በዕዳ ባርነት ውስጥ ከሚከት የዚህ ዓለም የገንዝብ አስተዳደር ስራዓት መትረፍ
(የብድር ካርዶችን /Credit cards በጥበብ ማስተዳድር )
ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚያስገነዝቡት፣ ዕዳ ውስጥ መግባት በራሱ ኃጢአት ባይሆንም፣ እግዚአብሔር ለሕዝቡ የሚመርጠው ከሁሉ የተሻለው መንገድ ግን አይደለም። ምክንያቱም ለመበደር ስንመርጥ፣ እምነታችንንና መተማመኛችንን በእግዚአብሔር ላይ ከማድረግ ይልቅ በብድር ካርድ ወይም በአበዳሪው ላይ እያደረግን በመሆናችን ነው። በምሳ 22፥7 ላይ “ሀብታሞች በድሆች ላይ ይገዛሉ፥ ተበዳሪም ለአበዳሪ ባሪያ ነው” እንደሚለው። መበደር በጣም በፍጥነት ወደ ልማድ ወይም ወደ ማያልቅ አዙሪት ሊቀየር ይችላል፤ ይህም ከጌታና እርሱ ከሚሰጠን ነፃነት ይበልጥ ያርቀናል የዕዳ ባሪያዎችምያ ደርገናል።ስለዚህ ወደዚህ አዙሪት ወደሞላው ባርነት ውስጥ ላለመግባትና የገባንም ካለን በቅዱስ ቃሉ መርህ መስረት ነጻ እንድንወጣ የሚከተሉትን እውነቶች ልብ ማለት ይጠቅማል።
የብድር ካርዶች (Credit cards) ምንነት ማወቅ
የብድር ካርዶች በራሳቸው ክፉም ጥሩም አይደሉም። የብድር ካርዶች በገቢያ ስራዓት ውስጥ የገንዘብ መክፈያ አማራጭ መንገዶች ናቸው፤ በራሳቸው ጥሩም ሆነ መጥፎ ነገር ሊያደርጉ አይችሉም። ነገር ግን የእነርሱ አወንታዊ ወይም አሉታዊ ተፅዕኖ የሚወሰነው እኛ ካርዳችንን ለመጠቀም በምንመርጠው ምርጫ ላይ የተመሰርተ በመሆን ነው።
የብድር ካርዶች በጥበብና ራስን በመግዛት መንፈስ ሲያገለግሉ ጠቃሚ ይሆናሉ አልፎ ተርፎም ለገንዘብ ቁጠባ የሚረዱ ሊሆኑ ይችላሉ። አደጋው ግን እኛ ካርዱን ከመጠቀም ይልቅ ካርዱ እኛን መጠቀም ሲጀምር ነው።ነገር ግን በጥበብ ጥቅም ላይ ሲውሉ፣የብድር ካርዶች የተለያዩ ማበረታቻዎችን (rewards) እና ጥቅማጥቅሞችን እንድናገኝ ሊረዱ ይችላሉ።
እንዲያውም የብድር ካርዶች በነፃ ገንዘብ እንደማግኘት ያህል ሊሆኑልን ሁሉ ይችላሉ። እንደ ካርዱ ዓይነት፣ ግዢዎችን በካርዳችን በመፈጸም እና በወሩ መጨረሻ ላይ ሙሉ በሙሉ በመክፈል የጥሬ ገንዘብ ተመላሽ ነጥቦችን (cash back) ፣ የነፃ በረራ ማይሎችን (flyer miles) እና ሌሎች ጥቅማጥቅሞችን ማግኘት ይችላል። ነገር ግን ይህን ለማግኘት መረሳት የሌለበት ነገር ቢኖር በየወሩ ሙሉ ዕዳው መከፈሉን እርግጠኞች መሆናችንን ነው።ምክንያቱም ዕዳን ባለመክፈል ዕዳን ማስተላለፍ (carrying a balance) ፣ ከማንኛውም ማበረታቻ ወይም ጥቅማጥቅም የበለጠ ኪሳራ ሊያስከትል ይችላልና።
ካርዳችንን በተሳሳተ መንገድ ከተጠቀምንበት፣ ራሳችንን በማያልቅ የዕዳ አዙሪት ውስጥ አስገብተን እንዘጋዋለን።ስለዚህ ወደፊት መራመድ ያቅተናል፣ በወለድ ክፍያዎች ገንዘባችንን እንባክናለን። እንዲሁም በሕይወት ለመቆየት ስንል ብቻ ተጨማሪ ዕዳ ውስጥ እንዘፈቃለን።ከዚህ ለመዳንንና ማንኛውንም ዕዳ ከፍሎ ለመጨረስ ግን፣ ዛሬ ላይ ብዙዎቻችን የሌለንን ሥርዓት (discipline) እና መስዋዕትነትን ይጠይቃል።ስለዚህ ከአደጋ የሚጠብቁንን ስርአቶ ች በማወቅና በመጥቅም ጠቢብ ልንሆን ይግባል።የብድር ካርዶችን ምንነት ማወቅም ለዚ ይጠቅማል።
የረጅም ጊዜ ዕዳን ማስወገድ (AVOID LONG-TERM DEBT)
በብድር ካርዳችን ላይ ዕዳዎች ከተከማቹብን፣ ሁሉንም ወጪዎቻችንን ከፍለን እስክንጨርስድረስ ካርዱን መጠቀም ማቆም፤ እንዲሁም ዕዳውን በተቻለ ፍጥነት ለመክፈል በትጋት መስራት ይጠይቃል።ሊኖርብን የሚገባው ብቸኛው የረጅም ጊዜ ዕዳ የቤት መግዣ ብድር (mortgage) ብቻ መሆን አለበት፤ እርሱንም ቢሆን በተቻለ ፍጥነት ከፍሎ ለመጨረስ መጋደል ይኖርብናል።ይህን በማድርግ የሚገኘውን ነጻነት ለመርዳት ዕዳን በመክፈል ነጻነትን የተለማመደችውን የመበለቲቱን ታሪክ ማስብ በቂ ነው 2ኛ ነገ 4:1-7 ። ዕዳችንን ለመክፈል ከደከምን በኋላ የሚኖረውን የሕይወት ምስክርነት ኃይል ታላቅ ነው!
ዕዳን አለማስቀጠል (AVOID A BALANCE)
የብድር ካርድን የምንጠቀመው ለነጥቦች ወይም ለማበረታቻ ጥቅማጥቅሞች ከሆነ፣ በወሩ መጨረሻ ላይ ሙሉ ዕዳውን ከፍለን መጨርስ ይኖርብናል።ቅዱስ ቃሉም በሮሜ 13፥8 “እርስ በርሳችሁ ከመዋደድ በቀር ለማንም ዕዳ አይኑርባችሁ…” ይላል።ስለዚህ ይህን መርህ መከትል መጽሐፍ ቅድሳዊ ነው ማለት ይቻላል።
በተጨማሪም፣ ከወር ወደ ወር ዕዳን ማስተላለፍ ወይም ዕዳን ሳይከፍሉ ማቆየት ለዕዳ ነጥባችን (credit score) ምንም የሚያስገኘው ጥቅም የለም፤ የወለድ ክፍያውም እጅግ ከፍተኛና አስከፊ የመሆን ዕድል አለው። ስለዚህ በደንብ ጥናት በማድረግ ምርጥ የማበረታቻ ፕሮግራም ያለው ካርድ ማግኘታችንን ማረጋገጥ ይኖርብናል።መዝ 37፥21“ኃጢአትኛ ይበደራል መልሶ አይከፍልም፤ ጻድቃን ግን ይቸራል።” በዚህ የቃሉ እውነት መስረት እዳን አለማስቀጠል ጠቢብነት ብቻ ሳይሆን ክርስቲያናዊ ግዴታም ጭምር ነው የሚሆነው።
በጃችን ያለውን መመለስ (REPAY WHAT YOU OWE)
ለክርስቲያኖች፣ የመክሰር አዋጅ ማወጅ (bankruptcy) እንደ አማራጭ ሊታይ አይገባም።ምክንያቱም ስንበደር፣ የተበደርነውን ለመመለስ መሐላ ወይም ቃል እየገባን ስለሆነ ነው። ምንም እንኳን የዓለማዊው ሕግ መክሰርን ማወጅን ተቀባይነት እንደለው አማራጭ ቢቆጥረውም፣ እግዚአብሔር ግን አሁንም ዕዳችንን ሁሉ እንድንከፍልና ቃላችንን እንድንፈጽም ይጠብቅብናል።
ቅዱስ ቃሉም መሀላን ስለመፈጽም እና ታማኝ ስለመሆን በመክ 5፥4-5 እንዲህ በማለት ያሳስባል “ሰነፎች ደስ አያሰኙትምና ለእግዚአብሔር ስእለት በተሳልህ ጊዜ ተፈጽመው ዘንድ አትዘግይ የተሳልኸውን ፈጽመው።” ይህን ሀላፊነት መወጣት ጊዜ ሊወስድ፣ ከባድ ሥራና ብዙ መሥዋዕትነት ሊጠይቅ ይችላል፤ ነገር ግን ዕዳችንን ከፍለን መገላገልና ይህንን ስናደርግ ጌታን ማክበር እንችላለን።
ማጠቃለያ
ገንዘብን በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ በአግባቡ ማስተዳደር ከእያንዳንዱ አማኝ የሚጠብቅ የህይወት ስርዓት ነው።በተመሳሳይ ሁኔታ የዚህ ዓለም ስርዓትም ገንዘብን የሚያስተዳድርበት የራሱ የሆነ ሰርዓት አለው። በተጨማሪ ደግሞ በዚህ ዓለም ስንኖር ከፍተኛ ፈተናና ተግዳሮት ወደ ህይወታችን ከሚመጣባቸው ምክንያቶችና መንገዶች መካከል ገንዘብ ዋናው ነው። ስለዚህ ቅዱስ ቃሉን መሰርት ያደረግ መርህ በመከተል ከዓለም የገንዘብ አስተዳደር ስርዓት በተለይ መንገድ ገንዘብን ለማስተዳደር የሁለቱን ስርዓቶች ልዩነት ማወቅና በቃሉ እውነት መስረት ገንዘብን ለእግዚአብሔር ክብርና ለሰወች ጥቅም ማዋል እንድንችል የብድር ካርዶቻችንን በአግባቡ እንጠቀም።
Source: https://cmaeec.com/w...
John 3:16
Whoever believes in him shall not perish but have eternal life.