የእግዚአብሔር መንግሥት በዕስቴር መጽሐፍ ውስጥ
ዋና ክፍለ-ምንባብ፦ የዕስቴር መጽሐፍ ምዕራፍ 1–10
ዋና ጥቅስ፦ «......ደግሞስ ወደ መንግሥት የመጣሽው እንደዚህ ላለው ጊዜ እንደ ሆነ ማን ያውቃል? » ዕስቴር 4:14
ማዕከላዊ ሐሳብ (ጭብጥ)፦ ስሙ የተሰወረ ቢመስልም እንኳ እግዚአብሔር ንጉሥ ነው።
መግቢያ
የዕስቴር ታሪክ የተፈጸመው ንጉሡ አርጤክስስ ሰፊ በሆነ ምድራዊ መንግሥት ላይ ይገዛ በነበረበት በፋርስ ግዛት ውስጥ ነው። የፋርስ ንጉሥ ኃያል መስሎ ቢታይም፣ መጽሐፉ እውነተኛው ንጉሥ እግዚአብሔር መሆኑን ያሳያል።ስለዚህ እግዚአብሔር ዕስቴርን በቦታዋ አስቀምጧል፣ የሐማንንም ክፉ ዕቅድ አጋልጧል፣ አይሁድንም ከጥፋት ጠብቋል፣ ልቅሶአቸውንም ወደ ደስታ ለውጧል።የዕስቴር መጽሐፍ የእግዚአብሔርን ስም በቀጥታ አይጠቅስም፤ ሆኖም ሙሉ ታሪኩ የእርሱን ልዑላዊ ገዥነት፣መለኮታዊ ጥበቃ እና ለሕዝቡ ያለውን ዓላማ ይገልጣል። የዕስቴር መጽሐፍ የእግዚአብሔር መንግሥት ከማንኛውም ምድራዊ ንጉሥና፣ መንግሥት፣ ሥጋት ወይም ጠላትነት የበለጠ እንደሆነ ያስተምረናል።በዚህ መጸሐፍ እንደምንመለከተው እግዚአብሔር የኪዳኑን ሕዝብ ለመጠበቅና የማዳን ዕቅዱን ለማስፈጸም ከበስተጀርባ ይሠራ እንደነበር እናስተውላለን።ስለዚህ መጸሀፉ ለእግዚአብሔር ሕዝብ ሕይወት ግራ የሚያጋባ ወይም አደገኛ በሚመስልበት ጊዜ በእርግጥ በሁኔታዎች ላይ ሥልጣን ያለው ማን ነው የሚለውን ጥያቄ እንደሚከተለው ይመልስልናል?
1፦ እግዚአብሔር በምድራዊ መንግሥታት ሁሉ ላይ ይገዛል
ዕስቴር 1:1–4፤ ዕስቴር 4:14፤ መዝ 47:7–8፤ ዳን 4:35
ንጉሥ አርጤክስስ ታላቅ ሀብት፣ ሥልጣን እና ግዛት ነበረው፤ ነገር ግን ኃይሉ የተወሰነ ነበር። ሕግጋትን ማውጣት፣ ግብዣዎችን ማድረግ እና ባለሥልጣናትን መሾም ቢችልም የእግዚአብሔርን ዓላማ ግን መቆጣጠር አልቻለም ነበር።በመሆኑም እግዚአብሔር ዕስቴርን በቤተ መንግሥት ውስጥ ለማስቀመጥ የንጉሱን አማካሪዎች እንኳ ሳይቀር ተጠቀመባቸው ምክንያቱም እርሱ በሁሉ ላይ ገዢ ስለሆነ። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ መርዶክዮስ ለዕስቴር የተናገራቸው ቃላት በእግዚአብሔር ንጉሥነትና ገዥነት ላይ የነበረውን እምነት ያሳያሉ «በዚህ ጊዜ አንቺ ዝም ብትዪ፣ ለአይሁድ ርዳታና ትድግና (መዳን) ከሌላ ስፍራ ይመጣላቸዋል» (ዕስቴር 4:14)። መርዶክዮስ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ታማኝ ስለሆነ የእግዚአብሔር ዕቅድ በዕስቴር ላይ ብቻ የተመሠረተ እንዳልሆነ ተረድቶ ነበር። ከዚህ የምንማረው እውነት ምድራዊ ገዢዎች ኃያል መስለው ሊታዩ ይችላሉ፤ እግዚአብሔር ግን ከሁሉ የበላይ የሆነ ንጉሥ ነው። ስለዚህ በምድራዊ ነገስታት ላይ ይሠለጥናል።
ስለዚህ እንድ እግዚአብሔር ህዝብ በሰዎች፣ በመንግሥታት ወይም በሁኔታዎች ፍርሃት ልንጠመድ አይገባም። የሰው ሥልጣን ዓመፀኛ ወይም ከአቅም በላይ መስሎ ሲታይ በእግዚአብሔር ልንታመን ይገባል።እንዲሁም የእግዚአብሔር ግዛት በዓለማዊ ኃይል ፈጽሞ እንደማይወሰን አናስታውስ።እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ ነገር ግን ዛሬም በሕይወታችን ውስጥ እግዚአብሔር አሁንም በሁኔታዎች ላይ ሥልጣን እንዳለው ለማመን አስቸጋሪ የሚያደርጉብን ሁኔታዎች ሊከሰቱ ይችላሉ ሆኖም የእግዚአብሔርን ገዢነት ግን ማስቀርት አይችሉም።
2፦ እግዚአብሔር ከበስተጀርባ/ሳይታይ ይሠራል
ዕስቴር 2:15–18፤3:8–11፤6:1–11፤ ሮሜ 8:28
በዕስቴር መጽሐፍ ውስጥ የእግዚአብሔር ስም በቀጥታ ባይጻፍም፣ እጁ ግን በሁሉም ቦታ ሲሰራ ይታያል።ከዚህ የተነሳ ዕስቴር በትክክለኛው ጊዜ ንግሥት ሆናለች። መርዶክዮስ በንጉሡ ላይ የተሸረበውን ሴራ ደርሶበታል። መርዶክዮስ ሊከበር በሚገባው በእዚያችው ሌሊት ንጉሡ እንቅልፍ አጣ። የሐማ ክፉ ዕቅድ በመጨረሻ በራሱ ላይ ፍርድን አመጣ።የዕስቴር መጽሐፍ እንደሚያስተምረው እግዚአብሔር ዝም ሊል ይችላል፣ ነገር ግን ፈጽሞ ከእኛ አይርቅም። ሕዝቡ ሙሉውን የእርሱን ዕቅድ ማየት ባይችሉም እንኳ፣ እርሱ ሁኔታዎችን ወደ ዓላማው ይመራል። የእግዚአብሔር መንግሥት ብዙውን ጊዜ በጸጥታና ባልተጠበቀ መንገድ ይሰራል ያድጋልም።
እኛ በግልጽ ማየት ባችልንበት ጊዜ እንኳ እግዚአብሔር በሥራ ላይ ነው።ስለዚህ በጸጥታ፣ በዘመናት መዘግየት ወይም በጥርጣሬ ወቅት በእግዚአብሔር እንታመን። የእግዚአብሔርን ታማኝነት ዛሬ በሚታየው ነገር ብቻ አንመዝን። ወደ ኋላ የሕይወታችንን ጉዞ መለስ ብለን በመመልከት የእግዚአብሔርን ጥበቃና መሪነት (ጥንቃቄውን) እናስተውል።ለምሳሌ ዕስቴር ለምን ንግሥት እንደሆነች በመጀመሪያ አላወቀችም ነበር። በኋላ ግን እግዚአብሔር ሕዝቡን ለማዳን በዚያ ቦታ እንዳስቀመጣት ተረዳች።ዛሬ ካላችሁበት ሆናችሁ ወደ ኋላ ስትመለከቱ እንደ አስቴር ሁሉ እግዚአብሔር በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ይመራችሁ እንደነበር በኋላ ላይ ያስተዋላችሁበትን ጊዜ በማስታወስ በአስራሩ መደነቅ ትችላላችሁ? ያ ጊዜ እግዚአብሔር በስውር ይሰራበት የነበር ጊዜ ነውና።
3፦ የመንግሥቱ ሕዝቦች የእግዚአብሔርን ዓላማ በድፍረት ማገልገል አለባቸው
ዕስቴር 4:13–16፤5:1–2፤7:3–6፤ማቴ 6:33
ዕስቴር ስለእግዚአብሔር ሕዝብ ደህንነት ከባድ ምርጫ የምትመርጠበት ጊዜ በህይወቷ ገጥሟት ነበር።ይህም ሳትጠራ ወደ ንጉሡ ፊት በመግባት ልትሞት መወስን ወይ ደግሞ እግዚአብሔር ህዝቡን ለማድን በእርሷ በኩል ለማለፍ ያቀርበላትን ጥሪ ችላ ማለትና የእግዚአብሔር ሕዝብ እንዲጠፉ መፍቀድ ነበር።በዚህ ሁለት ውጥረት ውስጥ ሆና ዕስቴር ጸሎትን፣ ጾምን፣ ድፍረትንና ታዛዥነትን መረጠች። «ብጠፋም እጠፋለሁ» አለች። (ዕስቴር 4:16) የመንግሥቱ ሕዝቦች ለግል ምቾትና፣ደኅንነት ወይም ለግል ስኬት ብቻ አይኖሩም።ነገር ግን እግዚአብሔር ለራሱ ዓላማ በቤተሰብ፣ በሥራ ቦታ፣ በቤተ ክርስቲያን፣ በትምህርት ቤትና በማኅበረሰብ ውስጥ እንዳስቀመጣቸው ይረዳሉ።በዚህ መረዳት መስርት ዕስቴር ሥልጣኗን የተጠቀመችው ራሷን ለመጠበቅ ሳይሆን የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለማገልገል ነበር። የእግዚአብሔር ሕዝቦች ተፅዕኖአቸውን ለፈቃዱ በድፍረት እንዲጠቀሙበት ተጠርተዋል።
እኛም ከዚህ እውነት በመነሳት እግዚአብሔር «አሁን ባለሁበት ቦታ ያስቀመጥከኝ ለምንድን ነው?» ብለን እንጠይቅ። ድምፃችንን ለተጎዱና ለተጨቆኑ ሰዎች መከላከያ አድርገን እንጠቀምበት። ከባድ ውሳኔዎችን ከማድረጋችን በፊት እንጸልይ፤ እንጹም። የእግዚአብሔርን ዓላማ ከግል ምቾታችንና ፍርሃት እናስበልጥ።ደግሞም እንዲህ ብለን እርሳችንን እንጠይቅ እግዚአብሔር አሁን በዚህ ሰዓት እያዘጋጀልኝ ያለው ለምን ሊሆን ይችላል?
ማጠቃለያ
በዕስቴር መጽሐፍ ውስጥ እግዚአብሔር የተሰወረ ቢሆንም ኃያል በሆነው ገዥነቱ አማካይነት ግን የእግዚአብሔርን መንግሥት/አገዛዝ ይገልጣል። የምድር መንግሥታት ይነሣሉ፣ ይወድቃሉም፤ እግዚአብሔር ግን ለዘላለም ንጉሥ ሆኖ ይኖራል። እርሱ ሕዝቡን ይጠብቃል፣ ክፉውን ያፈርሳል፣ አማኞችንም ዓላማውን በድፍረት እንዲያገለግሉ ይጠራል።ምክንያቱም እግዚአብሔር በምድራዊ መንግሥታት ሁሉ ላይ ይገዛልና። እግዚአብሔር ለሕዝቡ ሲል ከበስተጀርባ ይሠራል።ስለዚህ የመንግሥቱ ሕዝቦች የእግዚአብሔርን ዓላማ በድፍረት ያገለግላሉ።
Source: https://cmaeec.com/w...
John 3:16
Whoever believes in him shall not perish but have eternal life.