6 ሳምንት:- የባቢሎን ግንብ እና የሰው ኩራት
ዘፍጥረት 11፡1-9
ሥነ-መለኮታዊ ጭብጦች፡- የሰው ኩራትና መለኮታዊ ሉዓላዊነት
የክፍለ ምንባቡ ዋናው ሃሳብ፦ የሰው ራስን ከፍ ከፍ ማድረግ ወደ ግራ መጋባት እና መበታተን ያመራል፣ይሁን እንጂ እግዚአብሔር በሰው ልጅ ታሪክ ላይ ሉዓላዊ እንድሆነ ይኖራል።
መግቢያ
ግራ መጋባት ወደተባለና ሁላችንንም የሚያጋጠመንን ነገር ወደሚያብራራ ታሪክ ደርሰናል ሰዎች እርስ በርሳቸው የማይግባቡበት ምክንያት ምንድን ነው? ለምንድነው የሰው ልጅ ምኞት ከአንድነት ይልቅ በመከፋፈል የሚያበቃው? እግዚአብሔር ሲቀር ታላላቅ እቅዶች ለምን ይወድቃሉ? የሚሉ ጥያቄዎችን የምንጠይቅባቸውን ጉዳዮች ዘፍጥረት 11 በባቢሎን ግንብ ታሪክ ይመልስልናል። ይህ ታሪክ ስለ ጡቦች እና ቋንቋዎች የሚዘግብ ጥንታዊ ታሪክ ብቻ አይደለም ይልቁንም በሰው ልብ ውስጥ የተቀመጠን ኩራትና አስከትሎቱን የሚያሳይ መስታወት ነው።
በባቤል የሰው ልጅ ወደ ታላቅነት ወይም እራሱን ያለእግዚአብሔር ከፍ ከፍ የሚያደርግበትን መንገዱን ለመገንባት የሞከረበት ታሪክ ነው።ለዚህ የሰው ልጅ ሙከራ ደግሞ እግዚአብሔር ምላሽ የሰጠው በድንጋጤና በፍርሃት ሳይሆን በሉዓላዊ ሥልጣን ነው። ዛሬ የምንማረው ነገር ቢኖር የሰው ልጅ ራሱን ከፍ ከፍ ሲያደርግ እግዚአብሔር ጣልቃ የሚገባው ሰውን ለማፍረስ ሳይሆን ሰው ትሁት እንዲሆን ለማድርግና ታሪክን ወደ ፈቃዱ አቅጣጫ ለማዞር ነው።
I. የሰው ልጅ የአንድነት ኃይል (ዘፍ 11፡1-2)
“ምድርም ሁሉ አንድ ቋንቋና አንድ ቃል ነበራት። በመጀመሪያ ሲታይ ይህ ቃል የሚያምር ይመስላል። አንድ ቋንቋ፣ አንድ ህዝብ፣አጠቃላይ አንድነት፣ የሚለው ደስ የሚያሰኝ ገለጣ ነው። ከባቤል ታሪክ እንደምንማርው ግን አንድነት በራሱ ጥሩ አይደለም። ምክንያቱም አንድነት ጽድቅን ወይም ዓመፅን ሊያገለግል ይችላልና። ከጥፋት ውሀ በኋላ በምድር ላይ የበዙት ህዝቦች ወደ ምስራቅ ተሰደው አብረው ሰፈሩ። ይህ ገለጣ በዘፍጥረት ውስጥ ቀደም ባሉት ምዕራፎች እንደተመለክትነው ወደ ምሥራቅ መሄድ ብዙውን ጊዜ ከእግዚአብሔር መገኘት መራቅን ያሳያል (ዘፍ 3:16)። በስውር የተደረገ ፣ነገር ግን ሆን ተብሎ የተደረገ መሸሽ። ይህ እውነት የሚየሳስበን ነገር አንድነት ሁሉ አምላካዊ አይደለም የሚለውን ነው። ትብብር ሁሉ እግዚአብሔርን አያከብርም። ለእግዚአብሔር ያልተገዛ አንድነት አደገኛ ሊሆን ይችላል የሚለውን እውነት ነው።
II. የሰው ልጅ ኩራት (ዘፍ 11፡3-4)
" ኑ ለእኛ ከተማና ራሱ ወደ ሰማይ የሚደርስ ግንብ እንሥራ፥......... ስማችንንም እናስጠራ አሉ” ። ይህ ቁጥር ሦስት የትዕቢት መግለጫዎችን ያሳያል፡-
1. በራስ መተማመን “ኑ፣ እንሂድ…” ምንም ጸሎት የለም፣በእግዚአብሔር ላይ መደገፍ የለም፣ ስለ እግዚአብሔር ምንም የሚጥቀስ ነገር የለም ወይም እግዚአብሔርን እውቅና መንፈግ በግልጽ የታየበት ነው “ኑ እንሂድ” የሚለው ቃል። የሰው ልጅ በወቅቱ የነበርው ቴክኖሎጂ እና ትብብር ለእግዚአብሔር መታዘዝን ሊተካ እንደሚችል ያምን ነበር።
2. ራስን ከፍ ከፍ ማድረግ፦ "ስማችንን እናስጠራው" ይህ የትዕቢት አስኳል ነው ከእግዚአብሔር ይልቅ ለራስ ስምና ክብር መኖር።እግዚአብሔር የአብርሃምን ስም ታላቅ እንደሚያደርገው አስቀድሞ ቃል ገብቷል (ዘፍ 12) ።ነገር ግን ባቤል የሰው ልጅ ክብርን ከእግዚአብሔር ከመቀበል ይልቅ ለመንጠቅ ሲሞክር ያሳየናል።
3. ራስን መጠበቅ "በምድር ሁሉ ፊት ላይ ሳንበተን" ምጸቱ ይህ ነው፡- እግዚአብሔር የሰው ልጆች ምድርን እንዲሞሉ አዘዛቸው።ነግር ግን የሰው ልጅ እንዲህ አለ፣ አይ ባለንበት እንቆያለን ምድርን በመሙላት የእግዚአብሔርን ሀሳብ ከማስቀጠል እና የእግዚአብሔርን ስም ከማስጠራት ይልቅ በምትኩ ወደ ላይ ወደሰማይ እንገነባለን የሚል ሙከራ አደረጉ።የሰው ኩራት የእግዚአብሔርን ንድፍ/ፕሮግራም ወይም ዘላለምዊ ዕቅድ ይቃወማል እና በሰዎች ፍላጎት ይተካዋል።
III. የእግዚአብሔር ሉዓላዊ ጣልቃገብነት (ዘፍጥረት 11፡5-7)
ሰወች በአንድነት የእግዚአብሔርን እቅድ በመቃወም ሲንቀሳቀሱ እግዚአብሔር ዝም ብሎ አይመለከትም በእንቅስቃሴአችው መሀል ጣልቃ ገብቶ እቅዱን ያስቀጥላል።"እግዚአብሔርም የአዳም ልጆች የሠሩትን ከተማና ግንቡን ለማየት ወረደ" ይህ ንግግር ቅዱስ ምፀት ነው። የሰው ዘር “እስከ ሰማይ ድረስ የሚደርስ ግንብ” ሠርቷል፤ ሆኖም እግዚአብሔር ይህን ለማየት መውረድ ነበረበት። ሰወች የሰሩት ይህ ግንባቸው ለእግዚአብሔር አስጊ አልነበረም፣ ነገር ግን ኩራታቸው ለራሳቸው አደጋ ነበር። ምክንያቱም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። "ያሰቡትን ሁሉ ለመስራት አይከለከሉም።”
ኑ እንውረድ አንዱ ያአንዱን ነገር እንዳይስማው ቋንቋቸውን በዚያ እንደባልቀው።" እግዚአብሔር ይህን ያደረግው ሰውን በመፍራት ሳይሆን ከምሕረቱ የተነሳ ነው።ምክንያቱም ከቁጥጥር ውጪ የሆነ የሰው ልጅ ኩራት ወደማይታወቅ ክፋት ሰውን ይመራልና ነው። እግዚአብሔር ጣልቃ የሚገባው የሰውን ልጅ ለማጥፋት ሳይሆን ኃጢአትን ለመገደብ ነው። ስለዚህ ቋንቋቸው ድባልቆ ግራ ያጋባቸው። ይህ አንድ ወሳኝ ነገር ያስተምረናል እግዚአብሔር በሰዎች ግንኙነት ላይ እንኳን ሉዓላዊ ነው። ሰዎች የእግዚአብሔርን ስልጣን ሲቃወሙ ግራ መጋባት ይከሰታል።
IV. የሰው ልጅ ኩራት ውጤቱ ግራ መጋባትና መበታተን ነው (ዘፍ 11፡8–9)
"እግዚአብሔርም ከዚያ ወደ ምድር ሁሉ በተናቸው፥ ከተማይቱንም መሥራት ተዉ። አሁን በጣም የፈሩት መበታተን እውን ሆነ። ነገር ግን ልናስተውል የሚገባን እውነት እግዚአብሔር አሁንም የመጀመሪያ ትዕዛዙን ይፈጽማል እንጂ ሀሳቡን አይቀይርም። ይሁን እንጂ የሰው ልጅ ምድርን የሞላው በመታዘዝ ሳይሆን በፍርድ ነው። ባቤል የሚለው ስም ግራ መጋባት ማለት ነው። ይህ የእግዚአብሔር ጣልቃ ገብነት የሚያሳየን ከባድ ግን የአፍቃሪነት እውነት፡- ሰዎች ያለ እግዚአብሔር ለመነሳትና እራሳቸውን ለማክበር ሲሞክሩ እግዚአብሔር እቅዳቸው እንዲፈርስ ይፈቅዳል።
V. ሥነ-መለኮታዊ ነጸብራቆች
1. ኩራት ሁሌም ወደ ግራ መጋባት ይመራል። ኩራት ፍርድን ያደበዝዛል። ትዕቢት ግንኙነቶችን ይሰብራል። ኩራት ግልጽነትን በግራ መጋባት ይተካል የሚለውን ነው።
2. ታሪክን የሚቆጣጠረው እግዚአብሔር ብቻ ነው። ስርዎ መንግስታት ይነሳሉ ይወድቃሉ። ቋንቋዎች ይለወጣሉ። ዕቅዶች ይወድቃሉ። ነገር ግን የእግዚአብሔር አላማ ሳይሰናከል ወደፊት ይሄዳል።
3. የእግዚአብሔር ፍርድ ምሕረትም ነው። በባቤል ተሳክቶለት ቢሆን ኖሮ የሰው ልጅ ላልተወሰነ ጊዜ በአመጽ ወይም እግዚአብሔርን በመቃወም ይተባበር። እግዚአብሔር የማዳን እቅዱን ለመጠበቅ ትዕቢታቸውን አፈረሰ።
VI. ከወንጌል ጋር ያለው ግንኙነት
ባቤል የሰው ልጅ የታሪኩ መጨረሻ አይደለችም።በባቤል ሰወች በቋንቋዎች ግራ ተጋብተው ነበር።ስለዚ ሰዎች በምድር ሁሉ ተበታተኑ። ነገር ግን በጰንጠቆስጤ ቀን ደግሞ (የሐ ሥራ 2) ሰወች የሚናገሩትን ቋንቋዎች ሰወች ተረድተዋል። ስልዚህ መበተን ስይሆን ሰዎች ተሰበሰቡ የሰው ኩራት ሰውን በከፋፈለበት፣ የእግዚአብሔር መንፈስ አንድ እንዲሆን አድርገው። በባቤል ሰው በራሱ ጥረት ማድረግ ያልቻለውን አደረገ እስከ ሰማይ ድረስ ግንብ አልሠራም።ኢየሱስ እኛን ለማዳን ከሰማይ ወረደ፣ ለባቤል ፈውሱ የተሻለ መግባባት ሳይሆን በክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ፊት ትሁት ሆኖ መገኘት ነው።
VII. ለእኛ ያለው ፋይዳ ምንድነው?
1. ሕይወትን የምንገነባው ስማችንን ታላቅ ለማድረግ ነው ወይስ የእግዚአብሔርን ስም ለማክበር? ተነሳሽነታችንን መፈተሽ ይገባናል።
2. እግዚአብሔር ከሌለበት ምኞት መጠንቀቅ ያስፈልገናል ለእግዚአብሔር መገዛት የሌልበት ስኬት ወደ ግራ መጋባት ይመራልና።
3. የእግዚአብሔርን ሉዓላዊነት እንመን የእግዚአብሔር ዕቅዶች በሰወች ምክንያት ከሰወች ህይወት ቢከሽፉም እንኳ፣ የእግዚአብሔር ዓላማዎች ፈጽሞ አይሠረዙም።
ማጠቃለያ
የባቢሎን ግንብ የሚከትሉትን እውነታዎች ያስታውሰናል፡-የሰው ኩራት የሚፈርሱ ሀውልቶችን ይገነባል። የእግዚአብሔር ሉዓላዊነት ግን ለዘላለም የሚኖር መንግሥት ይገነባል።ስለዚህ በራሳችን ጉልበት ወደ ሰማይ ለመድረስ አንጣር።ይልቅ በዚያ ሆኖ ከሚገዛው አምላክ ጋር በትሕትና እንመላለስ።
Source: https://cmaeec.com/w...
John 3:16
Whoever believes in him shall not perish but have eternal life.