“በመጀመርያ እግዚአብሔር” ዘፍ 1፡1
መግቢያ
እያንዳንዱ የዓለም አተያይ ወይም ንጽረተ ዓለም የሚጀምረው ስለ ስለፍጥረት ጅማሮ ከማሰብ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በክርክር፣ በመከላከያ ወይም በፍቺ አይጀምርም የፍጥረትን ጅማሮ በተመለከት ለእግዚአብሔር ነዋሪነት እውቅና በመስጠት ስለዓለም ጅማሮ እንዲህ በማለት ያስረዳል፡- “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” በማለት ይጀምራል። በእነዚህ ቃላት፣ ቅዱሳት መጸሐፍት ( መጻሕፍ ቅዱስ) ለሁሉም እውነት፣ እምነት እና ሕይወት መሠረትን ይጥላል። ዘፍጥረት ስለመጀመሪያዎች ብቻ የሚናገር አይደለም ከመጀመሪያ ነገሮች ሁሉ በፊት እውቅና የሚሰጠው ስለ እግዚአብሔር ነው። እግዚአብሔር የሁሉ ነገር ሉዓላዊ ፈጣሪ ስለሆነ ሕይወታችን፣ እምነታችን እና መጪው ጊዜ በእርሱ መጀመር አለበት። ይህን ለመገንዘብ እንድንችል የሚከተሉትን እውነቶች እንመልክታለን።
1፡የዘፍጥረት አንድ ታሪክዊ ዳራ እና ዓላማ
የዘፍጥረት መጽሐፍ የተጻፈው ለእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ሕዝብ መሠረታዊ የሆኑትን የሕይወት ጥያቄዎች ለመመለስ ነው፡ እግዚአብሔር ማን ነው? እኛ ማን ነን? ለምንድነው ዓለም በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ያለችው? ከዚህ አንጻር ዘፍጥረት ሥነ-መለኮታዊ ታሪክ እና በመለኮታዊ መገለጥ የተተረጎሙ እውነተኛ ክስተቶችን በመጠቀም ዘላለማዊ እውነትን ለማስተማር የተጻፈ መጸሐፍ ነው። ከግብጽ የወጡ እስራኤላውያን መቤዠትን ከመረዳታችው በፊት ፍጥረትን መረዳት ነበረባቸው ይህም መጸሐፉ የተጻፈበት ሌላው ምክንያት ነው።
2፡ ዘፍ 1፡1 ገለጣ “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ።
2፡1. "በመጀመሪያ" - እግዚአብሔር እና ጊዜ
ጊዜ ራሱ ጅማሮ አለው። እግዚአብሔር ግን ጅማሮ የለውም ። እርሱ ከዘመን ወይም ከጊዜ ውጭ የሆነ ዘላለማዊና፣ ራሱን የቻለ ያልተፈጠረ ነው። ለመኖሩ ምክንያት የሌለው ነው። ይህ እውነት ኩራት/ትዕቢትን ፊት ለፊት በመጋፈጥ እና ታሪክ በዘፈቀደ የሚጎዝ እንዳልሆነ ያስታውሰናል። እግዚአብሔር ታሪክን ይመራዋል።
2.2 "እግዚአብሔር" - ማዕከላዊ ተዋናይ ነው።
“እግዚአብሔር” የቅዱሳት መጻሕፍት የመጀመሪያ ዓረፍተ ነገር ርዕሰ ጉዳይ ነው። ይህ ዓርፍተነገር እንዴትና ለምን ለሚለው ጥያቄ ምላሽ አይሰጥም ነገር ግን መፍጠር በሚለው ይጀምራል። መጽሐፍ ቅዱስ በእግዚአብሔር ይጀምራል ምክንያቱም ሕይወት ትርጉም የሚሰጠው እግዚአብሔር ማእከል ሲሆን ነው። እግዚአብሔር ከማእከላዊነት ሲወገድ ግራ መጋባት ይከተላል። የዘፍጥርት መጽሐፍ ድግሞ ይህን ያረጋግጣል።
3. "ፈጠረ" - መለኮታዊ ኃይል እና ስልጣን
ፈጠረ የሚለው የአማርኛ ቃል አቻ የሆነውና “ባራ” የሚለው የዕብራይስጥ ቃል ፍጥረት ከምንም የተፈጠረ መሆኑን ያመለክታል። እግዚአብሔር ከራሱ ውጭ የምንም ነገር ጥገኛ አይደለም። ፍጥረት ሁሉ ግን የእርሱ ጥገኛ ነው። ይህም የእግዚአብሔርን ፍፁም ሥልጣን በፍጥረት ሁሉ ላይ መሆኑን ያረጋግጣል።ፍጠረት ሁሉ ከእርሱ ስልጣን ውጪ መሆን
አይችልም።
4. "ሰማያትና ምድርን" - አጠቃላይ የፍጥረት መገኛ እርሱ ነው።
ይህ ሐረግ የሚያመለከተው ሁሉንም ማለትም የሚታዩ እና የማይታዩን ሁሉ ማለት ነው። ይህም የሚያረጋግጠው ከእግዚአብሔር የመፍጠር ኃይል ወይም ሉዓላዊ አገዛዝ ውጭ የሆነ ነገር የለም የሚለውን ነው።
- ሥነ-መለኮታዊ አንድምታዎች
በመጀመሪያ፣ እግዚአብሔር በታሪክ ላይ ሉዓላዊ ነው። ሁለተኛ፣ ፍጥረት ትርጉምና ዓላማ አለው። ሦስተኛ፣ አምልኮ እግዚአብሔር ፈጣሪ መሆኑን የመገንዘብ ትክክለኛው ምላሽ ነው። እግዚአብሔርን ፈጣሪ አይደልም ብሎ መካድ የስልጡን አስተሳሰብ ስህተት ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊ ዓመፅ ነው።
- ከነገር ክርስቶስ ጋር ያለው ግንኙነት
አዲስ ኪዳን ፍጥረት በራሱ በክርስቶስ እንደተፈጠረ ይነግረናል (ዮሐንስ 1፡1–3፤ ቆላ 1፡16) ስለዚህ የዘፍጥረቱ አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ ሙሉ በሙሉ የተገለጠ አምላክ ነው። ዓለምን የፈጠረው እርሱ ደግሞ የሚቤዠው እርሱ ነው።
ማጠቃለያ
እግዚአብሔር ፈጣሪ ከሆነ እኛ እራሳችንን አልፈጠርንም። ህይወታችን የእርሱ ነው። የተጠራነው በእርሱ ሉዓላዊነት እንድንታመን፣ ለስልጣኑ እንድንገዛ እና እርሱን በትህትና እንድናመልከው ነው። ስለዚህ የምንወስነው ውሳኔ ሁሉ ከእግዚአብሔር መጀመር አለበት። መጽሐፍ ቅዱስ እንድሚያስተምረው ሁሉም እውነት መጀመር ያለበት ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው። ምክንያቱም ከኃጢአት፣ ከመከራ፣ ወይም ከድነት በፊት፣ እግዚአብሔር ነበር። እንዲሁም እግዚአብሔር መጀመሪያ ላይ ስለነበረ አሁን ባለን እና በወደፊት ሕይወታችን በእርሱ ልንታመን እንችላለን። ይገባናል።
Source: https://cmaeec.com/w...
John 3:16
Whoever believes in him shall not perish but have eternal life.