በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ፡በልግስና መስጠት። 2ኛ ቆሮንቶስ 9:6–8
በዚህ ትምህርት የምንመለከተው በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ስላለው ልግስና ነው። ልግስና ገንዘብ ከመስጠት ያለፈ የህይወት ስርዓት ነው። ምክንያቱም ልግስና የእግዚአብሔርን ማንነትና ባሕርይ የሚያንጸባርቅ እንዲሁም የአማኞችን የልብ ሁኔታ የሚገልጥ እውነት ስለሆነ። በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ በልግስና የምንሰጠው እግዚአብሔር አስቀድሞ ልጁን ስለሰጠን ነው። ስለዚህ ጳውሎስ በ2ኛ ቆሮንቶስ 9 ላይ ልግስናን በተመልከተ የሰጠውን መርህ በመክተል ገንዘብን በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ ለማስተዳደር እንድንችል የልግስናን መርህ ጠጋ ብለን ለማየት እንሞክራለን።
1፡የልግስና ትርጉም፦
ልበ-ቀናነት (ቸርነት) ማለት ሲሆን፦ይህም ጊዜን፣ ገንዘብን፣ እርዳታን ወይም ደግነትን ምንም ዓይነት ምላሽ ሳይጠብቁ ለሌሎች በነጻነት ለመስጠት ወይም ለማካፈል ፈቃደኛ መሆን ማለት ነው።ወይም ባጭሩ ሲገለፅ፡ ለጋስ (ሰጪ) ልብ ማለት ነው። ለምሳሌ፦ ማንንም ሳይጠይቁ ሰውን መርዳት። ያለንን ለተቸገረ ሰው ማካፈል። ማበረታቻን፣ ትኩረትን ወይም ድጋፍን ለሌሎች መስጠት ማለት ሲሆን ። በክርስቲያናዊ እይታ ደግሞ፣ ልበ-ቀናነት (ለጋስነት) ብዙውን ጊዜ የልዑል እግዚአብሔርን የሰጪነት ባህሪ የሚያንጸባርቅ እንደሆነ ይታመናል። ይህን መረዳት በልግስና በመስጠት ገንዘብን በእግዚአብሔር መንግስት ወስጥ በአግባቡ ለመጥቀም የሚያስችል የመጀምሪያው መርህ ነው።
2. እግዚአብሔር የልግስና ሁሉ ምንጭ መሆኑን መርዳት
እግዚአብሔር ከመጀመሪያው ለጋስ ነው። ፍጥረትን፣ ዕለታዊ እንብካቤን/መግቦትን፣ ድኅነትንና ከሁሉም በላይ ደግሞ አንድያ ልጁን ኢየሱስ ክርስቶስን ሰጥቶናል። ዮሐ 3:16 እግዚአብሔር ዓለምን እንዲሁ ስለወደደ አንድያ ልጁን እንደሰጠን ያሰታውሰናል። ስለዚህ የእኛ በልግስና መስጠት ተአምር ሳይሆን በቀላሉ ለጸጋው የምንሰጠው ምላሽ ነው። ለዚህ ነው ስንሰጥ መለከት ማስነፋት የማይገባው። በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ በልግስና በመስጠት ገንዘብን በአግባቡ ለመጠቀም ይህ መርህ ደግሞ ሌላው ወሳኝ እውነት ነው።
3. ልግስና የመንግሥቱ ዕሴት መሆንን መረዳት
ዓለም ያለንን አጥብቀን እንድንይዝ ያስተምረናል። ኢየሱስ ግን ያለንን እንድንሰጥ ያስተምረናል። እርሱ “ስጡ ይሰጣችሁማል” እንዲሁም “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው” ብሎ አስተምሮናል። በልግስና የመስጠት መርህ በኢየሱስ ክርስቶስ አስተምህሮ ላይ የተመሰርተ የመንግስቱ እሴት መሆኑን መገንዘብ በጣም አስፈላጊ ነው። ምክንያቱም በልግስና መስጠት ከሃብታችን/ከገንዘባችን ይልቅ በእግዚአብሔር እንደምንታመን ያሳያልና። ይህን ታላቅ እሴት መጠበቅ ገንዘብን በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ በአግባቡ ለመጠቀም የሚያስችል ታላቅ መንፈሳዊ አቅም የሚሰጥ እውነት ነው።
4. እግዚአብሔር መስጠታችንን ብቻ ሳይሆን ልብን እንደሚመለከት ማወቅ
በማርቆስ 12 ላይ ኢየሱስ ሰዎች በቤተ መቅደስ ውስጥ ስጦታ ሲሰጡ ይመለከት ነበር። አንዲት ደሃ መበለት ሁለት ሳንቲሞችን ሰጠች፤ ኢየሱስም ሌሎች ከተረፋቸው ሲሰጡ እርሷ ግን ከችግሯ ላይ በመስጠቷ ከሌሎች ሁሉ አብልጣ ሰጥታለች በማለት ሰለስጦታዋ ብቻ ሳይሆን ስለሰጠችበት የልብ ሁኔታ መከርላት። እግዚአብሔር በስጦታችን ትልቅነት ብቻ አይደነቅም፤ ነገር ግን እርሱ ከስጦታችን በሰትጀርባ ያለውን መሥዋዕትነት፣ እምነትንና ፍቅርን ይመለከታል። በልግስና በመስጠት ገንዘብን በመንግስቱ ውስጥ ለመጠቅም ይህን መርህ በመስጠት ሂደት ወስጥ ተግባርዊ ማድርግ መቻላችንን የህሊና ምስክርነት በማግኘት ስለ ልባችን አቋም በእግዚአብሔር ዓይን ፊት አርገጠኛ መሆን ያስፈልገናል።
5. በልግስና መጠት ሌሎችን እንደሚባርክ ማወቅ
ምሳሌ 19:17 ለደሆች የሚደረግ ቸርነት በእግዚአብሔር ዘንድ እንደሚታይ ያስተምራል። ዕብ 13:16 መልካም ማድረግንና ማካፈልን እንዳንረሳ ያሳስበናል።ምክንያቱም በልግስና ስንሰጥ ለተቸገሩ ሰዎች በረከት እንሆናለን፣ከሁሉ በላይ የክርስቶስን ልብ እንጸባርቃለን። ይህን መርህ ማወቅና በልግስና በመስጠት ግንዘብን በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ መጠቅም የባስል መንፈሳዊነት ማሳያና እግዚአብሔርን የማክበሪያ መንገድ ነው።
ማጠቃለያ
በልግስና መስጠት የክርስቲያናዊው የሕይወት ስርዓት አካል ነው።ስለዚህ እንደ ክርስቲያን ገንዘብንም ሆነ ሌሎች ነግሮችን በልግስና ስንሰጥ የእግዚአብሔርን ፍቅር ለማግኘት ሳይሆን፤ አስቀድመን ከእርሱ ስለተቀበልነው ፍቅርና ልግስና የለንን ታማኝነት ለማረጋገጥ ነው። ለጋስ አማኝ በልግስና የሚሰጠው “እግዚአብሔር ስጪዬ ነው፣ ስለዚህ የእርሱ መንግሥት ደግሞ ቅድሚያ ሊሰጠው ይግባል” እያለ በልግስና ይሰጣል። ማለትም አምላካችን ለጋስና ሰጪ አምላክ ስለሆነ በልግስና እንሰጣለን። ይህን መርህ ያልጠበቀ መስጠት በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ የሚደርግ መስጠት ስለማይሆን እውነተኛውን በረከት አያመጣምና ይህን መረህ ተከትልን በልግስና እየሰጠን ገንዘብን በመንግስቱ ውስጥ ለእግዚአብሔር ክብርና ለሌሎች ጥቅም እንገልገልበት።
Source: https://cmaeec.com/w...
John 3:16
Whoever believes in him shall not perish but have eternal life.