩ አሕዛብን ድል ማድረግ ሳይሆን በእግዚአብሔር ፊት በትሕትና መንበርከክ ነበር። በገባዖን በነበረው ሕልሙ፣ ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለማስተዳደር የሚረዳውን "ጥበብ" ለመነ፤ ይህም ልመና እግዚአብሔርን እጅግ ደስ አሰኘው። ይህ አጋጣሚ ለመንግሥተ ሰማያት የሚተጋ መሪ ሊኖረው የሚገባውን የልብ ዝንባሌ ያሳያል። ሰሎሞን የራሱን አቅም ማነስ አውቆ በእግዚአብሔር ጥበብና ማስተዋል ላይ ተደገፈ። ከዚህ የምንማረው የእግዚአብሔር መንግሥት በሰው ብልሃት ሳይሆን መለኮታዊ ማስተዋልን በሚሹ መሪዎች አማካኝነት እንደሚያድግ ነው። ሰሎሞን ሕዝቡን ለመምራት ጥበብን እንደፈለገ ሁሉ፣ ዛሬም እያንዳንዱ አማኝ ቤተሰቡን ለመምራት፣ ማኅበረሰቡን ለማገልገልና ፈተናዎችን በጸጋ ለማለፍ ከእግዚአብሔር ጥበብን ሊለምን ይገባል። ጥበብ እንዴት መኖር እንዳለብን ታስተምረናለች፤ አምልኮ ግን ለምን እንደምንኖር ይገልጣል ልባችንን በራሱ በንጉሡ ላይ እንድናደርግ ይረዳናል። ይህን እውነት ማወቅ ደግሞ የእግዚአብሔር ጥበብ በኛ ህይወት ወደፊት እንዲገሰግስ ያደርገዋል።

3፦ የእግዚአብሔር መንግሥት በአምልኮ እና በክብር ይገለጣል (1ኛ ነገ 8፡22–61)

ሰሎሞን ቤተ መቅደሱን ሲመርቅ ያደረገው ጸሎት የንግሥናው ማማ (ጫፍ) ነበር። እዚህ ጋር መንግሥቱ የሚታየው በቁሳዊ ውበት ሳይሆን በመንፈሳዊ እውነት ነው እግዚአብሔር በሕዝቡ መካከል በማደሩ። የእግዚአብሔር ክብር ቤተ መቅደሱን በሞላው ጊዜ፣ ሕዝቡ ተደፍተው ሰገዱ፣ አመሰገኑም። ይህ ትዕይንት የእግዚአብሔርን መንግሥት ምንነት በትክክል ያሳያል እርሱም የእግዚአብሔር መኖር (Presence) በሕዝቡ ውስጥ መሙላቱ ነው። አምልኮ የመንግሥቱ ቋንቋ ነው። ኃይልና ክብር የጌታ ብቻ መሆኑን ያውጃል። ቤተ መቅደሱ ሕንጻ ብቻ አልነበረም፤ በሰው ልብ ውስጥ ያለውን የእግዚአብሔር አገዛዝ የሚያሳይ ምልክት እንጂ። ቤተ መቅደሱ በእግዚአብሔር ክብር እንደበራ ሁሉ፣ እኛም በዕለት ተዕለት አምልኮና ራስን በመስጠት ስንኖር ሕይወታችን የእርሱን መገኘት ሊያንጸባርቅ ይገባል። መንግስቱ በአምልኮና በክብር እንዲገልጥ የእግዚአብሔርን መገኘት የአማኝ የሁል ጊዜ ርሀብ ሊሆን ይገባል።

ማጠቃለያ

የ1ኛ ነገሥት መጽሐፍ የእግዚአብሔርን መንግሥት ሕያው ሥዕል ይስላል በቃል ኪዳን ታማኝነት ላይ የተመሠረተ፣ በመለኮታዊ ጥበብ የሚጸና እና በክብር አምልኮ የሚገለጥ መሆኑን። ዳዊትና ሰሎሞን የሚያሳስቡን፣ በእግዚአብሔር ፊት ስኬት የሚለካው በምድራዊ ስኬት ሳይሆን በመንፈሳዊ ታማኝነት መሆኑን ነው። ዛሬም ያው አምላክ ይነግሣል። መንግሥቱ ለቃሉ በሚታዘዝ፣ ጥበቡን በሚሻና በሙሉ ልብ በሚያመልከው አማኝ ሁሉ ውስጥ ሕያው ናት። ታማኝ፣ ጥበበኞችና በክብሩ የተሞላን በመሆን የዚህ ዘላለማዊ መንግሥት ዜጎች እንሁን፤ ጌታ ብቻ ለዘላለም ንጉሣችን መሆኑን እንመስክር።

ለተግባራዊ ሕይወት የሚረዱ ነጥቦች (Application)

1. የቃል ኪዳን ታማኝነት፦ ዛሬ በሕይወታችን እግዚአብሔር የታመንን እንድንሆን እግዚአብሔር የጠየቀን በምን ጉዳይ ነው? መታዘዛችን ከበረከት በላይ ለክብሩ መሆኑን እናስተውል።

2. ጥበብን መሻት፦ በራሳችን ብልሃት ከመመካት ይልቅ፣ በቤተሰብም ሆነ በሥራ ጉዳይ የእግዚአብሔርን አቅጣጫ ለመጠየቅ ምን ያህል ጊዜ እንሰጣለን?

3. ክብሩን ማንጸባረቅ፦ ሕይወታችን ሰዎች እግዚአብሔርን እንዲያዩ የሚያደርግ "ቤተ መቅደስ" ነውን? አምልኮአችንን ከቤተክርስቲያን ቅጥር ውጭ ወደ ዕለት ተዕለት ተግባራችን እናውጣው።

Source: https://cmaeec.com/w...

the cross
Jesus is Lord
John 3:16

Whoever believes in him shall not perish but have eternal life.