መግቢያ
ዋና ጥቅስ፦ ምሳሌ 1:7 — “እግዚአብሔርን መፍራት የእውቀት መጀመሪያ ነው…”
ምንም እንኳን “የእግዚአብሔር መንግሥት” የሚለው ቀጥተኛ ሐረግ በመጽሐፈ ምሳሌ ውስጥ እንደ ዋና መገለጫ ባይገኝም፣ ነገር ግን መጽሐፉ በእግዚአብሔር ግዛት ስር ያለ ሕይወት ምን እንደሚመስል አጥብቆ ያስተምራል።በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የእግዚአብሔር መንግሥት ማለት የእርሱ ግዛት ልዑላዊ ሥልጣኑ፣ ጥበቡ፣ ጽድቁ እና ዓላማዎቹ በዓለም ውስጥ የሚሰሩበት ማለት ነው። ከዚህ እውነት አንጻር መጽሐፈ ምሳሌ ሰዎች በእግዚአብሔር አገዛዝ ስር እንደ ዜጋ እንዴት በጥበብ መኖር እንዳለባቸው በስፋት ያስተምራል። ከዚህ ሰፊ ትምህርት ውስጥ የእግዚአብሔር መንግሥት ለንጉሡ በሚደረግ አክብሮት ይጀምራል፣ የእግዚአብሔር መንግሥት በእርሱ ጥበብ ይመራል ፣የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅንና ፍትሕን ያፈራል፣የእግዚአብሔር መንግሥት ትሕትናን ይፈልጋል፣ ትዕቢትንም ይቃወማል የሚለውን እንመለከታልን።
1. የእግዚአብሔር መንግሥት ለንጉሡ በሚደረግ አክብሮት ይጀምራል
የእግዚአብሔር መንግሥት ሕይወት የመጀመሪያው መርህ እግዚአብሔርን መፍራት ነው። ይህም እግዚአብሔርን መፍራት ማለት መሸበር ማለት ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም እርሱን ማክበር፣ በእርሱ መታመን፣ ለእርሱ መገዛት እና በሕይወት አቅጣጫ ሁሉ ላይ የበላይ ሥልጣን እንዳለው መቀበል ማለት ነው።መጽሐፈ ምሳሌ እግዚአብሔርን ወደ ጎን በማለት ማንም ሰው በእውነት ጥበበኛ ሊሆን እንደማይችል ያስተምራል።በመጽሐፈ ምሳሌ ትምህርት፣ ልምድ፣ ገንዘብ፣ ተፅዕኖ እና ብልህነት ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ትክክለኛ ግንኙነት ሊተኩ አይችሉም የሚል ነው።በአንጻሩ ግን “እግዚአብሔርን መፍራት” የጥበብ እና የጽድቅ ሕይወት መሠረት መሆኑ በመጽሐፈ ምሳሌ ውስጥ በተደጋጋሚ ተጠቅሷል (ምሳሌ 1:7፤ 9:10፤ 15:33) ።
ተግባራዊ ተዛምዶ፦
ከዚህ እውነት አንጻር የመንግሥቱ ዜጋ እያንዳንዱን ቀን የሚጀምረው “ጌታ ሆይ፣ ደስ የሚያሰኝህ ምንድን ነው?” ብሎ በመጠየቅ ነው።እኛም እንደ መንግስቱ ዜጋ በቤተሰባችን፣ በንግግራችን፣በውሳኔዎቻችን፣በሥራችን፣በፋይናሳችን እና በግንኙነቶቻችን ውስጥ የእግዚአብሔርን ፈቃድ መፈለግ አለብን ።መጽሐፈ ምሳሌ ጥበብን እግዚአብሔርን ከማክበር ተለይቶ የማይታይ አድርጎ ያቀርበዋል፤ ስለዚህ አማኞችን እግዚአብሔር በፈጠረው እና በሚገዛው ዓለም ውስጥ በኃላፊነት ስሜት እንዲኖሩ ይጠራቸዋል።
“የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው።” — ምሳሌ 9:10
2. የእግዚአብሔር መንግሥት በእርሱ ጥበብ ይመራል
አንድ መንግሥት ሕጎች፣ እሴቶች እና ነገሮችን የሚያደርግበት መንገዶች አሉት። ከዚህ እውነት አንጽር በመጽሐፈ ምሳሌ ውስጥ የእግዚአብሔር ጥበብ ለሰው ልጅ ሕይወት ትክክለኛውን መንገድ ያሳያል። እግዚአብሔር ዓለምን በጥበብ፣ በሥርዓት እና በዓላማ ፈጠረ፤ ስለዚህ ጥበብ ማለት በሰው ትዕቢት ወይም በግል ፍላጎት ከመመራት ይልቅ በእግዚአብሔር እቅድ መሠረት መኖርን መማር ነው ። (ምሳ 3:19–20፤ 8:22–31) ሰዎች እቅድ ሊያቅዱ ይችላሉ፣ ነገር ግን የመጨረሻው ውሳኔና ስልጣን ግን የእግዚአብሔር ነው። “ሰው በልብ መንገዱን ያቅዳል፤ እግዚአብሔር ግን እርምጃውን ይወስንለታል።” (ምሳ 16:9) ይህ እውነት የእግዚአብሔር መንግሥት ከእቅዶቻችን እንደሚበልጥ ያሳስበናል። ስለዚህ እንደመንግስቱ ዜጎች ሁሉንም የህይወት ዕቅድ በኃላፊነት ስሜት ማቀድ አለብን፣ እንዲሁም እቅዶቻችንን ለጌታ ማስረከብ ይገባናል። (ምሳ16:3) “የምታደርገውን ሁሉ ለእግዚአብሔር አደራ ስጥ፣ እቅድህም ሁሉ ይሳካልሀል” ይላልና።
ተግባራዊ ተዛምዶ፦
በህይወታችን ውስጥ አስፈላጊ ውሳኔ ከማድረጋችን በፊት በጸሎት፣ በቅዱሳት መጻሕፍት እውቀት፣ በጥበበ ምክር እና በትሕትና መንፈሳዊ ጥበብን እንፈልግ። በሕይወታችን ላይ በእግዚአብሔር ምትክ ስሜታችን፣ ጫናዎቻችን ወይም ምኞታችን እንዲገዛን አንፍቀድ።ከዚህ እውነት አንጻር መጽሐፈ ምሳሌ እግዚአብሔርን የሰውን እርምጃዎች የሚያቀና እና በሰው እቅዶች መካከል እንኳ ዓላማውን የሚያስፈጽም አድርጎ ወጥ በሆነ መንገድ ያቀርበዋል።
3. የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅንና ፍትሕን ያፈራል
የእግዚአብሔር መንግሥት ስለ ግል እምነታችን ብቻ አይደለም፤ነገር ግን ከሌሎች ሰዎች ጋር በሚኖረን የግንኙነት መንገድ ላይም ተፅዕኖ ያሳድራል። መጽሐፈ ምሳሌ ጥበብን ከታማኝነት፣ ከፍትሕ፣ ከልግስና፣ ከትሕትና፣ ከታማኝ ንግግር እና ለድሆች ከሚያስፈልግ እንክብካቤ ጋር በተደጋጋሚ ያገናኛል። “ከመሥዋዕት ይልቅ ጽድቅንና ፍትሕን ማድረግ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት አለው።” ምሳሌ 21:3 “ለድሀ ቸርነት የሚያደርግ ለእግዚአብሔር ያበድራል፤ በጎነቱንም መልሶ ይከፍለዋል።” ምሳሌ 19:17 “አታላይበእግዚአብሔር የተጭበረበረን ሚዛንን ይጸየፋል፤ ትክክለኛ ሚዛን/ መልኪያ ግን ደስ ያሰኘዋል።” ምሳሌ 11:1 እነዚህ ጥቅሶች እግዚአብሔር ስለ ንግድ፣ ስለ መሪነት፣ ስለ ቤተሰብ ሕይወት፣ ስለ ማህበረሰብ ሕይወት እና ስለ ተጎጂዎች አያያዝ እንደሚያስብ ያሳያሉ።ስለዚህ አንድ የእግዚአብሔር መንግስት ዜጋ ወይም አማኝ ሌሎችን እያታለለ፣ ድሆችን እያስጨነቀ፣ ሐሰትን እየተናገረ ወይም በዓመፅ እየሠራ ንጉሡን እግዚአብሔርን አከብራለሁ ሊል አይችልም።
ተግባራዊ ተዛምዶ፦
በመንግሥቱ ሥር መኖር ማለት ማንም በማያየን ጊዜ ታማኝ መሆን፣ በሥራችን ፍትሐዊ መሆን፣አቅርቦት ለሚያስፈልጋችው ሰወች ደግ መሆን እና በቃላችን ጠንቃቃ መሆን ማለት ነው። በቤታችን፣ በቤተክርስቲያን፣ በትምህርት ቤት፣ በሥራ ቦታ እና በማህበረሰብ ውስጥ የእግዚአብሔር ሕዝብ የንጉሣቸውን ጠባይ ማንጸባረቅ መቻል አለባቸው።ለዚህ ነው መጽሐፈ ምሳሌ የእግዚአብሔርን ጥበብ በሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎች ብቻ ሳይወሰን በቤቶቻችን፣ በማህበረሰቦቻችን፣ በንግድ ተቋሞቻችን እና በማህበራዊ ግንኙነቶቻችን ውስጥ በሰፊው እንደሚተገበር የሚያሳስበን።
4. የእግዚአብሔር መንግሥት ትሕትናን ይፈልጋል፣ ትዕቢትንም ይቃወማል
ትዕቢት የመንግሥቱ ሕይወት ትልቁ ጠላት ነው፤ ምክንያቱም ትዕቢት ራስን በዙፋን ላይ ለማስቀመጥ ይሞክራልና። መጽሐፈ ምሳሌ ትዕቢተኛ ሰው በእግዚአብሔር ከመታመን ይልቅ በራሱ ጥበብ፣ በራሱ ኃይል እና በራሱ ስኬት እንደሚታመን ያስጠነቅቃል። “ትዕቢት ጥፋትን፣ ኩሩ መንፈስም ውድቀትን ይቀድማል።” “ትዕቢት ጥፋትን የእብሪት መንፈስም ውድቀትን ትቀድማለች” (ምሳ 16:18) ፤ በትሑታን ዘንድ ግን ጥበብ ትገኛለች።” ምሳሌ 11:2 ትሕትና ደካማነት አይደለም። እግዚአብሔር አምላክ መሆኑን እና እኛ አምላክ አለመሆናችንን የመቀበል ጥንካሬ ነው እንጂ።ትህትና ማለት ለመማር ዝግጁ መሆን፣ ለመጸጸት ፈቃደኛ መሆን፣ እርማትን ለመቀበል ዝግጁ መሆን እና ለእግዚአብሔር ክብር ለመስጠት የተዘጋጁ መሆን ነው።
ተግባራዊ ተዛምዶ፦
በእግዚአብሔር መንግሥት ግዛት ስር ለመኖር ትዕቢታችንን ማስወገድ አለብን። እርማትን መቀበል፣ ሌሎችን ይቅር ማለት፣ ስህተታችንን ማመን እና በራሳችን ከመታመን ይልቅ በእግዚአብሔር ላይ መደገፍ አለብን።ከዚህ እውነት አንጻር መጽሐፈ ምሳሌ የጥበብ ባህልን በተመለከተ የሚያስተምረን እውነት እግዚአብሔር ላዘጋጀው የሕይወት ሥርዓት መታዘዝ በዋናነት የልብ ጉዳይ እንጂ የውጭ ባህሪ ብቻ አለመሆኑን የሚያጎላ መጸሐፍ ነው።
ማጠቃለያ
የመጽሐፈ ምሳሌ መልእክት እግዚአብሔር እውነተኛው ንጉሥ እንደሆነ እና በጥበብ መኖር ማለት እያንዳንዱን የሕይወት ዘርፍ ለእርሱ ስልጣን ማስገዛት ማለት እንደሆነ ማስገንዘብ ነው። ይህም ንጉሡን ፍሩ ፣ የንጉሡን ጥበብ ተከተሉ ፣ የንጉሡን ጽድቅ ተለማመዱ፣ በንጉሡ ፊት በትሕትና ተመላለሱ በመንግስቱ ውስጥ እግዚአብሔርን መፍራት ተግባርዊ ህይወት አስፈላጊ መሆኑን አጻንኦት በመስጠት ያስተምራል።ምክንያቱም የእግዚአብሔር መንግሥት የሚታየው ሰዎች እግዚአብሔርን ሲፈሩ፣ ጥበቡን ሲከተሉ፣ ጽድቅን ሲለማመዱ እና በትሕትና ሲመላለሱ ነው።
Source: https://cmaeec.com/w...
John 3:16
Whoever believes in him shall not perish but have eternal life.