Home » የዘፍጥረት መጽሐፍ (Tuesday Sermons) » Tuesday – April 7, 2026

የዘፍጥረት መጽሐፍ ታሪካዊ ዳራ

Last updated on April 7, 2026 - by Pastor Tariku Eshetu

5ኛው ሳምንት ዘፍጥረት 6-9

የጥፋት ውሃ - የኀጢአት ፍርድ እና ጸጋ

መግቢያ

በቅዱሳት መጻህፍት ውስጥ ካሉት በጣም ኃይለኛ እና አሳሳቢ ታሪኮች አንዱ የጥፋት ውሃ ታሪክ ነው።ይህ ታሪክ ወደ ሰዎች አእምሮ እንስሳትን፣ ዝናብን እና ቀስተ ደመናን ያመጣል። ዘፍጥረት 6-9 በዋናነት ስለ ስለኖህ መርከብ ወይም ስለጥፋት ውሀ ዘገባ ማቅረብ አላማው አይደለም። ነገር ግን ስለእግዚአብሔርን ባህሪ ማስትዋወቅ ዋና ዓላማው ነው።ስለዚህ ይህ ክፍል ዓለም በኃጢአት ስትሞላ እግዚአብሔር ማን እንደሆነ ያሳየናል፣ እንዲሁም እግዚአብሔር በፍርድ እና በጸጋ ለኀጢአት እንዴት ምላሽ እንደሚስጥ ያሳየናል። በዚህ ታሪክ መሃል ኖኅ የተባለ አንድ ሰው ቆሟ እንያለን። ኖህ የኖረው ከእግዚአብሔር በራቀው ዓለም ውስጥ ነው፣ነገር ግን የእምነት፣ የመታዘዝ እና የመተማመን ምሳሌ ሆነ። የጥፋት ውኃ ይህንን ዋና እውነት ያስተምረናል የእግዚአብሔር ፍርድ በኀጢአት ላይ እውነት ነው ነገር ግን ሁልጊዜ በጸጋ ይታጀባል የሚለውን።

I. በኃጢአት የተጨናነቀ ወይም የተበከለ ዓለም

ዘፍጥረት 6 የሰውን ልጅ የአጥፊነት ምስል ምን ያህል እንድሆነ ያሳየናል። ቅዱሳት መጻሕፍት የሰው ልጅ ክፋት ታላቅ እንደነበረ እና የልብ አሳብ ሁሉ ያለማቋረጥ ክፉ እንደሆነ ይነግሩናል። ስለዚህ ዓመፅ ምድርን ሞላ፣ ኃጢአት ተደብቆ አልቀረም ነገር ግን ማኅበረሰባዊ ግንኙነቶች እና ባህል የተበላሸ ቀረጽ እንዲይዙ አደረገ።ከዚህ እውነት አንጻር በዚህ ምንባብ እንደምንመለከተው እግዚአብሔር የሚያየው ተግባራትን ብቻ ሳይሆን የልብ ተነሳሽነትንም ጭምር እንደሆነ ነው።እግዚአብሔር ልብን ያያል ስንል እነዚህን እውነቶች ያስታውሰናል፡-
• ኃጢአት ሳይታረም ሲቀር ይስፋፋል።
• የኀጢአት ብክለት መላውን ማህበረሰብ ይነካል
• እግዚአብሔር ክፋትን ሳይቀጣ ለዘለዓለም ቸል አይልም።
ይህ እውነት እግዚአብሔር በሰው ልጆች ላይ ያለው ሀዘንና ፍርድ ከተበላሸ ግንኙነት እንደሚፈስ እንጂ በግድየለሽነት የሚፈጸም ተግባር እንዳልሆን ያሳየናል። እግዚአብሔር ከሰወች ሩቅ አይደለም ስለዚህ በሰወች ኃጢአት በጥልቀት ይጎዳል ወይም ያዝናል። ምክንያቱም ፍጥረቱን ወይም ሰውን ስለ ስለሚወድ።

II. የእግዚአብሔር የፍርድ እውነታ

ዘፍጥረት 6፡5 እንዲህ ይላል። "እግዚአብሔርም የሰው ክፋት በምድር ላይ እንደ በዛ፥ የልቡም አሳብ ሁል ጊዜ ክፉ እንደ ሆነ አየ።" ይህ ጥቅስ የሚያሳየን እግዚአብሔር ከድርጊት በላይ የሰውንም ልብን እንደሚያይ ነው:: በዚህ ጊዜ ዓመፅ፣ ሙስና እና ግፍ ምድርን ሞልተዋታል። የሰው ልጅ የእግዚአብሔርን የህይወት ስጦታ እግዚአብሔርን እራሱን ለመቃወም ይጠቀምበት ነበር።

ሆኖም ፍርድ ከመከሰቱ በፊት እግዚአብሔር ፍርድ እንደሚያመጣ ያውጃል። የጥፋት ውኃ በዘፈቀደ ወይም በአጋጣሚ የመጣ ክስተት አይደለም መለኮታዊ ፍትሕ የሰፈነበትና ሆን ተብሎ የተፈጸመ ተግባር ነው። ይህም ብዙ ጊዜ የምንሸሸውን አንድ ጠቃሚ እውነት ያስተምረናል።እርሱም እግዚአብሔር ቅዱስ ነው የሚለውን እና ኃጢአት መዘዝ ወይም ቅጣት አለው የሚለውን እውነት ነው።

ምክንያቱም በክፉ ላይ የማይፈርድ አምላክ አፍቃሪ አይሆንምና። ፍትህ አስፈላጊ ነው ለምን ከተባለ ህይወት አስፈላጊ ስለሆነ። የጥፋት ውኃ እግዚአብሔር ኃጢአትን በቁም ነገር ወይም ያለዋዝ እንደሚመለከተውና ትዕግሥቱ ከኀጢአት ጋር የመስማማቱ ማስረጃ እንዳልሆነ ያረጋግጥልናል። ፍርድ የእግዚአብሔር ፍላጎት አይደለም ግን አንዳንድ ጊዜ አስፈላጊ ነው።ምክንያቱም እግዚአብሔር ቅዱስ ሥለሆነ።
እግዚአብሔር ኃጢአትን ችላ አይልም በኀጢት ላይ ይፈርዳል።ፍርድ እግዚአብሔር ንዴቱን መወጣቱን የሚያምለክት አይደለም። ነገር ግን በቅድስና እና በፍትህ የሚሰራ አምላክ መሆኑንን የሚያረጋግጥ ነው።ከዚህ እውነት አንጻር ስንመለከት የጥፋት ውኃ ኃጢአት መዘዝ እንዳለበት ያሳየናል፣ እንዲሁም የእግዚአብሔር ትዕግሥት በሰው ዘንድ ተቀባይነት የለውም የሚለውን እውነት እንድንገነዘብ ያደርገናል።

III. በኀጢአትና በፍርድ መካከል የተገለጠ ጸጋ

በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ካሉት በጣም ተስፋ ሰጪ ጥቅሶች አንዱ፡-" ኖኅ ግን በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን አገኘ።የሚለው ነው። ይህ ገለጣ በኀጢአትና በፍርድ መካከል ጸጋ እንድተገለጥ የሚያሳይ ገለጣ ነው። በዚህ ታሪክ ውስጥ ኖኅ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገ ጻድቅ ሰው ተብሎ ተገልጿል:: ይህ ማለት ኖህ ፍጹም ነበር ማለት አይደለም ነገር ግን ኖህ በእግዚአብሔር ታምኖ በታማኝነትና በመታዘዝ ኖረ ማለት ነው።

ኖኅ ግን በእግዚአብሔር ፊት ሞገስን አገኘ ማለት፦በሙስና፣ በአመጽ እና በሚመጣው ፍርድ መካከል የእግዚአብሔር ጸጋ ይታያል ማለት ነው። እግዚአብሔር ጥፋትን ወይም ፍርድን ዝም ብሎ አላወጀም የመዳንንም መንገድ አዘጋጅቶ ነበርና ። መርከቡ መሰራቱ የኖህ ሃሳብ አልነበረም የእግዚአብሔር የጸጋ እቅድ ነበር እንጂ። ጸጋ ሁል ጊዜ በእግዚአብሔር ይጀምራል። ይህ አንድ ጠቃሚ እውነት ያስታውሰናል የእግዚአብሔር ፍርድ ከምህረት አይለይም የሚለውን።እግዚአብሔር ኖኅን መረጠ፣ ለኖኅ ተናገረ፣ እና በኖኅ በኩል የመዳንን መንገድ አዘጋጀ።

IV. ኖህ፡ የእምነት ምሳሌ ነው

ዘፍጥረት ኖህን አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ያደረገ ጻድቅ ሰው እንደሆነ ይገልጻል። ይህ ማለት ኖህ ፍጹም ነበር ማለት አይደለም ነገር ግን በእግዚአብሔር በመታምን በሙስና በተሞላ ዓለም ውስጥ የተለየ ኑሮ ኖሯል ማለት ነው። የኖህን እምነት ስናስብ በጣም አስገራሚ ሆኖ እናገኘዋለን።ማንም በማያደረገው ጊዜ እግዚአብሔርን ታዘዘ አንዲት ጠብታ ዝናብ ሳይዘንብ መርከብን ሠራ፣ ከሕዝብ አስተያየት በላይ የእግዚአብሔርን ቃል አመነ። እምነት አንድ ነገር እውነት ነው ብሎ ማመን ብቻ አይደለም።እግዚአብሔር የተናገርውን እውነት መኖር ነው እንጂ። የኖህ ታዛዥነት ዓመታትን ፈጅቷል።ይህም እምነት ትዕግስትን፣ ጽናትን እና በእግዚአብሔር ተስፋ ላይ መተማመንን ይጠይቃል ማለት ነው።

V. በእምነት መታዘዝና መርክብ መሥራት

እግዚአብሔር ኖኅ መርከብ እንዲሠራ አዘዘው።አንድ መቶ ሀያ ዓመታት አካባቢ የፈጀው የመርከቡ ስራ በጣም ትልቅ ነው። ምንም ዝናብ አልነበርም፣በዙሪያው ካለው ባህል የመርከቡ ስራ ትክክል መሆኑን የሚያረጋግጥ ማስረጃ እና ማበረታቻ የለም ቢሆንም ኖኅ በእምነት ታዘዘ። እምነት እግዚአብሔር እንዳለ ማመን ብቻ አይደለም በቃሉ ላይ እርምጃ በመውስድ በእግዚአብሔር መታመንን ጭምር ነው።የኖህ ታዛዥነት ይህንን ያሳየናል። እምነት ብዙውን ጊዜ ለዓለም ሞኝነት ይመስላል፣እምነትን መታዘዝም ትዕግስትን ይጠይቃል። መተማመን ማለት ውጤቱ ከመታየቱ በፊት መስራት ማለት ነው። ኖኅ መርከቡን የሠራው የእግዚአብሔር ቃል እውነት ነው ብሎ ስላመነ ብቻ ነው።

VI. በእግዚአብሔር አቅርቦት መዳን

የጥፋት ውኃ ሲመጣ እግዚአብሔር ራሱ የመርከቧን በር ዘጋው።ከጥፋት ውሀ ማምለጭ አንድ መርከብ ብቻ በዚያ ነበር። ትውልዱ አይቶት የማያውቀው በእግዚአብሔርና በኖኅ አምካይነት የተሰራ ነው።ለመዳን የነበርው አንድ መንገድ ብቻ ነበር። በመርከቧ ውስጥ ያሉት ሁሉ በሕይወት የተረፉት መርከቡ ውስጥ መግባት ስለሚገባቸው ሳይሆን በእግዚአብሔር ዝግጅት ላይ እምነት ስለነበራቸው ነው። ይህም መዳን ምንጊዜም የእግዚአብሔር ሥራ እንደሆነ ያስተምረናል። እግዚአብሔር መንገዱን ያዘጋጃል ሰዎች ደግሞ በእምነት ምላሽ ይሰጣሉ።ድኅነትም የዚህ መስተጋብር ውጤት ነው።

VII. እግዚአብሔር ኖኅን አሰበ

ዘፍጥረት 8፡1 እንዲህ ይላል።”እግዚአብሔር ግን ኖኅን አሰበ”።ይህ ማለት ግን እግዚአብሔር ኖኅን ረስቶት ነበር ማለት አይደለም።ነገር ግን እግዚአብሔር በታማኝነት የማዳን ስራውን ይሰራ ነበር ማለት ነው። በዚህ ስራው ውስጥ ውሃው ቀነሰ፣ደረቅ መሬት ታየ፣ ሕይወት እንደገና ተጀመረ።ምክንያቱም ፍርዱ ለዘላለም አልነበርምና ጸጋ የእግዚአብሔርን የማዳን ታሪክ ወደፊት ያንቀሳቅሰዋል። የእግዚአብሔር ዓላማ ጥፋት ሳይሆን ተሐድሶ ነው። ጸጋ በሕልውና አያበቃም ወደ መታደስ ይመራል።

VIII. አምልኮ፣ ቃል ኪዳን እና ተስፋ

ኖኅ ከመርከቡ ከወጣ በኋላ የመጀመሪያው ተግባሩ አምልኮ ነው። ስለ ድኅነት እግዚአብሔርን አመሰገነ።እግዚአብሔርም በተስፋ ቃልና በኪዳን የታጀበ ምላሽ ሰጠ። ሕይወትን ለመጠበቅ እና ምድርን ዳግመኛ በጎርፍ ላያጠፋም ራሱን ሰጥቷል(እዚአብሔርም በልቡ አለ) ። ቀስተ ደመናውም የዚህ የተስፋ ቃል ምልክት ሆነ ይህም ምህረት ፍርድን እንደሚከተል ማስታወሻ ነው። ከዚህ የትነሳ እያንዳንዱ ማዕበል አሁን የጸጋን ተስፋ ይሸከማል።

የዚህ ታሪክ ዋና ሀሳብ

ኖኅ በኃጢአተኛ እና ከእግዚአብሔር በራቀ ዓለም ውስጥ ግየእምነት ምሳሌ ሆኖ ቆሟል። የጥፋት ውሃ የእግዚአብሔር ፍርድ እውነተኛ እና ከባድ እንደሆነ ይገልፃል፣ነገር ይሁን እንጂ ሁል ጊዜ የእግዚአብሔር ፍርድ በጸጋ ይታጀባል። እግዚአብሔር ድኅነትን ይሰጣል፣ሰው ደግሞ በእምነትና በታዛዥነት ለእግዚአብሔር ምላሽ ይሰጣል።እግዚአብሔርም ህይወትን ይጠብቃል እንዲሁም ለፍጥረታቱ ታማኝ ሆኖ ይኖራል የሚል ነው።

ለዛሬ ያለው ትምህርት

እግዚአብሔር አሁንም በዚህ ዘመን ልብን ያያል ይፈርዳልም፣እምነት አሁንም መታዘዝን ይጠይቃል፣እግዚአብሔር አሁንም የመዳን መንገድን ይሰጣል፣ የእግዚአብሔር የተስፋ ቃል አሁንም የታመ ነው።ምናልባት ዛሬ ዓለም አቀፋዊ ጎርፍን ላንጋፈጥ እንችላለን፣ ነገር ግን በዕለታዊ ምርጫዎቻችን ይህ ጎርፍ ሊያጋጥመን ይችላል እናም እንደ ኖህ ከእግዚአብሔር ጋር እንሄዳለን ወይስ ዓለምን እንከተላለን?

ማጠቃለያ

የጥፋት ውኃ ታሪክ እግዚአብሔር ጻድቅና መሐሪ መሆኑን ያስታውሰናል። እርሱ በኃጢአት ላይ ይፈርዳል፣ በእርሱ የሚታመኑትን ግን ያድናቸዋል።ስልዚህ አካሄዳችንን ከእግዚአብሔር ጋር ያደርግን ሰዎች እንሁን ለጸጋው በእምነት የታዛዥነት ምላሽ የምንሰጥ፣ እና የምስጋና ሰዎች ልንሆን ይገባል።

Source: https://cmaeec.com/w...

the cross
Jesus is Lord
John 3:16

Whoever believes in him shall not perish but have eternal life.