የእግዚአብሔር መንግሥት በመኃልየ መኃልይ መጽሐፍ ውስጥ
ፍቅር፣ ታማኝነትና የመንግሥቱ ባሕል
ዋና የንባብ ክፍል፦ መኃልየ መኃልይ 8፥6–7
ዓላማ
አማኞች በትዳርና በግንኙነታቸው ውስጥ የፍቅርን፣ የታማኝነትንና የቁርጠኝነትን እሴቶች በመኖር የእግዚአብሔርን ጽድቅና ቅድስና እንዲያንጸባርቁ ማበረታታት።
ዋና መልእክት
የመኃልየ መኃልይ መጸሐፍ በዋነኝነት ስለ ባልና ሚስት ፍቅር የሚናገር መጽሐፍ ቢሆንም፣ ከእግዚአብሔር መንግሥት አንጻር ስናጠናው ፍቅር፣ ታማኝነት፣ ቅድስና እና የቃል ኪዳን ግንኙነት በሕይወታችን ውስጥ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆኑ እንማራለን።ሆኖም መኃልየ መኃልይን ከመንግሥቱ አንጻር ስናብራራ፣ የመጽሐፉን ቀጥተኛ ትርጉም ማለትም በባልና በሚስት መካከል ያለውን የፍቅር ሀሳብ መጠበቅ አለብን። ከዚያም የመንግሥቱን መርሆች ከሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ጋር በማያያዝ ማብራራት ይገባል።
መግቢያ
የእግዚአብሔር መንግሥት ማለት እግዚአብሔር እንደ ንጉሥ የሚገዛበትና ፈቃዱ የሚፈጸምበት የግዛት አገዛዝ ነው። የመንግሥቱ ባሕል በአማኞች አስተሳሰብ፣ በባሕርይ፣ በቤተሰብና በግንኙነቶቻቸው ውስጥ መታየት አለበት። መኃልየ መኃልይ የፍቅርን ውበት፣ የግንኙነትን ደስታና የታማኝነትን ክብር የሚገልጽ መጽሐፍ ነው። ስለዚህ ከዚህ መጽሐፍ በመነሳት የእግዚአብሔር መንግሥት በፍቅራችንና በግንኙነታችን ውስጥ እንዴት መገለጥ እንዳለበት መማር እንችላለን ከዚህ እይታ አንጻር ሦስት ዋና ነጥቦችን እንመለከታለን።
1፡በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ፍቅር የከበረ ስጦታ ነው
መኃልየ መኃልይ 8፥6 “ፍቅር እንደ ሞት ብርቱ ነው።” እግዚአብሔር ሰውን ከፈጠረ በኋላ በግንኙነት እንዲኖር ፈቃዱ ነበር። በዘፍጥረት 2፥18 ላይ፣ ሰው ብቻውን መኖሩ መልካም እንዳልሆነ እግዚአብሔር ተናግሯል። ይህም በትዳር ውስጥ ያለው የፍቅርና የአጋርነት ግንኙነት በእግዚአብሔር ዕቅድ ውስጥ ፍቅር ምን ያህል ቦታ እንዳለው ያሳያል።ከዚህ እውነት አንጻር ስንመለከተው መኃልየ መኃልይ የባልና የሚስትን ፍቅር እንደ ውብ፣ የተከበረና ጠንካራ ግንኙነት ያቀርባል። ከመንግሥቱ አንጻር ደግሞ ይህ ፍቅር በራስ ወዳድነት ሳይሆን በክብር፣ በመረዳዳትና በመተማመን መገለጥ እንዳለበት ያሳስብናል።
ግብረ መልስ እንደ መንግስቱ ዜጎች ባልና ሚስት እርስ በርሳቸው መከባበር አለባቸው።እንዲሁም ፍቅራችንን በቃል ብቻ ሳይሆን በተግባር መግለጽ አለብን። የመንግሥቱ ባሕል በቤተሰባችን ውስጥ መታየት አለበት። 1ኛቆሮ13፥4–7።ምክንያቱም በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ ፍቅር የሚናገሩት ቃል ብቻ ሳይሆን፣ በባሕርያችንና በድርጊታችን የሚገለጥ ሕይወት ነውና።
2. የመንግሥቱ ፍቅር ታማኝነትንና ቁርጠኝነትን ይጠይቃል
መኃልየ መኃልይ 6፥3 “እኔ የውዴ ነኝ፥ ውዴም የእኔ ነው።” ይህ ጥቅስ በፍቅር ግንኙነት ውስጥ ያለውን የመተማመንና የመሰጠት ስሜት ያሳያል። እውነተኛ ፍቅር በስሜት ብቻ አይመሠረትም፤ነገር ግን በታማኝነት፣ በቁርጠኝነትና በተግባርም ይገለጣል።የእግዚአብሔር መንግሥት የቃል ኪዳን ታማኝነትን ከፍ አድርጎ ያስተምራል። በትዳር ውስጥ ታማኝነት ማለት በቃል፣ በሐሳብና በተግባር ለትዳር አጋራችን ታማኝ መሆን ነው። ይህን የታማኝነት መርህ ከእግዚአብሔር ጋር ባለን ግንኙነትም ውስጥ አስፈላጊ እንድሆን በዚህ መጸሐፍ ውስጥ እንማራለን። እግዚአብሔር ለቃል ኪዳኑ ታማኝ ነው፤ እኛም ለእርሱ በእምነትና በታዛዥነት መኖር አለብን።
ግብረ መልስ በትዳር ውስጥ ታማኝነታችንን ጠብቅ። ቃል የገባኸውን ነገር በታማኝነት እንፈጽም።ከሰውች ጋር ባለን ግንኙነት ውስጥ እውነተኛነትንና መተማመንን አጠናክር።በእግዚአብሔር ፊት የምትንናገረውና የምናደርገው ነገር አንድ እንዲሆን ጥረት አድርግ። ኤፌ 5፥25፤ ሉቃስ 16፥10።ላይ እንደምንመለከተው የመንግሥቱ ፍቅር በስሜት ብቻ የሚኖር ሳይሆን፣ በታማኝነትና በቁርጠኝነት የሚጸና ፍቅር ነውና።
3. የእውነተኛ ፍቅር ዋጋ በገንዘብ ሊገዛ አይችልም
መኃልየ መኃልይ 8፥7 “ብዙ ውኃ ፍቅርን ሊያጠፋ አይችልም፥ ወንዞችም ሊያጥለቀልቁት አይችሉም።” ይህ ጥቅስ እውነተኛ ፍቅር በችግርና በመከራ መካከል ያለውን ጽናት ይገልጻል። በተጨማሪም ፍቅር እንደ ሸቀጥ በገንዘብ ሊገዛ እንደማይችል ያስተምራል። በዓለም ውስጥ ሰዎች ገንዘብን፣ ሥልጣንንና ውጫዊ ውበትን ከፍ አድርገው ሊመለከቱ ይችላሉ። ነገር ግን በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ የሰው ዋጋ በገንዘቡ ወይም በማኅበራዊ ደረጃው አይለካም።በእግዚአብሔር መንግስት ውስጥ ፍቅር በገንዘብ ሳይሆን በቅንነት፣ በመስጠትና በታማኝነት ይገለጣል። ይህ ማለት በትዳር ውስጥም ሆነ ከሌሎች ጋር ባልን ግንኝነት ችግር ፈጽሞ አይኖርም ማለት አይደለም። ይልቁንም በችግር ጊዜ መግባባትን፣ ይቅርታን፣ ትዕግሥትንና ታማኝነትን መለማመድ እንዳለብን ያሳስበናል። ሆኖም ፍቅር ማለት በደልን መቀበል ወይም አደገኛ ሁኔታን በዝምታ መታገስ አይደለም።
ግብረ መልስ ግንኙነታችንን በገንዘብ ብቻ አንለካ። በችግር ጊዜ በትዕግሥትና በጥበብ መፍትሔ እንፈልግ። ይቅርታንና መግባባትን እንለማመድ። በቤተሰባችንና በጉባኤህ ውስጥ ፍቅርን በተግባር እንግለጽ።1ኛ ቆሮ 13፥7።ምክንያቱም በእግዚአብሔር መንግሥት ውስጥ እውነተኛ ፍቅር በገንዘብ አይገዛም፤ በችግር ጊዜም በጥበብ፣ በታማኝነትና በቁርጠኝነት መገለጥ አለበት።
Source: https://cmaeec.com/w...
John 3:16
Whoever believes in him shall not perish but have eternal life.