ሁሉም ነገር የእግዚአብሔር ነው እኛ ባለአደራዎች ነን።
ገንዘብን በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ ለመጠቀም ማወቅ የሚገባን ሁለትኛው መርህ መጽሀፍ ቅዱስ ስለ ባለአደራነት የሚያስተምረውን እውነት በቅጡ መርዳት ነው። ለዚህ እንዲርዳን አስቅድመን የእግዚአብሔርን የባለቤትነት ትርጉም እንመለከታለን። ዳዊት በመዝ 24፥1 1ኛ ዜና 29፥11–14 “ምድርና በእርስዋ የሞላው ሁሉ የእግዚአብሔር ነው” ሲል ያውጃል። ይህ እውነት ስለገንዝብ ያልንን የተሳሳተ መርዳት ሁሉንም ነገር ይለውጠዋል።ምክንያቱም ምድር የእግዚአብሔር ከሆነች፣ ገቢያችን፣ ንብረታችን፣ ስጦታዎቻችን፣ ጉልበታችን ጊዜአችን እና የወደፊት ሕይወታችንም ሁሉ የእርሱ ናቸው ማለት ነው። ሁሉ የእግዚአብሔር ነውና።
ባለአድራነት ማለት ደግሞ፦ እግዚአብሔር የሁሉም ነገር ባለቤት መሆኑን ማወቅ እና እኛ ደግሞ እርሱ በአደራ የሰጠንን ስጦታዎች፣ ሀብቶች፣ ጊዜ፣ ችሎታዎች እና ዕድሎች የምናስተዳድር ሥራ አድራ ተቅባዮች/ባለአደራዎች መሆናችንን መረዳት ነው። ይህም በክርስቲያናዊ የግንዘብ አጠቃቀም ህይወታችን ውስጥ፣በታማኝነት ኃላፊነትን በመወጣት፣ በምስጋና እና በእግዚአብሔር ፊት በሚኖር ተጠያቂነት የሚታወቅ የሕይወት ዘይቤን መኖር ማለት ነው።
የባለአድራነት ዋናው ሐሳብ
• ያለን ነገር ሁሉ ባለቤቱ እግዚአብሔር ነው፤ እኛ ጠባቂዎች ነን የሚል ነው።
• ባለአደራነት ከገንዘብ በላይ የሆነን ነገር ሁሉ ያጠቃልላል፤ እሱም ጊዜን፣ ተሰጥኦን፣ መንፈሳዊ ስጦታዎችን፣ ወንጌልን እና መላው ሕይወታችንን ያካትታል።
የባለአደራነት ግቡ እግዚአብሔር የሰጠንን ነገር ለእርሱ ክብር እና ለሌሎች መልካምነት መጠቀም ነው።ይህ በቀላል ትርጉም በአጭሩ ሲቀመጥ ደግሞ፡ መንፈሳዊ ባለአድራነት ማለት “የእግዚአብሔር የሆነውን ነገር በታማኝነት ማስተዳደር” ማለት ነው ይህም የከበረ ነገር አደራ እንደተሰጠው ሰው አደራ ለሰጠው አካል ተግባራዊ መልስ በመስጠት መኖር ማለት ነው።
መጽሐፍ ቅዱሳዊ አፅንዖት፦
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፣ ባለአደራነት ከእግዚአብሔር ስጦታዎች ጋር የተያያዘ መሆኑን መገንዘብ እና እነዚያን ስጦታዎች እንደ ባለቤት ሳይሆን በእግዚአብሔር ሥልጣን ሥር እንዳሉ አገልጋዮች በኃላፊነትና በታማኝነት ከመጠቀም ጋር በጽኑ የተያያዘ መሆኑን የሚያረጋግጥ አስተምህሮ ነው። ስለዚህ፣ባለአደራነት የቤተክርስቲያንን የገንዘብ አያያዝና አስተዳደር የሚያመለክት ቃል ብቻ ሳይሆን የክርስቲያናዊ ደቀ መዝሙርነት አካልም ጭምር ነው።ባጠቃላይ መንፈሳዊ ባለአደራነት ማለት በማንኛውም የሕይወት ዘርፍ የእግዚአብሔር ታማኝ ጠባቂ/አገልጋይ ሆኖ መኖርማለት ነው።
ባለአደራነትን በተግባር ማዋል
ባለአደራነትን በተግባር ማዋል ማለት፦ ጊዜችንን፣ ገንዘባችንን፣ ስጦታዎቻችንን፣ አካላችንን፣ ግንኙነታችንን እና ዕድሎቻንን ለራሳችን ብቻ እንደምንጠቀምባቸው የግል ንብረቶች ማየት አቁመን፣ ባንጻሩ ደግሞ እንዚህን ስጦታዎች እግዚአብሔር የሰጠን በታማኝነት ልንገለገልባቸው ከእግዚአብሔር የተሰጡ አደራዎች አድርገን መቁጠር እና ባለአደራነትን በተግባር ማሳየት መቻል ነው።ይህን ስናደርግ መልካም የባለአደራነት ዕለታዊ ልማድ የሚጀምረው ራስን በመስጠት ወይም እራስን በመገዛት ነው፣ እንዲሁም የታሰበባቸው ውሳኔዎችን መወሰንና፣ በመጨረሻም የተቀበልነውን ሁሉ በጥንቃቄ በመጠቅምና በምስጋና ይጠናቀቃል።
ወደ ዕለታዊ የባለአድራነት ተግባራዊ ልምምዶች ለመግባት
• ቀኑን ስንጀምር የጊዜ ሰሌዳችንን ለእግዚአብሔር በመስጠት እና ጊዜያችንን እንዴት መጠቀም እንዳለብን ጥበብን ከእርሱ በመጠየቅ መጀመር።
• በየዕለቱ በሕይወታችን ላይ ፈጣን “የባለአድራነት ቁጥጥር” እናድርግ ይህም ማለት ጊዜያችንን፣ ገንዘባችንን፣ ጉልበታችንን እና ትኩረታችንን እንዴት እየተጠቀምነው እንደሆነ በቃሉ መሰርት መገምገም።
• በየዕለቱ ስጦታዎቻችንን በቤተክርስቲያን፣ በቤተስብ ውስጥ እና በማኅበረሰብ ውስጥ ሌሎችን ለማገልገል በተግባራዊ መንገድ እንጠቀምባቸው።
• ከየዕለቱ ግቢና ወጪአችን የቀረውን ትርፍ ነገር ለመስጠት ከመጠበቅ ይልቅ፣ በጥበብ በጀት እናውጣ እና በልግስና እንስጥ።
• በየዕለቱ እግዚአብሔር አደራ የሰጠንን ነገር የሚያባክኑ ብክነቶችን፣ ትኩረትን የሚከፋፍሉ ነገሮችን እና ግድየለሽ የሆኑ ልማዶችን እናስወግድ። ምክንያቱም ባለአደራነት ሀብትን ስለማስተዳደር ብቻ ስይሆን፤ነገር ግን ስለ ምስጋና፣ ታዛዥነት እና ለእግዚአብሔር ያለንን ፍቅር ጭምር የሚመለክት ነውና። ይህም ማለት “ዛሬ እግዚአብሔር በሰጠኝ ነገር እንዴት እርሱን ማክበር እችላለሁ?” ብሎ መጠየቅ ማለት ነው።
ቀለል ያለ ዕለታዊ የባለአደራነት የሕይወት ዘይቤ
1. ጠዋት መጸለይ፦ ቀኑን ለእግዚአብሔር አደራ መስጠት።
2. አንድ የታሰበበት በጎ ተግባር መምረጥ
3. የአገልግሎት ወይም የልግስና ሥራ መሥራት።
ማታ ቀኑን መገምገም፦ የትኛው ላይ ታማኝ ነበርኩ? እግዚአብሔር የሰጠኝን በምን ላይ አዋልኩ? እግዚአብሔርን ማመስገንን ለነገ የሚሆን አንድ ትንሽ መሻሻል ማቀድ።
እኛ ፍጹም ባለቤቶች ሳንሆን ባለአደራዎች የመሆናችን ተግባራዊ ማሳያ።
ያለን ነገር ሁሉ ከእግዚአብሔር እጅ የተቀበልነው የጸጋው ውጤት/ትሩፋት ነው። በ1ኛ ዜና ምዕራፍ 29 ላይ ያለው የዳዊትና የእስራኤል ህዝብ ታሪክ እጅግ ኃይለኛ የሆነው ይህንን እውነት በተግባር ስለሚያስይ ነው። ዳዊትና ሕዝቡ ለቤተ መቅደሱ ግንባታ በደስታና በልግስና ገንዘብና ስጦታ ሰጥተዋል፣ ነገር ግን ዳዊት ገና ከጅማሬው የራሳቸው የሆነን ነገር እንደሚሰጡ አድርጎ አላሰበም።ለዚህ ነበር ሲጸልይ፦ “ሁሉ የተገኘው ከአንተ ነው፥ ለአንተም የሰጠንህ ከእጅህ የተቀበልነውን ብቻ ነው።” ያለው።
ከዚህ እውነት አንጻር አንድ ክርስቲያን ለገንዘብ ሊኖረው የሚገባው ትክክለኛ አመለካከትና መርህ ይህ ነው። በሀብታችን ላይ እንደ ጌታ ወይም እንደባለቤት አልጠቀምም ማለትና፤ ነገር ግን ከእግዚአብሔር ስልጣንና ባለቤትነት በታች እንደ አገልጋይ እቆማለሁ ማለትን ነው። ይህ እውነት ትዕቢትን ያርማል። ባለጸጎች በሀብታቸው እንዳይመኩ ያሳስባቸዋል፣ ምክንያቱም ሀብታቸው በራሳቸው ኃይል የተፈጠረ አይደለምና።ይህ እውነት ድሆችንም ያጽናናቸዋል፣ ምክንያቱም የእግዚአብሔር ባለቤትነት ሕይወታቸው እንዳልተረሳ ወይም እንዳልተጣለ ያሳያልና። ሁሉም ነገር የእግዚአብሔር ከሆነ፣ ማንኛውም አማኝ ከእርሱ እንክብካቤ ውጭ አይሆንምና።
ማጠቃለያ፦
እንደ አማኝ የገንዘብ ውሳኔዎችን ከማድረጋችን በፊት፣ “ጌታ ሆይ፣ አስቀድሞ የአንተ የሆነውን ይህን ነገር እንዴት እንድጠቀምበት ትፈልጋለህ?” ብለን ፈቃዱን መጠየቅ ይገባናል ነግር ግን በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ ይህን አለማድረግ ግልጽ የሆነ አመጻ ነው።ምክንያቱም በጃችን ላይ ላለው ነገር ሁሉ እኛ ባለቤቶች ሳንሆን ባለአደራዎች ነንና። በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ ገንዘብን ጨምሮ ከእርሱ የተቀበልነውን ሁል ልነጥቀምበት የሚግባን በዚህ መርህ መሰርት ነው።ባለአደራዎች እንጂ ባለቤቶች አለመሆናችንን እንወቅ።
Source: https://cmaeec.com/w...
John 3:16
Whoever believes in him shall not perish but have eternal life.