3. ሰማያዊ/መንፈሳዊ ጥበብ ገንዘብን በአግባቡ ያስተዳድረዋል ይህን ማወቅ
መንፈሳዊ ጥበብ ምንድነው?
መንፈሳዊ ጥበብ አንድ ሰው የእግዚአብሔርን ፈቃድ እንዲለይና እርሱን በሚያከብር መንገድ እንዲኖር የሚረዳ ከእግዚአብሔር የሚሰጥ ማስተዋል ነው። በክርስትና አስተምህሮ ትርጓሜ ውስጥ መንፈሳዊ ጥብበ ከእውቀት ወይም ከሕይወት ተሞክሮ በላይ ነው። መንፈሳዊ ጥበብ በመንፈስ ቅዱስ በቅዱሳት መጻሕፍት እውቀት፣ በትሕትና እና በታዛዥነት የተቀረጸ ጥልቅ ግንዛቤ ነው።
መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትርጉም
መጽሐፍ ቅዱስ መንፈሳዊ ጥበብን “እግዚአብሔርን በመፍራት” እና “እግዚአብሔርን በትክክል በማወቅ” ላይ የተመሠረተ እንደሆነ አድርጎ ያቀርበዋል። ያዕቆብ ይህንን ጥበብ ንፁህ፣ ታራቂ፣ ገር፣ ምሕረት የሞላበት እና ቅን በማለት ይገልጸዋል፤ ይህም መንፈሳዊጥ ጥበብ በዕውቀት ልክ የሆነና በባህሪም እንደሚለካ ያሳያል። ያዕ 3:13,17
የመንፈሳዊ ጥበብ ተግባራዊ ትርጉም፦መንፈሳዊ ጥበብ በተግባር ሲታይ፣ አንድን ሰው የሚከተሉትን እንዲያደርግ ይረዳዋል፦
ከእግዚአብሔር ዓላማዎች ጋር የሚስማሙ ውሳኔዎችን መወሰን ያስችለዋል።
እውነትን ከስህተት መለየት ያስችለዋል።
ለሰዎች በጸጋ እና በማስተዋል ምላሽ መስጠት እንዲችል ያደርገዋል።
የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በዕለት ተዕለት ሕይወት ላይ መተግበር ያስችለዋል።
በቀላል መንገድ ለመግለጽ መንፈሳዊ ጥበብ ማለት የእግዚአብሔርን እውነት እንድንረዳና እንድንኖረው መንፈስ ቅዱስ እኛን የሚረዳበት መንገድ ነው። ከዚህ ትንታኔ ስንነሳ መንፈሳዊው ጥበብ የሚያስተምረን ገንዘብ የእግዚአብሔር እንደሆነ ነው፤ ባለአደራነት ደግሞ ለእርሱ ክብር እንዲሆን አደራ የሰጠንን ገንዝብ በታማኝነት መጠቀም ነው።
መንፈሳዊ ጥበብ የሚጀምረው እግዚአብሔር ባለቤት መሆኑን በመቀበል ነው
መዝ 24:1 ምድርና በእሷ ውስጥ ያለው ሁሉ የጌታ እንደሆነ ይናገራል። ምሳ 3:9 እግዚአብሔርን በሀብታችንና ከፍሬያችን ሁሉ በበኩራቱ እንድናከብር ያስተምረናል።ስለዚህ ብልህ ባለአደራነት የሚጀምረው “ያለኝ የእኔ ነው” ማለትን ትተን “ያለኝ የእግዚአብሔር ነው” ማለት ስንጀምር ነው። እግዚአብሔር ባለቤት ከሆነ፣ እኛ አስተዳዳሪዎች እንጂ ጌቶች አይደለንም ማለት ነው። ይህ እውነት ገንዘብን እንዴት እንደምናወጣ፣ እንደምናስቀምጥ፣ እንደምንሰጥ እና እንደምናቅድ ይወስንልናል።
መንፈሳዊ ጥበብ ለገንዘብ ሳይሆን ለእግዚአብሔር እንድንገዛ ያስተምረናል
ማቴዎስ 6:24 ማንም ለሁለት ጌቶች መገዛት እንደማይችል፣ወይም ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት እንደማይቻል ይናገራል። ገንዘብ መልካም አገልጋይ ነው ነገር ግን፤በመንፈሳዊ ጥበብ ካልገዛነው ክፉ ጌታ ነው።ገንዘብ ጌታችን በሚሆንበት ጊዜ ፍርሃትን፣ ስግብግብነትን፣ ጭንቀትንና ራስ ወዳድነትን ይወልዳል። ያዕ 3:17 ከላይ የሆነችውን ጥበብ ንፁህ፣ ታራቂ፣ ገርና ምሕረት የሞላባት አድርጎ ይገልጻታል።ስለዚህ የእግዚአብሔር ጥበብ ገንዘብን በራሱ ተገቢ ቦታ ላይ እንዲሆንና በጌታ አገዛዝ ሥር እንዲቆይ ያደርገዋል።
መንፈሳዊ ጥበብ ከብዛቱ ይልቅ ለታማኝነት ዋጋ ይሰጣል
ሉቃ 16:10-11 በጥቂቱ የታመነ በብዙ ደግሞ ኃላፊነት እንደሚሰጠው ይናገራል።እግዚአብሔር ባለአደራነትን የሚመዝነው በስጦታው ታላቅነት ብቻ ሳይሆን በልብ ታማኝነት ጭምር ነው። በማር 12:41-44 ላይ የተጠቀሰው የደሀዋ መበለት መዋጮ፣ እግዚአብሔር የሚያየው መስዋዕትነትን እንጂ ብዛቱን ብቻ እንዳልሆነ ያሳያል።ስለዚህ ጠቢብ አማኝ ታላቅ ነገርን ከመጠበቁ በፊት በጥቃቅን ነገሮች የታመነ ነው።በገንዘብ ላይ ያለን ታማኝነት የሚረጋገጠው በትላልቅ ወጭዎች ብቻ ሳይሆን በተለመዱት የዕለት ተዕለት ልምዶቻችን ውስጥ ነው።ለዚህ ነው መንፈሳዊ ጥበብ አስፈላጊአችን የሆነው።
መንፈሳዊ ጥበብ ገንዘብን የሚጠቀመው ዘላለማዊነትን አልሞ ነው
ማቴ 6:19-21መዝገባችንን በሰማይ እንድንሰበስብ እንጂ በምድር ላይ እንዳናከማች ያስተምረናል።ምድራዊ ሀብት ጊዜያዊ ነው፤ ዘላለማዊ ሀብት ግን ጸንቶ ይኖራል።ጠቢብ ባለአደራ በልግስና ይሰጣል፣ የእግዚአብሔርን ሥራ ይደግፋል፣ ችግረኞችን ይረዳል፣ እንዲሁም ሀብቱን ለክርስቶስ መንግሥት ዓላማዎች ያውላል። ለዚህ ነው 1ጢሞ 6:17-19 ባለጠጎች እንዳይታበዩ ወይም በማይረባ ባለጠግነት ላይ ተስፋ እንዳያደርጉ የሚያስጠነቅቀው። ምክንያቱም የመንግስቱ ልጆች ግባችን እንዲሁ የገንዘብ ስኬት ማግኘት ብቻ ሳይሆን ዘላለማዊ ፍሬ ማፍራት ነው።
መንፈሳዊ ጥበብ ባለን መርካትን ያመጣል፣ ከስግብግብነትም ይጠብቃል
1 ጢሞ 6:6 እግዚአብሔርን መምሰል ባለን ነገር ከመርካት ጋር ታላቅ ትርፍ እንደሆነ ይናገራል። ስግብግብነት መቼም አይረካም፤ ሁልጊዜ ተጨማሪ ይጠይቃል። ጠቢብ ባለአደራነት ግን በሥርዓት ማውጣትን፣ በአመስጋኝነት መኖርን እና በእግዚአብሔር አቅርቦት ላይ መታመንን ያካትታል።ቅዱስ ቃሉም በዕብ 13:5 ባለን ነገር እንድንረካ ያዝዘናል። ባለን ነገር መርካት ልባችንን የንብረት ባሪያ ከመሆን ይጠብቀዋልና።
መንፈሳዊ ጥበብን ለመተግብር የሚርዱ መመዘኛዎች
ገንዘብን እንዴት ነው የማየው? የእግዚአብሔር ንብረት አድርጌ ወይስ የራሴ አድርጌ ነው የማየው? የገንዘብ አወጣጥ ሁኔታ መመርመር፦ገንዘብ አወጣጤ እምነትን፣ የስሜት መረጋጋትን ወይስ ፍርሃትን ያንጸባርቃል? የገንዘብ አሰጣጥን መገምገም፦ ለአምልኮና ታስቦበት የሚደረግ ነው?የገንዘብ ቁጠባችንን እና እቅዳችንን መገምገም፦ ጥበባዊ እና ኃላፊነት የተሞላበት ነው? የፋይናንስ ግባችን እግዚአብሔርን ለማክበር እየረዳን መሆኑንና አለመሆኑን ማረጋገጥ።
የመንፈሳዊ ጥበብ ተግባራዊ እርምጃዎች
መጽሐፍ ቅዱስ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ነገሮች ቅድሚያ መስጠትን የሚያረጋግጥ በጀት ማዘጋጀት፣ ፣ከወጪ ሲተርፍ ወይም የምንፈልገውን ሁሉ አድርገን የተረፈ ካለ ሳይሆን መጀመሪያ ለእግዚአብሔር መንግስት ስራ መስጠት አለብን። ነፃነትን የሚያሳጣና ወደ ባርነት የሚመራውን ዕዳ ማስወገድ።ለሚያስፈልጉ ነገሮችና ለወደፊት ኃላፊነቶች በጥበብ መቆጠብ። ልግስናን እንደ አምልኮ ተግባር መለማመድ። ለጥቃቅን ነገሮችም ቢሆን እንኳን፣ በገንዘብ ውሳኔዎች ላይ፣ ከመወሰናችን በፊት መጸለይ።
ማጠቃለያ
መንፈሳዊ ጥበብ እና የገንዘብ ባለአደራነት የማይነጣጠሉ ነገሮች ናቸው። ጥበብ እጥረትን ከመፍራት ይልቅ እግዚአብሔርን መፍራትን ታስተምረናለች። ባለአድራነት ደግሞ ገንዘብን በታማኝነት፣ በልግስና እና ከዘላለማዊነት አንጻር እንድናስተዳድር ያስተምረናል። ስለዚህ ዋናው ጥያቄ ምን ያህል ገንዘብ አለን የሚለው ሳይሆን፣ በእጃችን ባለው ነገር እግዚአብሔርን እያከበርን ነው ወይ የሚለው ነው።ስለሆንም እግዚአብሔር ልቦናችንን፣ ልማዶቻችን እና ሀብታችንን እንዲቀርጽ እንፍቀድ፣ከስግብግብነት ይልቅ ጥበብን፣ ከብክነት ይልቅ ባለአድራነትን፣ ከፍርሃት ይልቅ ታማኝነትን እንምርጥ።ገንዘብን በመንፈሳዊ ጥበብ እንስተዳድር።
Source: https://cmaeec.com/w...
John 3:16
Whoever believes in him shall not perish but have eternal life.