Home » Sunday sermon – June 28, 2026

በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ መኖር

Last updated on June 28, 2026 - by Pastor Tariku Eshetu

ገንዘብን በእግዚአብሔር መንግስት ውጥ መጠቀም

የንባብ ክፍል፦ ማቴዎስ 6፥19–24፤ 1ኛ ጢሞቴዎስ 6፥6–10፣ 17–19

መግቢያ

ገንዘብ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ውስጥ በጣም ከተለመዱት ጉዳዮች አንዱ ቢሆንም፣ በተመሳሳይ ጊዜ ደግሞ መንፈሳዊ ማንነታችንን በጉልህ ከሚያሳዩ ነገሮችም አንዱ ነው። ኢየሱስ ስለ ገንዘብ በተደጋጋሚ ተናግሯል፤ ይህን ያደረገው ገንዘብ በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ ከሁሉ የላቀ ነገር ስለሆነ ሳይሆን፣ ልባችንን ለማግኘት ከእግዚአብሔር ጋር በቀላሉ ስለሚወዳደር ነው።ምክንያቱም ገንዘብን የምንይዝበት መንገድ ማንን እንደምናምን፣ ምን እንደምንፈራ እና ከሁሉ በላይ ለምን ነገር ዋጋ እንደምንሰጥ ግልጥ አድርጎ ያሳያል። ብዙ ሰዎች የፋይናንስ ሰላም የሚገኘው በዋናነት ብዙ በማግኘት፣ ብዙ በመቆጠብ ወይም የተሻለ ምክር በማግኘት ይመስላቸዋል። እርግጥ ነው እነዚህ ነገሮች ሊረዱ ይችላሉ፣ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ ይልቅ ጠለቅ ያለ እውነትን ያስተመረናል። ስለዚህ የሚከተሉትን መርሆዎች ማወቅና ተግባራዊ በማድረግ የዚህ ትምህርት ተጥቃሚዎች እንሁን።

1፡እንደ አማኝ ማድርግ የማንችለውን ማወቅ

- በማቴዎስ ምዕራፍ 6 ላይ ጌታችን ኢየሱስ ግልጽ ማስጠንቀቂያ ይሰጠናል እንዲህ በማለት “ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ በአንድነት መገዛት አትችሉም” ። ይህ ማለት ገንዘብ ክፉ ነው ማለት አይደለም።ገንዘብ የመግዛት ኃይል ስላለው የሚገዛችሁን ምረጡ ማለት ነው እንጂ።ምክንያቱም ገንዘብ በእግዚአብሔር ሥልጣን ሥር ካልተገዛ እኛን መግዛት ይጀምራልና።በመሆኑም፣ክርስቲያናዊ የገንዘብ አያያዝ በጀት ስለማውጣት ብቻ የሚነጋገር አይደለም። ስለ አምልኮ፣ ስለ ጥበብ እና ስለ ምስክርነት ጭምር የሚነጋገርም ነው እንጂ።ምክንያቱም ለገንዘብና ለእግዚአብሔር በአንድነት መግዛት አንችልምና።

- መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚያስተምረው ገንዘብን በክርስቶስ ጌትነት ስር ለማስገዛት የመጀመሪያው ጉዳይ የባንክ አካውንታችን መጠን ሳይሆን የልባችን ሁኔታ መስተካከል ነው።ምክንያቱም አንድ ሰው ድሃ ሆኖ ታማኝ ሊሆን ይችላል፣ ወይም ባለጸጋ ሆኖ የገንዘብ ባሪያ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ እውነተኛው ጥያቄ “ገንዘቤን እንዴት ላስተዳድር?” የሚለው ብቻ ሳይሆን “ክርስቶስ በገንዘቤ ላይ እንዴት ይነግሣል?” የሚለውን ቀዳሚ የአማኝ ሀላፊነት ተግባራዊነት ማርጋገጥ ነው።ምክንያቱም ለገንዘብና ለእግዚአብሔር በአንድነት መገዛት አንችልምና

- በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፣ ገንዘብን ማገልገል ምን ማለት ነው፦ እግዚአብሔርን እንደ ብቸኛ ሀብትና መታመኛ ከመቁጠር ይልቅ፣ ለሀብት ወይም ለገንዘብ ተገዥ መሆን እና ሀብትን/ገንዘብን እንደ ትልቅ ውድ ነገር መቁጠር ማለት ነው። ይኸም የሚገለጠው እቅዶቻችንንና ባህሪያችንን ሁሉ ገንዘብ ሊሰጠን የሚችለውን ጥቅም ለማሳደግ ብቻ በማስላት በምናደርገው ተግባራዊ እንቅስቃሴ ነው።ነገር ግን ቃሉ ለገንዘብና ለእዚአብሔር በአንድነት መገዛት አትችሉም ይለናል።

- ገንዘብን ማገልገል በተግባር ሲገለጥ ምን ማለት ነው? ሕይወታችን በገንዘብ ተስፋዎች ዙሪያ ላይ ይሽከረከራል።እንዲሁም በየቀኑ “ከገንዘብ ምን ዓይነት ጥቅሞችን ማግኘት እችላለሁ?” ብለን እንጠይቃለን፣ እንዲሁም ለእግዚአብሔር ከመገዛት ይልቅ ከፍተኛ የፋይናንስ ትርፍ ወደሚያስገኝልን አቅጣጫ ምርጫዎቻችንን እንቀይሳለን ማለት ነው።በዚህ ጊዜ ገንዘብ መገልገያ መሳሪያ መሆኑን ይተውና ጌታችን ይሆናል ማለት ነው።በዚህ ሁኔታ እንዳንቀጥል ግን ለገንዘብና ለእግዚአብሔር በአንድነት መገዛት አትችሉም ተብለናል።

- ገንዘብ ጌታችን ይሆናል በተግባር ሲገለጥ ምን ማለት ነው? ፦ የገንዘብን “ጥያቄዎች” እንሰማለን፣ ፍላጎቶቹንም እንታዘዛለን፤ወይም የዚህን ጌታ ፍላጎቶች ያለምንም ጥያቄ ለማሟላት እራሳችንን እንሰጣለን ማለት ነው። በሌላ አባባል ክፍያዎችን፣ የዕዳ ጫናን፣ ማኅበራዊ ደረጃችንን ማስተካከልን፣ ደኅንነትን/የመኖር ዋስትናን ለማሟላት ማንኛውንም ዋጋ ስለገንዘብ እንከፍላለን፣ እንዲሁም ቅድሚያ የምንሰጣቸውን ነገሮች ገንዘብ እንዲወስንልን እንፈቅዳለን ማለት ነው። ነገር ግን ይህን ስናደርግ ለገንዘብና ለእግዚአብሔር በአንድ ላይ መገዛት አንችልምና ከፍተኛ ጭንቀትና ድባቴ ውስጥ እንወድቃልን።ልባችንም ለዕዚአብሔር ሳይሆን ለሀብት/ለገንዘብ የተገዛ ይሆናል።

- ልባችን ለሀብት የተገዛ ይሆናል ምን ማለት ነው? ፦ ኢየሱስ ለሁለት ጌቶች መገዛት አትችሉም፤ ወይም አንዱን ጠልታችሁ ሁለተኛውን ትወዳላችሁ ይላል (ማቴዎስ 6:24) ።ልባችን ለሀብት/ለገንዘ የተገዛ ይሆናል ማለት ፍቅራችን ታማኝነታችን፣ ተስፋችን እና ደኅንነታችን/የመኖር ዋስትናችን በእግዚአብሔር ላይ ሳይሆን በሀብት/በገንዘብ ላይ እንዲያርፍ ማድረግ ማለት ነው። ለገንዘብ ያለን ፍቅር ትላቅ ስለሚሆን ህሊናችንን መታዘዝ ይማንችል የገንዘብ አገልጋዮች እንሆናልን።ምክንያቱም ለገንዘብና ለእግዚአብሔር በአንድ ላይ መገዛት ስለማንችል።

- ገንዘብን እያገለገልን መሆኑን እንዴት እናውቃልን? ገንዘብን ማገልገል በገንዘብ አጠቃቀማችንና በሕይወት ዘይቤአችን ላይ ይንጸባረቃል። ገንዘብን እያገለገልን መሆናችንን ማወቅ የምንችለው ገንዘባችን ወዴት እንደሚሄድና የያዝናቸው ንብረቶች ስለ ውስጣዊ ፍላጎታችን ምን እንደሚመሰክሩ በማየት ነው።ስግብግብነት፣ ራስ ወዳድነት የሞላበት ምቾት ወይም ድሆችን ለመርዳት ፈቃደኛ አለመሆን አብዛኛውን ጊዜ ገንዘብን ማገልገልን የሚያሳዩ ጥሩ ምልክቶች ናቸው።በዚህ ዓይነት የህይወት ስረዓት እይኖሩ እውነተኛውን የልብ ደስታና እርፍት ማግኘት አይቻልም።ምክንያቱም ለገንዘብና ለእግዚአብሔር በአንድ ላይ መገዛት ስለማይቻል።

- እግዚአብሔርን ማገልገልና ገንዘብን የማገልገል ልዩነት ምንድነው? ፦ አንድ ልብ ማለት ያለብን ነገር ቢኖር የሀብት/የገንዘብ መኖር እና ሀብትን/ገንዘብን ማገልገል አንድ አለመሆናቸውን ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስ ሀብት እኛን ከእግዚአብሔር የመሳብ ኀይል ስላለው በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ “አታላይ” እና እንቅፋት እንደሚሆን ያስጠነቅቃል፣በዚህ ማስጠንቀቂያ መሰረት በመኖር ለእርሱ ባልተገዛንበት ጊዜ ገንዘብን እግዚአብሔርን ለማክበር ልንጠቀምበት እንችላለን ወይም ገንዘብን የእግዚአብሔርና የእኛ አገልጋይ እንደርገዋለን።በሌላ አባባል ከገንዘብ ባርነት ነጻ በመሆን ገንዝብን እግዚአብሔርን ለማክበር በመጠቀም እግዚአብሔርን እናገለግልበታልን ማለት ነው።ምክንያቱም ለገንዘብና ለእግዚአብሔር በአንድ ላይ መገዘት ስለማንችል። ልዩነቱም ይሔው ነው።

ማጠቃለያ

ገንዘብን በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ ለእግዚአብሔር በማስግዛት ለመጠቀም እንዲሁም በገንዘብ እግዚአብሔርን እያከበርንና እያገለገልን ለመኖር እንድንችል ለገንዘብና ለእግዚአብሔር በአንድ ጊዜ መገዛት የማንችል መሆኑን መገንዘብና ከገንዝብ ባርነት ነጻ ሊያወጣን ለሚችለው ለቃሉ የእውነት መርህ እርሳችንን እንስጥ።ለገንዘብና ለእግዚአብሔር በአንድ ላይ መገዛት አንችልምና።

Source: https://cmaeec.com/w...

the cross
Jesus is Lord
John 3:16

Whoever believes in him shall not perish but have eternal life.