ንባብ፡- ዘፍጥረት 1-2
መግቢያ
በእያንዳንዱ ትውልድ ውስጥ በጣም አስፈላጊ እና አከራካሪ ከሆኑ ጥያቄዎች አንዱ እኔ ማን ነኝ? የሚለው ነው። ዘመናዊው ስልጣኔ ይህንን ጥያቄ ወደ ውስጥ በመመልከት ለመመለስ ይሞክራል። ይህንም ሲያደርግ ስሜቶችን፣ ፍላጎቶችን፣ ስኬቶችን መስረት በማድረግ ነው። ነገር ግን ቅዱሳት መጻሕፍት ወደ ላይ በማመልከት እንዲህ በማለት ይህን ጥያቄ ይመልሱታል የሰው ፈጣሪ እግዚአብሔር ነው ማንነቱም እርሱ ነህ ያለው ብቻ ነው። ዘፍጥረት ምዕራፍ 1 እና 2 የሚያስተምረን የሰውን ልጅ ማንነት፣ ክብር እና የተፈጠርበትን ዓላማ ነው። ይህ የተፈጠርበት ዓላማ ደግሞ በርሱ የሚወስን ሳይሆን በእግዚአብሔር በተሰጠው ማንነት የተመሰረተ ነው። ስልሆነም ፍጥረትን እስክንረዳ ድረስ እራሳችንን ሙሉ በሙሉ መረዳት አንችልም።
ከዚህ እውነት አንጻር በዚህ ትምህርት የምንይዘው ዋና ሀሳብ (ትልቅ ሀሳብ) እግዚአብሔር ሆን ብሎ የሰውን ልጅ በራሱ አምሳል ስለፈጠረ፣ እያንዳንዱ የሰው ልጅ ሕይወት በፊቱ የተቀደሰ ክቡር፣ መለኮታዊ ዓላማ እና የሞራል ኃላፊነት ያለበት መሆኑን ነው።
ዓላማ
የዚህ ትምህርት ዓላማ እስራኤላውያን የፍጥረትን አስተምህሮ ወይም ነገር ፍጥረትን እና የእግዚአብሔርን መልክ ትርጉም እንዲረዱ፣ እንዲሁም እነዚህ እውነቶች አምልኮአቸውን፣ ሥነ ምግባራቸውን እና የዕለት ተዕለት አኗኗራቸውን እንዴት እንደሚመሩ ለመርዳት ነው።
I) የፍጥረት ፈጣሪ
እግዚአብሔር፦ ስርዓት፣ ሓይልና ቸርነት ዘፍጥረት 1 ፍጥረት ሥርዓት ያለው፣ ሆን ተብሎ የተፈጠረ እና መልካም እንደሆነ ይናገራል። ይህን ሁሉ እግዚአብሔር የፈጠረው በትግል ሳይሆን በሉዓላዊ ቃሉ ነው። "እግዚአብሔርም አለ... እንዲሁም ሆነ።" ፍጥረትን በተመለከት የሚከተሉትን እውነቶች መገንዘብ ተገቢ ነው።
1. ፍጥረት በእግዚአብሔር ቃል መፈጠሩን
እግዚአብሔር ፍጥረትን የፈጥረው ይሁን የሚል ቃል በመናገር ነው። ይህም ፍፁም የሆነውን ሥልጣኑን ያሳያል። ተፈጥሮ እግዚአብሔርን አይቆጣጠርም ነገርግን እግዚአብሔር ተፈጥሮን ያዛል፣ ፍጥረትም የፈጣሪን ድምጽ በመታዘዝ ምላሽ ይሰጣል። የዚህ እውነት ሥነ-መለኮታዊ እውነት፡ ደግሞ የእግዚአብሔር ቃል ኃይለኛ፣ እምነት የሚጣልበት እና የሚስራ ነው የሚል ነው።
2. የፍጥረት በትዕዛዝ እና በዓላማ መፈጠር
ፍጥረት የሚገለጠው በመዋቅር በቀናት፣ በወሰኖች እና በተግባራት ነው። ይህ የፍጥረት ሥርዓት የእግዚአብሔርን ጥበብ እና ሐሳብ ያንጸባርቃል። አጽናፈ ዓለሙ የተመሰቃቀለ ወይም ድንገተኛ ክስተት አይደለም። ነገር ግን በስራዓት የተደራጀ እና ሆን ተብሎ የተነደፈ ነው።
3. ፍጥረት መልካም ተባለ
ከእያንዳንዱ የፍጥረት መፈጠር በኋላ፣ እግዚአብሔር የፍጥረትን “መልካምነት” ያውጃል። ፍጥረት ሲጠናቀቅ ደግሞ “እጅግ መልካም” ነው ተብሎአል። ክፋት ጥንታዌነት የለውም። መልካምነት ግን ጠንታዌነት አለው። ኃጢአት ወደ ዓለም የገባው በኋላ ነው። ስለዚህ የተፈጠረው ዓለም ዋጋና ትርጉም ያለው እንዲሁም ያለኀጢአት የነበረ ነው። ምክንያቱም እግዚአብሔር ስለፈጠረው ነው። ባጠቃላይ የዘፍጥረት መጸሀፍ የመጀመሪያው ምዕራፍ የሚያረጋግጥልን እውነት የእግዚአብሔርን ፈጣሪነት ብቻ ሳይሆን ፍጥረት ሁሉ የእርሱ መሆኑን ጭምር ነው። እግዚአብሔር ፍጥረትን በአላማ ስለፈጠር ይህ ዓላማው እውን እንዲሆን ሰውን በመጨረሻ ፈጠረ። ዘፍጥረት 1 የተዋቀረ፣ ሥርዓት ያለው የፍጥረት ዘገባን ያቀርባል።እንዲሁም የእግዚአብሔርን ኃይል ለንግግር ቃሉ አጽንዖት ይሰጣል። ዘፍጥረት 2 በይበልጥ የሚያተኩረው በሰው ልጅ ላይ ነው፣ ይህም ግንኙነትን፣ ዓላማን እና በእግዚአብሔር እና በሰው መካከል ያለውን ቅርርብ በማጉላት ነው። በመሆኑም እነዚህ ምዕራፎች አንድ ላይ ሆነው ስለ ፍጥረት ትርጉም እና ግብ ተጓዳኝ ምስል ይሰጡናል ማለትነው።
II) በእግዚአብሔር መልክ የተፈጠረ የሰው ልጅ ክቡር ነው (ዘፍ 1፡26-27)
“እግዚአብሔርም አለ፡- ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌአችን እንፍጠር። ሰው የፍጥረት ቁንጮ ነው። የሰው ልጅ ከሌላው ፍጥረት የተለየ ነው። ምክንያቱም፦
1. በመለኮታዊ ሃሳብ እና ምክር ስልተፈጠረ
በዚህ የንባብ ክፍል ውስጥ “እኛ” የሚለው ሐረግ መለኮታዊ መመካከርን ያመለክታል። ሰው ይሁን በሚል ቃል ሳይሆን በመለኮታዊ ምክር(Divine counsel)እና ሃሳብ(Divine Intention) ነው የተፈጠረው። "እንፍጠር"( “Let Us”)የሚለው ብዝሀነትን የሚያሳየው ሐረግ ደግሞ የእግዚአብሔርን ማንነትና ባለጠግነት ይጠቁማል እንዲሁም ሙሉ የሥላሴ መገለጥን የሚናፍቅ ገለጣን የሚያሳይ ነው።።
2. በእግዚአብሔር መልክ ስለ ተፈጠረ (ኢማጆ ዴኢ Imago Dei )
በእግዚአብሔር መልክና አምሳል መፈጠር አካላዊ መመሳሰል ማለት አይደለም። ነገር ግን ውክልናን እና ነጸብራቅን የሚያመለክት ነው።የእግዚአብሔር መልክ (Imago Dei) ትርጉሙም የሚያመለከትው፦
1. ህብርት የማድርግ ችሎታ ወይም የግንኙነት አቅምን (Relational Dimension) ነው። ሰዎች የተፈጠሩት ከእግዚአብሔር ጋር እና እርስ በርሳቸው ተግባቦት ወይም ህብረት ለማድረግ እንዲችሉ ተደርገው ነው።ይህም በእዚአብሔር መልክ የመፈጠር አንዱ ፋይዳ ነው።
2. የሞራል ግንዛቤ መኖር ሥነ ምግባራዊ ችሎታ (Moral Dimension) ሰወች የጽድቅንና የሞራል ኃላፊነት የመወጣት ችሎታ አላቸው እንዲሁም ሰዎች የሞራል ግንዛቤ እና ኃላፊነት አለባቸው።ስልዚህ ሰወች በምርጫቸውም ሆነ በተግባራቸው በእግዚአብሔር ፊት ተጠያቂዎች ናቸው።
3. ኀላፊነትን የመተግበር ብቃት ተግባራዊ ሚና መወጣት (Functional Dimension) የሰው ልጅ ስልጣን ተሰጥቶታል ይህም በእግዚአብሔር ስልጣን ስር በመኖር ፍጥረትን የመመገብ እና ማስተዳደር ስልጣን ነው። ሰዎች እንዲገዙና ፍጥረትን እንዲቆጣጠሩ የአምላክ ተወካዮች ሆነው ተሾመዋል። ስለዚህ ለፍጥረት ተገቢውን ትኩርት መስጠት ከሰወች ይጠበቃል።
4. የወንድ እና የሴት እኩልነት/. የወንድ እና የሴት እኩል ክብር "ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።" ወንዶችም ሆኑ ሴቶች የእግዚአብሔርን መልክ ይሸከማሉ። ስለዚህ የሰው ልጅ ክብር በፆታ፣ በዘር፣ በችሎታ እና በማህበራዊ ደረጃ ላይ የተመሰረተ ሳይሆን በራሱ ባፈጣጠሩ ላይ የተመሰረተ ነው። የዚህ እውነት ሥነ-መለኮታዊ አንድምታ ደግሞ እያንዳንዱ የሰው ሕይወት የተቀደሰ ነው የሚል ነው።
III) ለግንኙነት እና ለዓላማ የተፈጠረው የሰው ልጅ (ዘፍጥረት 2)
ዘፍጥረት 2 የእግዚአብሔርን ግላዊ ተሳትፎ በሰው ልጅ ላይ አሳድጎ ያሳየናል። ይህም፦
1. የእግዚአብሔር ግላዊ የሰው ልጅ አፈጣጠር
እግዚአብሔር አዳምን ከምድር አፈር አበጀው የሕይወትን እስትንፋስም በአፍንጫው እፍ አለበት። የሰው ልጅ ከሁለት አካል የተገኘ ንጹህና ትሁት ፍጥረት ነው። ይህም ከምድር አፈር እና ከፍ ካለው ከእግዚአብሔር (ከእግዚአብሔር እስትንፋስ የተሰጠ) ነው።
2. እንደ እግዚአብሔር ጥሩ ንድፍ ሥራ ሆኖ ተፈጠር፦
ዘፍጥረት 2 እግዚአብሔር ሰውን በጥንቃቄ እና ለግላዊ ተሳትፎ ሲፈጥር ያሳየናል። እግዚአብሔር አዳምን የአትክልቱን ስፍራ (ኤደን ገነትን) እንዲያበጃት እና እንዲጠብቃት ሐላፊነት እዲወስድ አድርጎታል። ይህም ለአዳም የተሰጠው የስራ ሀላፊነት፣ ስራ የእግዚአብሔር መልካም እቅድ አካል እንጂ የውድቀት ውጤት እንዳልሆነ ይገልጻል። የሔዋን መፈጠር ደግሞ የሰው ልጅ የተነደፈው(designed) ለማህበረሰባዊነት እንጂ ለመገለል ወይም ብቸኛ እንዲሆን እንዳልሆነ ያሳያል።
3. ማህበረሰብ እና ጋብቻ
እግዚአብሔር ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ "መልካም አይደለም" ሲል ተናግሯል። ስለዚህ ሔዋን ተስማሚ አጋር ሆና ተፈጠረች።በመሆኑም ጋብቻ ሰወች ምድርን እንዲሞሏት በእግዚአብሔር የተቋቋመ/የተመስርተ የቃል ኪዳን ግንኙነት እና የእግዚአብሔር ተቋም ነው።
V) የነገረ-ክርስቶስ ፍጻሜና እውነተኛው የእግዚአብሔር መልክ መመለስ
በሰው ልጆች ውስጥ ያለው የእግዚአብሔር መልክ በኃጢአት ተጎድቷል ነገር ግን አልጠፋም። "እርሱ የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው"(ቆላ 1:15) ኢየሱስ ክርስቶስ እግዚአብሔርን ፍጹም በሆነ መልኩ ገልጧል። እንዲሁም የተበላሸውን የእግዚአብሔር መልክ በቤዛነት አድሷል።" አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኗል"(ሮሜ 8፡29)። ከዚህ የተነሳ በክርስቶስ ያመኑ አማኞች እንደገና የእግዚአብሔርን ባህሪ ለማንፀባረቅ ይታደሳሉ።
IV) የፍጥረት ሥነ-መለኮታዊ አንድምታ እና ኢማጆ ዴኢ(Imago Dei)
Ø የሰው ሕይወት ቅድስና - የሰው ሕይወት ከመፀነስ እስከ ሞት ድረስ የተቀደሰ ነው።
Ø የሰው ሃላፊነት - ሰወች እንዴት እንደምንኖር በእግዚአብሔር ፊት ተጠያቂዎች ነን።
Ø የፍጥረት መጋቢነት - የበላይነት ማለት እንክብካቤ እንጂ ብዝበዛ አይደለም።
Ø ለሥ ነምግባር መሰረት ነው - ፍትህ፣ ርህራሄ እና የክብር ፍሰት የሚመጣው ከኢማጆ ዴኢ(Imago Dei) እንደሆነ ለማሳየት ይህ ስነ መልኮት እዚህ ጥቅም ላይ ውሏል
ለዚህ ዘመን የሚያስተምረን እውነት ምንድን ነው?
እያንዳንዱን ሰው ዋጋ በመስጠት እና በአክብሮት መያዝን፣ በእግዚአብሔር ሥልጣን ሥር በኃላፊነት መኖርን። ሥራን፣ ጋብቻን እና ማህበረሰብን እንደ እግዚአብሔር ንድፍ አክብሮ መያዝ። የእግዚአብሔርን ባህሪ በቅድስና፣ በፍቅር እና በመታዘዝ የማንጸባረቅ ኀላፊንትን ያስተምርናል።
ማጠቃለያ
ዘፍጥረት 1-2 ከየት እንደመጣን ብቻ ሳይሆን ማን እንደሆንን ያስተምረናል። የተፈጠርነው በእግዚአብሔር መልክ እና ለክብሩ ነው። እውነተኛ ማንነት የሚገኘው ሰው ለሰው ማንነት በስጠው መላምት ውስጥ ሳይሆን በመለኮታዊ ንድፍ ውስጥ(in gdivine desin) ነው። ሰወች የእግዚአብሔርን መልክ ስለምንሸከም፣ በቅድስና፣ በትሕትና እና በፍቅር እንድንኖር ተጠርተናል ወይም ይጠበቅብናል። ሌሎችን በክብር መያዝ፣መጋቢ ፍጥረትን (የፍጥረት ባላደራነትን) በኃላፊነት መያዝ አለብን፣እንዲሁም በዕለት ተዕለት ህይወታችንም የእግዚአብሔርን ባህሪ በማንጸባረቅ መኖር አለብን።
Source: https://cmaeec.com/w...
John 3:16
Whoever believes in him shall not perish but have eternal life.