Home » Sunday sermon – May 3, 2026

በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ መኖር

Last updated on May 3, 2026 - by Pastor Tariku Eshetu

የእግዚአብሔር መንግሥት ዜና መዋዕል ቀዳማዊ

መንግሥት የአንተ ናት

ምንባብ ፦1ኛ ዜና መዋዕል 17:1–15፤ 1ኛ ዜና መዋዕል 29:10–13

መግቢያ

የአንደኛ ዜና መዋዕል መጽሐፍ የታሪክ መጽሐፍ ብቻ አይደለም፤ የእግዚአብሔር መንግሥት መጽሐፍም ነው እንጂ።እግዚአብሔር ሕዝቡን በገዛ መገኘቱ፣ በተስፋ ቃሉ እና በዘላለማዊ አገዛዙ ዙሪያ በማደራጀት መንግስቱን እንዴት እንደሚገነባ ይነግረናል።ከዚህ እውነት አንጻር ዳዊት ለእግዚአብሔር ቤት ሊሠራለት ፈለገ፤ እግዚአብሔር ግን ከዚያ የሚበልጥ ነገር ገለጠለት እርሱም ምንድን ነው እርሱ ለዳዊት ቤት እንደሚሠራለት ነገረው። ያ ተስፋ ከምድራዊ መንግሥት አልፎ ወደ ዘላለማዊው የእግዚአብሔር መንግሥት ያመለክተናል። በዚህ መልዕክት ውስጥ የእግዚአብሔር መንግሥት በእርሱ ምርጫ የተመሠረተ፣ በመገኘቱ ላይ ያተኮረ እና በክብሩ የሚታወጅ መሆኑን እናያለን።

1. እግዚአብሔር መንግሥቱን በገዛ ምርጫው ይመሠርታል

በ1ኛ ዜና መዋዕል 17 ላይ ዳዊት ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ለመሥራት ያለውን ፍላጎት ገለጸ። እግዚአብሔር ግን ቤቱን የሚሠራው ዳዊት እንዳልሆነ ነገረው። ይልቁንም እግዚአብሔር ለዳዊት ቤት እንደሚሠራለት ቃል ገባ። ይህም እውነት የእግዚአብሔር መንግሥት በሰው ፍላጎትና ጥረት እንደማይጀመር ያስተምረናል።የእግዚአብሔር መንግሥት የሚጀምረው በመለኮታዊ ጸጋ ነው። ዳዊት ራሱን የገነባ/ያበቃ ሰው አልነበረም፤ እስራኤልም ያለ እግዚአብሔር ረዳትነት ራሷን የምታስተዳድር ሀገር አልነበረችም።ነገር ግን መንግሥቱ የቆመው እግዚአብሔር ስለመረጠው፣ ስለጠራውና ስለመሠረተው ነው። ዛሬም እውነቱ ይሄው ነው። የእግዚአብሔርን መንግሥት በሰው ኃይል፣ በብልሃት ወይም በሥልጣን አንገነባም።ሰወችን የሚጠራ፣ የሚያድንና የሚሾም እግዚአብሔር ነው። እግዚአብሔር መንግስቱን ካልመሠረተው፣ ሥራው ሊቆም/ሊጸና አይችልም። ስለዚህ የመጀመሪያው እውነት ይህ ነው፦ ዳዊት የተሾምበትና ያገለገለው መንግሥት የእግዚአብሔር ነው፤ ምክንያቱም የመሠረተው እርሱ ራሱ ነውና።

ተግባራዊ ልምምድ
በሰው ኃይል መታመንን ትተን በእግዚአብሔር ሉዓላዊ ዓላማ ላይ መታመን መጀመር አለብን። አገልግሎታችን፣ ቤተሰባችንና ቤተ ክርስቲያናችን መገንባት ያለባቸው በእግዚአብሔር ምርጫ ላይ እንጂ በእኛ ምርጫ ላይ መሆን የለበትም።

2. እግዚአብሔር መንግሥቱን በመገኘቱ ላይ ያደርገዋል

በዜና መዋዕል መጽሐፍ ውስጥ የቃል ኪዳኑ ታቦት ማዕከላዊ ስፍራ አለው። ታቦቱ ወደ ኢየሩሳሌም በመጣ ጊዜ፣ የእግዚአብሔር መገኘት በሕዝቡ መካከል ዋናው ነገር መሆን እንዳለበት አሳይቷል።የእግዚአብሔር መንግሥት ማለት ስለ ግዛት፣ ስለ አገዛዝ ወይም ስለ መሪነት ብቻ አይደለም።የእግዚአብሔር መንግሥት ማለት እግዚአብሔር በሕዝቡ መካከል ማደሩ ማለትም ጭምር ነው። በዜና መዋዕል መጽሐፍ ውስጥ አምልኮ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ለዚህ ነው። ካህናቱ፣ ሌዋውያኑ፣ መዘምራኑና የቤተ መቅደሱ አገልግሎት ሁሉ ወደ አንድ እውነት ያመለክታሉ ይህም የእግዚአብሔር ሕዝብ አምላኪ ሕዝብ መሆን አለበት ወደሚል እውነት ነው። እግዚአብሔር ችላ በሚባልበት ቦታ የእግዚአብሔር መንግሥት ሕያው አይሆንም። የእግዚአብሔር መንግሥት ሕያው የሚሆነው እግዚአብሔር በሚከበርበት ስፍራ ነው። ዳዊት ያለ እግዚአብሔር የሚቆም መንግሥት ባዶ እንደሆነ ተረድቶ ነበር። የእግዚአብሔር መገኘት የሌለበት ዙፋን/ስልጣን ዘላቂ ኃይል የለውም። አምልኮተ እግዚአብሔር የሌለባት ሀገር ውሎ አድሮ መፈራረሱ አይቀሬ ነው። ምክንያቱም ለሕዝቡ ሕይወትን፣ ቅድስናንና ማንነትን የሚሰጠው የእግዚአብሔር መገኘት ነውና።

ተግባራዊ ልምምድ
የእግዚአብሔር መገኘት በእውነት በሕይወታችን ውስጥ ማዕከላዊ ስፍራ አለው ወይ? ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን። በሃይማኖታዊ ተግባራት መጠመድና ከእግዚአብሔር ግን መራቅ ይቻላል። የመንግሥቱ ሕይወት የሚጀምረው ጌታን በድጋሚ በሕይወታችን ማዕከላዊ ስናደርገው ነው።

3. እግዚአብሔር መንግሥቱን ለክብሩ ያውጃል

በ1ኛ ዜና መዋዕል 29:10–13 ላይ ዳዊት በብሉይ ኪዳን ውስጥ ከሚገኙት ታላላቅ ጸሎቶች አንዱን አቅርቧል። እንዲህም አለ፦ "አቤቱ፥ ታላቅነትና ኃያል፥ ክብርም፥ ድልና ግርማ ለአንተ ነው... መንግሥትም የአንተ ነው"። ይህ የመልዕክቱ ማጠቃለያ ነው። መንግሥቱ ለዳዊት ክብር፣ ለእስራኤል ትዕቢት ወይም ለማንኛውም ሰብአዊ መሪ ዝና አይደለም። መንግሥቱ ለእግዚአብሔር ክብር ብቻ ነው። ዳዊት ኃይል፣ ሀብት፣ ክብርና ተሰሚነት ነበረው፤ ነገር ግን እነዚህ ሁሉ ከየት እንደመጡ ያውቅ ነበር። ነገሮች ሁሉ የጌታ እንደሆኑ ተረድቶ ነበር። ለዚህም ነው በልግስና የሰጠው፣ በትሕትና ያመለከውና እግዚአብሔርን በግልጽ ያመሰገነው። እውነተኛ የመንግሥቱ ሰዎች ክብርን ለራሳቸው አይሰበስቡም፤ ይልቁንም ክብርን ወደ እግዚአብሔር ይመልሳሉ። ይህ ደግሞ ከዳዊት የሚበልጠውን የእግዚአብሔርን ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስን ያሳየናል። እርሱ የመጣው የገዛ ራሱን ክብር ሊፈልግ ሳይሆን አብን ሊገልጥና ዘላለማዊ መንግሥትን ሊመሠርት ነው። በእርሱ ውስጥ የእግዚአብሔር አገዛዝ ፍጹም፣ ጻድቅና ዘላለማዊ ነው።

ተግባራዊ ልምምድ
መኖር ያለብን ለእግዚአብሔር ክብር እንጂ ለራሳችን አይደለም። እያንዳንዱ ስጦታ፣ እያንዳንዱ ስኬትና እያንዳንዱ ዕድል ለአምልኮ የሚቀርብ መሥዋዕት መሆን አለበት። እግዚአብሔር ሲከበር መንግሥቱ ያድጋል።

ማጠቃለያ

የአንደኛ ዜና መዋዕል መጸሀፍ እንደሚያስተምረን የእግዚአብሔር መንግሥት በሰው አይገነባም፣ በሰው ላይ አያተኩርም፣ ወይም ለሰው ክብር አይቆምም። በመለኮታዊ ምርጫ የተመሠረተ፣ በመገኘቱ ላይ ያተኮረና ለክብሩ የታወጀ ነው። የዳዊት የመጨረሻ ኑዛዜ የእያንዳንዱ አማኝ ኑዛዜ ሊሆን የመሚገባው ነው "አቤቱ፥ መንግሥት የአንተ ናት።" የመጽሐፍ ቅዱሳዊ እምነት እምብርት ይኸው ነውና። እግዚአብሔር ይነግሣል፣ እግዚአብሔር ያስተዳድራል፣ እግዚአብሔርም የገባውን ቃል ይፈጽማል።ስለዚህ ለንጉሡ እንስገድ። በመገኘቱ ፊት እናምልክ። ለክብሩ እንኑር። መንግሥቱ ለማያልቀው ለዘላለማዊው ንጉሥ ለኢየሱስ ክርስቶስ እንገዛ።አሜን!!!!

Source: https://cmaeec.com/w...

the cross
Jesus is Lord
John 3:16

Whoever believes in him shall not perish but have eternal life.