የእግዚአብሔር መንግሥት በመጽሐፈ ኢዮብ
መግቢያ
መጸሐፍ ኢዮብ የያዘው መሰረታዊ ጭብጥ እንዲህ የሚል ነው። እግዚአብሔር ዓላማው ከአእምሯችን በላይ በሆነበት ጊዜ እንኳን በሰማይ ባለሁኔታ ሁሉ ላይ፣ በመከራ ወይም በስቃይ ሁሉ ላይ፣ በፈጠረው ፍጥረት እና በእያንዳንዱ ህይወት ሁሉ ላይ የሚገዛ ሉዓላዊ ንጉሥ ነው የሚል ነው ። የመጽሐፈ ኢዮብ መጽሐፍ እንደሚያስተምረው እውነተኛ እምነት ማለት የሁሉንም ነገር መልስ ማወቅ ማለት አይደለም፤ ይልቁንም ነገሮች ባልገቡን ጊዜና ሁኔታ ውስጥ ስናልፍ ንጉሡን ማምለክ እና በእርሱ ማመንን መቀጠል አለብን የሚለውን እውነታ አጽንዓዖት መስጠት ነው። ምክንያቱም የእግዚአብሔር አገዛዝ የሚረጋገጠው በእምነት ነው። ይህንንም በኢዮብ መጸሐፍ እንመለከተዋልን።
ዋና ክፍል፦ ኢዮብ 1–2፤ 38–42
ቁልፍ ጥቅስ፦ “ሁሉን ታደርግ ዘንድ ቻይ እንደሆንክ፣ አሳብህም ሊከለከል እንዳይችል አወቅሁ” (ኢዮብ 42:2) ።
1. እግዚአብሔር ከማንኛውም ኃይል በላይ ይገዛል የሚል እምነት ኢዮብ 1:6-12
መጽሐፈ ኢዮብ የሚጀመረው መላእክት በእግዚአብሔር ፊት በሚቀርቡበት ጊዜ ሰይጣን ደግሞ በእግዚአብሔር ፊት ተጠያቂ የሆነበትን የሰማይ ትዕይንት በማቅረብ ነው።በዚህ ትዕይንት ውስጥ እንደምንመለከትው ሰይጣን ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ኢዮብን መነካት አልቻልም ወይም አይችልምም፤ ይህም የሚያረጋግጥልን ነገር ቢኖር ክፋት በርግጥ ያለ ቢሆንም እንኳ ከእግዚአብሔር ስልጣንና ግዛት ውጭ ፈጽሞ ነፃ አለመሆኑን ነው። ከዚህ አንጻር በዚህ ትዕይንት ውስጥ ስለእግዚአብሔር መንግስት ቢያንስ ሶስት ነግሮችን ማየት እንችላለን።
• እግዚአብሔር በሰማይ ንጉሥ ነው፣ስለዚህ የሰማይ ፍጥረታት ሁሉ ለእርሱ መልስ ይሰጣሉ ይህን አለማድረግ አይችሉም።
• ሰይጣን ከእግዚአብሔር ጋር እኩል አይደለም፤ እንቅስቃሴው በእግዚአብሔር ሥልጣን የተገደበ ነው።
• የሰው ልጅ ስቃይ ወይም የሚያልፍበት መከራ ምስጢር ሊሆንበት ይችላል፣ ነገር ግን ከእግዚአብሔር ዕውቀት ወይም ግዛት ውጭ አይደለም።
ተግባራዊ መመሪያ፦
ስለዚህ ህይወት ከቁጥጥር ውጭ እንደሆነች ሲሰማን፣ እግዚአብሔር ዙፋኑን እንዳላጣና አገዛዙ የማይናወጥ መሆኑን እንመን። ውጊያውን ላንረዳው እንችላለን፣ ነገር ግን ሙሉውን ታሪክ የሚያየውን ንጉሱን እግዚአብሔርን ማመን እንችላለን ይገባናልም።እግዚአብሔር ከማንኛውም ኀይል በላይ ይገዛልና።
2. የመንግሥቱ እምነት በስቃይና በመከርም ውስጥ ንጉሱን ያመልካል ኢዮብ 2:1-10
ሰይጣን በእግዚአብሔር ፈቃድ መሰርት በኢዮብ ጤንነትና ንብረት ላይ ጥፋትን አድርሶአል። ኢዮብ ንብረቱንና ልጆቹን ካጣ በኋላ እጅግ አዘነ ይህም ተፈጥሮአዊ ነው፣ በሚስቱም እግዚአብሔርን ስድቦ/ረግሞ እንዲሞት ምክረ ሀሳብ ተሰጥቶ ነበር ነገር ግን ኢዮብ ተደፍቶ ሰገደ፤ የእግዚአብሔርንም ስም ባረከ። ቅዱስ ቃሉ የኢዮብን ምላሽ በዚህ መልኩ ዘግቦልናል ኢዮብ እግዚአብሔርን በንግግሩ አልበደለም ወይም አልከሰሰም ይላል።ይህም የሚከተሉትን እውነቶችን ስለ እግዚአብሔር መንግስት እንድናስተውል ያደርገናል፦
• የመንግሥቱ ዜጎች የሥቃይን ወይም የመከራን መኖር አይካዱም፤ ኢዮብ አልቀሰ፣ ልብሱን ቀደደ፣ አዘነይኅም ተፈጥሮአዊ ነው።ምክንያቱም እምነት ተጨባጭ እውነትን መካድ አይደልምና።
• የመንግሥቱ እምነት ስቃይን ወይም መከራን እግዚአብሔርን ላለማምለክ እንደ ምክንያት አይጠቀምም።በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ አምልኮን ይቀጥላል።
• የመንግስቱ እምነት በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ አምልኮ እግዚአብሔር በሚሰጥበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ህይወት ከባድ በሚሆንበት ጊዜም አምልኮ የተገባ መሆኑን ያውጃል።
ተግባራዊ መመሪያ፦
የእምነት ፈተና እግዚአብሔርን በበረከት ውስጥ አለማመስገን ብቻ ሳይሆን፣ በመከራና በችግር ውስጥም ንጉሱን የምናከብረው መሆናችን የሚያረጋግጥ ነው።ይህ ሲሆን እንደ ኢዮብ፣ የእግዚአብሔርን ቸርነት አጥብቀን እየያዝን እውነተኛ ሐዘናችንን ወደ እግዚአብሔር ማቅረብ እንችላለን።ምክንያቱም የመንግስቱ እምነት በስቃይና በመከራም ውስጥ ንጉሱን ያመልካልና።
3. እምነት በመንግሥቱ ውስጥ ትሕትናንና መታደስን ያመጣል ኢዮብ 38- 42
እግዚአብሔር ለኢዮብ ከዐውሎ ነፋስ ውስጥ በተናገረው ጊዜ፣ ለእያንዳንዱ ሁነቶች ሙሉ ማብራሪያ አልሰጠውም። ይልቁንም ጥበቡን፣ ኃይሉን እና በፍጥረት ላይ ያለውን ገዥነት ገለጠለት እንጂ፤ ኢዮብም ይህን መገለጥ ሲያገኝ እንዲህ አለ “ሁሉን ታደርግ ዘንድ ቻይ እንደሆንክ አሳብህም ይከለከል ዘንድ ከቶ እንዳይችል አወቅሁ” ብሎ መልስ ሰጠ፤ ከዚህ መገለጥበኋ ኢዮብ እግዚአብሔር ጋር በእምነት ጥልቅ ወደሆነ ግላዊ ህብረት ተሸጋገረ።ይህም፦
• የእግዚአብሔር ጥበብ ከሰው ልጅ አእምሮ በላይ መሆነን የሚያረጋግጥ ነው።
• የእግዚአብሔር ዓላማ በስቃይ፣ በሰይጣን ወይም በሰው ልጅ ድክመት ሊሸነፍ ወይም ሊሻር እንድማይችህ ያረጋግጣል።
• እግዚአብሔር የሐሰት ትምህርትን ያርማል፦ የኢዮብን ወዳጆች ገሠጻቸው፤ የኢዮብንም ጸሎት ስለ እነርሱ ተቀበለ።
• እግዚአብሔር ኢዮብን ነገሩን ሁሉ አደሰለት፤ ይህም እርሱ ጻድቅ፣ ሩህሩህ እና ታማኝ ሆኖ እንደሚኖር በርግጥ ያሳያል።
ተግባራዊ መመሪያ፦
ለእግዚአብሔር ከመገዛታችን በፊት ሁሉንም ነገር መረዳት አያስፈልገንም።ምክንያቱም የመንግሥቱ እምነት ምላሽ ሁሉን ማወቅ አለብኝ የሚል ትዕቢት ሳይሆን ሁሉንታደርግ ዘንድ ቻይ እንደሆንክ ሀሳብህም ይከለከል ዘንድ ከቶ እንደማይቻል አወቅሁ የሚል ትሕትና ነው “ጌታ ሆይ፣ አንተ እግዚአብሔር ነህ፤ እኔ አይደለሁም። በጥበብህ፣ በኃይልህ እና በዓላማህ አምናለሁ።” ማለት ነው።ምክንያቱም እንዲህ ያለው እምነት ትህትናንና መታደስን ይመጣልና።
ማጠቃለያ
የመጽሐፈ ኢዮብ መልእክት አማኞች ለስቃያቸው ሁልጊዜ ፈጣን ማብራሪያ ያገኛሉ የሚል አይደለም። ነገር ግን አማኞች በማንኛውን ሁኔታ ውስጥ ሲያልፉ እግዚአብሔር ንጉሥ ሆኖ ይኖራል የሚል ነው። ስለዚህ ዛሬም በተለያየ መከራ ውስጥ ስለሚያልፉ እውነተኝ አማኞች ሁሉ እርሱ ከሰይጣን በላይ ይገዛል፣ ሕዝቡን በስቃይ ውስጥ ይደግፋል፣ አገልጋዮቹን ወደ ጥልቅ የራሱ ዕውቀት ያመጣል። የኢዮብ የመጨረሻ የእምነት ምስክርነትም የሚያረጋግጠው ይህንን እውነት ነው። ስለዚህ የእግዚአብሔርን ዕቅድ ሊቆም ማንምና ማንም እንደማይችል እንመን።
Source: https://cmaeec.com/w...
John 3:16
Whoever believes in him shall not perish but have eternal life.